ሁለተኛውና ዋና ፀሐፊው አቶ ተክላይ ዛሬ ቃላቸውን ሰጥተዋል

ዳኛው ገንዘቡ እንዳይባክን በሽምግልና እንዲፈታ ጠየቁ

Ethiopia Zare (ኀሙስ ጥቅምት 13 ቀን 2001 ዓ.ም. October 23, 2008)፦ በቫንኩቨር ከተማ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ጠቅላይ ፍ/ቤት የተሰየመው ችሎት በቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት ሁለተኛው ተከሳሽና ምስክር አቶ ተክላይ ጸጋዬ ምስክርነት ሲሰጡና መስቀለኛ ጥያቄ ሲጠየቁ ውለዋል።

 

በትናንትናው ዕለት ምስክርነት መስጠት የጀመሩት የተከሳሾች ዋንኛ ምስክርና በ1995 ዓ.ም. በአቡነ መርቆርዮስ በሚመራው ሲኖዶስ የተቋቋመችውንና ለአስር ዓመትም በዚያ መልኩ የቆየችውን ቤተክርስቲያን በአዲስ ሕግና መተዳደሪያ ደንብ ያለ ህዝቡ ፈቃድ ወደ አባ ጳውሎስ እንዲዛወር ወይንም እነሱ እንደሚሉት ገለልተኛ እንድትሆን አድርገዋል የተባሉት አምስት የቦርድ ዳይሬክተሮች መካከል አቶ አበበ ንስሬ ቀርበው ምስክርነታቸውን መስጠታቸውን መዘገባችን አይዘነጋም። ከአቶ አበበ ንስሬ ስህተቶች በመማርና በነገሩ ውስጥም ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል የሚባሉት አቶ ተክላይ በምስክረነታቸው ላይም ይሁን በመስቀልኛ ጥያቄው ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሲያሳዩ ተስተውለዋል።

 

ቄሱን (አባ ዮሐንስን) ለምን እንዳባረሩ ከራሳቸው ጠበቃ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ፖለቲካ እየተናገሩ ስላስቸገሩ” ነው ብለው መልስ ሲሰጡ የተደመጡት አቶ ተክላይ ምን አይነት ፖለቲካ እንደሆነ በተጠየቁ ጊዜም አባ ጳውሎስን ከፋስሽቱ ኢጣሊያ ጳጳስ ጋር እያስተካከሉ የተናገሩትን አንስተዋል። ‘ልክ የጣሊያን ጳጳስ ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ሊወሩ ሲመጡ የጦር መሳሪያዎቻቸውንና ወታደሮቹን ባርከው እንደላኩት ሁሉ አባ ጳውሎስም የኢህአዴግን ወታደሮች በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜና ከዚያም በኋላ ባርከዋል ብለዋል’ ሲሉ አቶ ተክላይ ምስክርነት ሰጥተዋል። በዚህም ብዙ ሰዎች ተቀይመው ከቤተክርስቲያን እንደቀሩና በዚያና በሌሎች ምክንያቶች ሳቢያም እንዳባረሯቸው መስክረዋል። አቶ ተክላይ ቀደም ሲል ኤርትራዊ የነበሩ ሲሆን፣ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ እስከ ሃያ የሚደርሱ ኤርትራዊያንም እንዳሉ ተናግረዋል። እሳቸው አሁን ከየትኛው እንደሆኑ አልገለጹም።

 

ይሁን እንጂ የአቶ አበበ ንስሬን ያህል በመስቀለኛ ጥያዎች ባይዋከቡም፤ አላውቅም ብለው ሊያልፉ ከሞከሯቸው እውነታዎች ሊያመልጡ አልቻሉም። መጀመሪያ የቫንኩቨር ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ራሷን ችላ ያለማንም ረዳት ትንቀሳቀስ እንደነበር ከሊቀ ካህናት ምሳሌ ጋርም ያላቸው ግንኙነት እንደማንኛውም ቤተክርስቲያን የመንፈሣዊ ግንኙነት ብቻ እንደሆነ ቢመሰክሩም የከሳሾች ጠበቃ በመስቀለኛ ጥያቄያቸው በራሳቸው በአቶ ተክላይና በሥራ ጓደኞቻቸው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በካናዳ የተጻፉና የቫንኩቨሯ ቅ/ማርያም ቤተክርስቲያንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በካናዳ ቅርንጫፍ መሆኗን የሚጠቁሙ ደብዳቤዎችን እያወጣ ባሳያቸው ጊዜ ቤተክርስቲያኗ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በካናዳ ቅርንጫፍ እንደነበረች አምነዋል።

 

በቤተክርስቲያኗ በቆዩበት ጊዜም ከአቶ አበበ ንስሬ በተቃራኒ አቶ ተክላይ አገልጋይ ቄሱ የአባ ጳውሎስንም የአቡነ መርቆርዮስንም ስም እየጠሩ ይቀድሱ እንደነበርና ማንንም ቢጠሩም ግድ እንደማይሰጣቸው ተናግረዋል።

 

አዲስ ቤተክርስቲያን ሲያስመዘግቡና የቤተክህነቷን ገንዘብም ለምን ለህዝቡ በጊዜው ሳያሳውቁ እንዳይንቀሳቀሱ በተጠየቁ ጊዜም አጥጋቢ መልስ ሊያገኙ ተስኗቸው ታይተዋል። የስብሰባ ቃለጉባዔ ብለው ባቀረቡት ሰነድም ላይ መጀመሪያ ከያዙት ማስታወሻ ላይ ጨማምረው ጽፈው እንደሆነ ተጠይቀው ያንን እንዳላደረጉ መስክረዋል። ችሎቱ ነገም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን፣ ከአቶ ተክላይ ቀጥሎ በሽምግልና ካገለገሉት ሰዎች አንዱ የአቶ በላይ ምስክርነት እንደሚሰማ ይጠበቃል።

 

ችሎቱ መጀመሪያ ስምንት ቀን ይፈጃል ብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ተጨማሪ አራት ቀን እንደሚያስፈልገው ዳኛው የጠቆሙ ሲሆን፤ ከዚያ በፊት ግን ጉዳዩ በድርድር-ጉባዔ ሊያልቅ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ደንበኞቻቸውን ጠይቀው ለነገ እንዲያቀርቡ የህዝቡ ገንዘብ በጠበቃ ወጪ መባከኑ ያሳሰባቸው ዳኛ አዘው የዛሬው ችሎት ተጠናቋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!