የዳኛ ውሳኔ ይጠበቃል

Ethiopia Zare (አርብ ሚያዝያ 23 ቀን 2001 ዓ.ም. May 1, 2009)፦ ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደው የቫንኩቨር ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ውዝግብ በተለያየ ጊዜ በተደረጉና ሦስት ሣምንታትን በወሰደው ችሎት ትላንት ጠበቆች ባቀረቡት የማጠቃለያ ሃሳብ መጠናቀቁ ታወቀ። ዳኛው ውሳኔያቸውን እስኪሰጡ ከሳሽና ተከሳሽ ወገኖች በትዕግስት እንዲጠበቁ ጠይቀዋል።

 

የቤተ ክርስቲያኗ ውዝግብ የመጨረሻዎቹ የተከሳሽ መስካሪዎች አቶ ታሪኩ እና ወጣት ክብሮም የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ወጣት ክብሮም ከሀገሩ ኤርትራ ተሰዶ ወደ ቫንኩቨር ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የቤተክርስቲያኗ አባልና ዘማሪ በመሆን ሲያገለግል መቆየቱን ከገለጸ በኋላ፤ የተገኘባቸው ስብሰባዎች ላይ ያያቸውንና የሰማቸውን ሂደቶች አብራርቶ መስክሯል። በተለይ ኖቬንበር 12/2006 እ.ኤ.አ. በተደረገው የሽምግልና ሂደት የድጋፍ ፊርማ ይሰበሰብ እንደነበርና እሱ እንዳልፈረመ፣ የስደተኛውና የሀገር ቤቱ ፓትርያርክ ጉዳይ አለመነሳቱንና በነበሩት ቄስ ላይ ዘማሪ ቡድኑ ቅሬታ እንደነበረው ብዙ ጊዜ ይወያዩ እንደነበር ገልጿል።

 

ከአምስቱ ተከሳሾች አንዱ የሆነው አቶ ታሪኩ ተስፋ ሁለት ፓትርያርክ መኖራቸውን የምታውቀው መቼ ነው ተብሎ ሲጠየቅ በ2007 እ.ኤ.አ. ነው ቢልም፤ ከ95 በኋላ ሲኖዶሱ ሁለት መሆናቸውን አንብቤያለሁ ሲል አስተካክሏል። አቶ ታሪኩ ተከሳሽ ሆኖ በቀረበው ኮሚቴ ውስጥ የገንዘብ ያዥ በመሆኑ ብዙ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን የተጠየቀ ሲሆን፣ በተለይ እነሱ ከመመረጣቸው በፊት የነበረው ኮሚቴ ሲፈርስ የባንክ ገንዘብ በቀድሞው ኮሚቴ ታግዶ እንደነበርና ያንን እገዳ ያስነሳው ማን  እንደሆነ ሲጠየቅ ቄስ ምሳሌ መሆናቸውን እንደማያውቅ ገልጿል። አቶ ታሪኩ ከቄስ ምሳሌ ጋር የመንፈሣዊ እንጅ የአስተዳደር ግንኙነት የለንም ሲል መልስ ቢሰጥም፤ ቄስ ምሳሌ ስለመሆናቸው በወቅቱ በራሱ የተፈረሙ ቼኮችና ኮሚቴው የተጻጻፈው ደብዳቤዎች በማስረጃነት ቀርበዋል።

 

ታላቁ የኃይማኖት አባት አቡነ ይስኃቅ በውጭ የሚገኙትን ፓትርያርክ እንደማይቀበሉ መግለጻቸውን በመጽሔት ላይ ማንበቡን የገለጸው አቶ ታሪኩ፣ ለማስረጃነት ያቀረበው መጽሔት በስደት ላይ ያሉትን ፓትርያርክ በምን ሁኔታ እንደሚያያቸው በግልጽ ያሳየ መሆኑን አንዳንድ በቦታው የነበሩ ሰዎች ለመታዘብ ችለዋል።

 

አቶ ታሪኩ ስለ አዲሱ መተዳደሪያ ደንብ ሲጠየቁ በአቶ ተክላይ የቀረበ ድራፍት ነው እንጂ የመተዳደሪያ ደንብ አይደለም ሲል በመረጃነት የቀረበው አዲስ የመተዳደሪያ ደንብ በአምስቱ የኮሚቴ አባላት ፊርማ የፀደቀ መሆኑንና የአቶ ታሪኩ ፊርማ መኖሩን በተመለከተ ስለፊርማው ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለና ፊርማው ግን የሱ መሆኑን አረጋግጦ በደንቡ ላይ አለመፈረሙን ገልጿል። የስፖንሰር፣ የአባላት መዋጮና ሌሎች ገቢዎችን በሚመለከት አቶ ታሪኩ ጥያቄዎች ቀርበውለት ምላሽ ሰጥቷል።

 

በችሎቱ ላይ የነበሩ ሰዎች በተለይ የወጣት ክብሮምን እውነተኛ ምስክርነት ሲያደንቁና የእውነተኛ ክርስቲያን ምስክርነት ሲሉ የተደመጡ ሲሆን፣ በአቶ ታሪኩ የምስክርነት ሂደት ብዙ የሚያውቃቸውን ነገሮች ደብቋል የተሳሳተ ምስክርነት ሰጥቷል ሲሉ ተደምጠዋል።

 

የመተዳደሪያ ደንቡን በሚመለከት ከሽማግሌዎች አንዱ የነበረው አቶ ጳውሎስ አመሳ  ቀርቦ ምስክርነቱን የሰጠ ሲሆን፣ በሽምግልና ወቅት በእንግሊዘኛ ያዘጋጁትን አዲሱን  መተዳደሪያ ደንብ የእነታሪኩ ኮሚቴ በአቶ ተክላይ በኩል  ለሽማግሌዎች እንደተሰጡና በኦክቶበር 2006 በተደረገው አጠቃላይ ስብሰባ ላይ ለተሰብሳቢዎቹ አቅርበውት እንደነበር ቃላቸውን ሰጥተዋል።

 

የክሱን ጭብጥ በሚመለከት ከከሳሽና ከተከሳሽ ወገን ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡን ጠይቀን፤ ከከሳሽ ወገን ያለአባላት እውቅና በቤተክርስቲያን ላይ አዲስ ቤተክርስቲያን መስርተዋል፣ ከካናዳ አቀፍ ቤተክርስቲያን እንድትለይና ገለልተኛ ነን በሚል ሰበብ ቤተክርስቲያኗ በአባ ጳውሎስ ስር እንድትሆን ሙከራ አድርገዋል፣ የባንክ ገንዘብ ሕገወጥ በሆነ መልኩ አዛውረዋል ብለዋል። በተከሳሽ ወገን አቶ ታሪኩ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉና የፍርዱን ውሳኔ መጠባበቅ ነው ብለዋል።

 

ጠበቆች የማጠቃለያ ሃሳባቸውን ካቀረቡ በኋላ ዳኛው ውሳኔያቸውን እስኪሰጡ በትዕግስት እንዲጠባበቁ በመግለጽ ችሎቱን የዘጉ ሲሆን፣ ሁለቱንም ጠበቆች አነጋግረን ውሳኔው እስከሁለት ወር ሊወስድ እንደሚችል ግምታቸውን ሰጥተዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!