ተከሳሾች ምስክሮቻቸውን ማቅረብ ጀመሩ

የቅድስት ምርያም ቤ/ክርስቲያን የችሎት ውሎ

Ethiopia Zare (ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2001 ዓ.ም. October 22, 2008)፦ ባለፈው ሣምንት በቫንኩቨር ከተማ፣ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ጠቅላይ ፍ/ቤት የቫንኩቨር ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያንን መሰረት ያደረገ ክስ መሰማቱን መዘገባችን ይታወሳል። ችሎቱ በዚህ ሣምንትም ቀጥሎ ውሎ በትናንትናው ዕለት የተከሳሾች ዋንኛ ምስክርና በ1995 ዓ.ም. በአቡነ መርቆሪዎስ በሚመራው ሲኖዶስ የተቋቋመችውንና ለአሥር ዓመትም በዚያ መልኩ የቆየችውን ቤ/ክ በአዲስ ሕግና መተዳደሪያ ደንብ ያለህዝቡ ፈቃድ ወደ አባ ጳውሎስ እንዲዞሩ ወይንም እነሱ እንደሚሉት ገለልተኛ እንድትሆን ካደረጉት አምስት የቦርድ ዳይሬክተሮች መካከል አቶ አበበ ንስሬ ምስክርነት ሲሰጥ ውሏል።

 

ከአንድ ቀን በላይ በፈጀው የምስክርነት ቃልም የተከሳሾች ጠበቃ ቤተክርስቲያኗ ስትመሰረት ከየትኛው ሲኖዶስ ወይም ፓትርያርክ ይወግኑ እንደነበር ሲጠይቅ፤ አቶ አበበ ንስሬ ቤተክርስቲያኗ ሲጀመርም ጀምሮ ገለልተኛ እንደሆነች ቢናገርም፤ በመስቀለኛ ጥያቄ ወቅት ግን እስከ 2006 እ.ኤ.አ. ድረስ የአባ መርቆርዮስን ስም እያነሱ ይቀድሱ እንደነበር ተናግሯል። ከዚያ አስቀድሞ ግን የከሳሾች ጠበቃ “በአገልግሎት ሰዓት የማንን ስም ነበር የምትጠሩት ሲለው” ጥያቄውን በቀጥታ በመመለስ ፈንታ፡ የማናቸውም ስም ቢጠራም ሆን ተብሎ የተደረገ ሳይሆን በአጋጣሚ እንደሆነ፤ ለምሳሌም በ2006 እ.ኤ.አ. ያባረሯቸው ቄስ/መነኩሴ በስህተትና ባጋጣሚ የአባ ጳውሎስን ስም አንዳንድ ግዜ ይጠሩ እንደነበር ሲናገር፤ ዳኛው ጣልቃ ገብተው ማወቅ የሚፈልጉት በአጋጣሚ የሆነውን ሳይሆን “ሆን ብለው የትኛውን ስም ይጠሩ እንደነበር” እንደሆነ ሲጠይቁ አባ መርቆርዮስን እንደሆነ ተናግሯል።

 

ምስክሩ ቀደም ሲል በሰጠው ምስክርነት ላይ አቡነ ይስሀቅ የአቡነ ተክለኃይማኖት፣ ከዚያም በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአቡነ መርቆርዮስ ተከታይ እንደነበሩና አቡነ መርቆርዮስን ጨምሮ ብዙ ሊቃነ ጳጳሳትን በስደት እንደተቀበሉ ተናግሮ ስለነበር፤ የከሳሽ ጠበቃ ለምን ጳጳሳቱ ኢትዮጵያን ለቀው እንደወጡ ሲጠይቀው በነበረው አስተዳደር ደስተኞች ስላልነበሩ እንደሆነ ተናግሯል። ፓትሪያርኩ ለሕይወታቸው ሰግተው እንደተሰደዱና በውጭ እንደሚኖሩ ሲጠየቅ አቶ አበበ ንስሬ ግን በ2006 እ.ኤ.አ. ወደ ኢትዮጵያ በሄደ ጊዜ ብዙ ሊቀ ጳጳሳት ያለውን ሥርዓት ሲቃወሙ እንደተመለከተና ምንም እንዳልደረሰባቸውና ጳጳሳቱ ወደ ኢትዮጵያ መሄድ እንደሚችሉ ተናግሯል።

 

ምስክሩ በተደጋጋሚ በሰጠው ቃል ቤተክርስቲያኗ ከተቋቋመችበት ጊዜ ጀምሮ ከውጪው ሲኖዶስም ይሁን ፓትሪያርክ ጋር እንዲሁም በቶሮንቶ ከሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በካናዳ መስራችና የበላይ ጠባቂ ሊቀ ካህናት ምሳሌ ጋር ምንም አይነት የጠበቀ የሥራም ይሁን የእምነት ግንኙነት እንዳልነበረ የምስክርነት ቃሉን የሰጠ ቢሆንም፤ የከሳሾች ጠበቃ ቤተክርስቲያኗ ከተመሰረተች በኋላ በነበሩት ዓመታት በራሱ በአቶ አበበ ንስሬ የተጻፉ ደብዳቤዎችን አውጥቶ አቶ አበበ እንደ ፀሐፊ ለሊቀ ካህናት ምሳሌ በላከው ደብዳቤ ላይ “እኔ አገልጋይዎ፣ አባ ሀዲስ የተሰኙ የአቡነ ዜና ማርቆስ፣ አቡነ ይስኃቅና የእርስዎ ተቃዋሚ የሆኑ መነኩሴ እዚህ ቫንኩቨር መጥተው ላገልግል ሲሉ፤ የእርስዎ ፈቃድ ከሌለ አልፈቅድም ብለን መልሰናቸዋል" ይላል። “ይሄንን ስትል ምን ማለትህ ነው?” ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄም “ለምን እንደሆነ አላስታውስም። እኔ እንጃ፤ አላውቅም። …” ብሎ ሲመልስ ዳኛው ጣልቃ ገብተው “ብዙ ነገሮችን የማስታወስ ጥሩ ችሎታ አለህ። እንዴት ይሄንን ረሳህ? እኔ እንደምረዳው ከሆነ ይሄ የሚጠቁመው ቤተክርስቲያኗ ወደ ውጪው ፓትሪያርክና ወደካናዳው ሊቀ ካህናት እንደምትገናኙ ነው። እንደዚያ ማለትህ ነው ወይ? ምን ማለት ነው? ሲለው እውነቱን ተነፍገናል ያሉ የከሳሽ ወገኖች ሳቃቸውን ለመቆጣጠር ሲታገሉ ተስተውለዋል።

 

አቶ አበበ መልስ ለመመለስ ብዙ ጊዜ ስለወሰደ ዳኛው ጣልቃ በመግባት መልስህ ይኸው ነው? አታውቅም? ሲሉት አቶ አበበ ለምን ያንን እንዳደረገ በትክክል እንዳላስታወሰ ያንን ማድረጉም ስህተት እንደነበረ አባ ሀዲስ ምናልባትም የአንድ ብሔር (የትኛው ብሔር እንደሆነ አልጠቀሰም) ተወላጅ እንደነበሩና በዚያ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል፤ በሌላ መልኩ ደግሞ አባ ሀዲስ የአባ ጳውሎስ ተከታይ ሆነው እንደመጡ ከነአባ ዜና ማርቆስ ጋርም አንድ እንዳልሆኑ ጠቅሷል።

 

የከሳሽ ጠበቃ አቶ አበበ ንስሬ እንዲመልስለት እንደማያስገድደው ማወቅና ለዳኛው ማሳየት የሚፈልገውም የቫንኩቨር ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ስትመሰረት ጀምሮ የአቡነ መርቆርዮስ ተከታይና የካናዳው ቤተክርስቲያን አካል እንደነበረች እንደሆነ ቢነግረውም፤ አቶ አበበ ግን በማመንና ባለማመን አጣብቂኝ ውስጥ እንደነበር ታይቷል። ችሎቱ ረቡዕና ኀሙስን ቀጥሎ የሚውል ሲሆን፤ የመስቀልኛ ጥያቄው ሂደትም በነገው ዕለት እንደሚቀጥል ታውቋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!