በሞጣ ሦስት መስጅዶችና አንድ ቤተክርስቲያን ተቃጠሉ
በማኅበራዊ ድረገጾች ላይ የተሠራጨው በሞጣ የነበረው ቃጠሎ ከሚያሳይ ቪዲዮ ላይ የተወሰደ
የንግድ ተቋማትም ላይ ቃጠሎ ደርሷል
ኢዛ (ቅዳሜ ታኅሣሥ ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 21, 2019)፦ ትናንት ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት ላይ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ አካባቢ በሦስት መስጅዶችና በአንድ ቤተክርስቲያን ላይ የደረሰው ቃጠሎ በአካባቢው ያለመረጋጋት እንዲፈጠር ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ድርጊቱን አውግዘዋል።
ትናንት በሞጣ ከተማ ቃጠሎ ከደረሰባቸው ሦስት መስጅዶች ውስጥ በቀበሌ 03 የሚገኘው መስጅድ ሙሉ ለሙሉ የተቃጠል ሲሆን፣ በቀበሌ 05ና 06 የሚገኙት መስጅዶች በከፊል የቃጠሎው ሰለባ ኾነዋል። ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንም በከፊል በቃጠሎው መጠቃቱ ታውቋል። የቃጠሎ ምክንያት እስካሁን ይፋ ባይኾንም ጥቃቱ ከቤተ እምነቶቹ አልፎ በንግድ ተቋማት ላይ ጭምር ያነጣጠረ እንደነበር ተገልጿል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ ትናንት ምሽት በመስጅዶቹና በቤተክርስቲያኑ ላይ የእሳት ቃጠሎ መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ነው። አንድ የገበያ ማዕከልም ተቃጥሏል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በዚህ ድርጊት ላይ ተሳታፊ የኾኑ ተጠርጣሪዎችን አፈላልጎ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል። የክልሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ድርጊቱን አቅደው መርተዋል ተብለው የተጠጠሩ አምሥት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው የማጣራት ሒደት መጀመሩንና ሌሎች ተጠርጣሪዎችም ላይ ክትትል እየተደረግ መኾኑን ገልጿል።
ዛሬ ከቀትር በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ድርጊቱን የሚያወግዝ መልዕክት ኧኑረዋል። እንዲህ ያሉ ጽንፈኛ አካሔዶችም አጥብቄ ኧውግዛለሁ ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ ከፋፋይ አጀንዳዎችን በመረዳትና በመጠየፍ የጋራ አንድነታችንን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል። የሃይማኖት ተቋማትም ድርጊቱን በማውገዝ መግለጫ አውጥተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን ባልታሰበው ጥቃት ኀዘን ላይ ለሚገኙ ተከታዮችዋና ለእስልምና እምነት ተከታዮች መግለጫ አውጥታለች። በዚሁ መግለጫዋ፤ “የተፈጸመው ድርጊት ለአገራችን ሰላምና እድገት የማይጠቅም፤ ለዘመናት የቆየ በአብሮነት የመኖር እሴቶቻችንን የሚንድ መኾኑን ሕዝባችን ተረድቶ፤ በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ጉዳዩ እስኪጣራ በትእግሥት እንድትጠባበቁ እናሳስባለን” ብላለች። (ኢዛ)



