አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት

የ“አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት” መስራቾች

ሕብር ኢትዮጵያና ኢሃን ይገኙበታል

ኢዛ (ሐሙስ ታኅሣሥ ፳፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 2, 2020)፦ በቅርቡ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መልሶ እውቅና ያገኘው ኢዴፓና ሌሎች ሁለት ፓርቲዎች “አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት” የሚል ስያሜ የያዘ ትብብር መፍጠራቸውን ይፋ አድርገዋል። ከኢዴፓ ጋር ትብብር መፍጠራቸውን ያስታወቁት “ህብር ኢትዮጵያ” እና “ኢሃን” ናቸው።

ሦስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ አሁን ላይ የሕልውና አደጋ ውስጥ ናት ብለው የሚያምኑ መኾኑን ትብብሩን ይፋ ባደረጉበት ወቅት በሠጡት መግለጫ ጠቅሰዋል። በአገሪቱ አለ ያሉትን ችግር ይቀለብሳል ያሉትን ጠንካራና እውነተኛ የፌዴራሊስቶች ጎራ መፍጠርን ዓላማ በማድረግ “አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት”ን ለመፍጠር ስለመስማማታቸው አስታውቀዋል።

ፓርቲዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ራሳቸውን ለማሰባሰብና ለማጠናከር የሚጥሩ የኮንፌደሬሽን ኃይሎች መኖራቸውንም በመጥቀስ፤ አብሮነት የተባለው ትብብር ሕዝባዊ ስብሰባዎችን፤ እንዲሁም ሰላማዊ ሰልፎችንም በጋራ የማድረግ ስምምነት ስለመፍጠራቸው ከሠጡት መግለጫ ለማወቅ ተችሏል።

እነዚህ ተባባሪ ፓርቱዎች ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ መካሔድ የለበትም የሚልም አቋም ይዘዋል። አሁን በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ምርጫው መቼም ይካሔድ መቼም በአንድ የምርጫ ማኒፌስቶ በጋራ ለመወዳደር ስለመስማማታቸው አስታውቀዋል። አያይዘውም ምርጫን ማሸነፍ የሚያስችል ውይይትና ድርድር ከወዲሁ ለመጀመር፤ እንዲሁም ከምርጫ በኋላ የጥምር መንግሥት ለማቋቋም አስገዳጅ ሁኔታ ሊፈጠር ስለሚችል በዚህ ዙሪያም ከወዲሁ እየሠራን ነው ብለዋል።

አቶ ልደቱ አያሌው ያሉበት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢዴፓ) ኅዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተወከሉ አምስት አባላት ጋር ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ፤ ምርጫ ቦርድ ታኅሣሥ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. እነ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ፓርቲውን የማይወክሉ መኾኑን አረጋግጧል። ከዚህም ባሻገር ከኢዜማ ጋር ያደረጉት ውሕደት ሕገወጥና በተጭበረበረ መንገድ የተፈጸመ መኾኑን አረጋግጧል። በዚህም መሠረት አቶ ልደቱ ያሉበት ኢዴፓ ሕጋዊ እውቅና እንዳለው ቦርዱ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የተለያዩ አካላትና ተቋማት በደብዳቤ አሳውቋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ