የኢዴፓ አመራሮች ጋዜጣዊ

የኢዴፓ አመራሮች ጋዜጣዊ

ቢሮዎቹ የሚመለሱት አቶ ልደቱ ያሉበት ኢዴፓ ነው

ኢዛ (ሐሙስ የካቲት ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 27, 2020)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለኢዴፓ (የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ) አመራር ቢሮዎቹ እንዲመለሱለት ማሳሰቢያ ሠጠ። ቢሮዎቹ እንዲመለሱለት ምርጫ ቦርድ የወሰነለት፤ አቶ ልደቱ አያሌው ያሉበት ኢዴፓ ነው።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ቀደም ሲል ይጠቀምባቸው የነበሩትና ከፓርቲው በወጡ አባላት እስካሁን ተይዘው የቆዩትን ጽሕፈት ቤቶቹን መልሶ ማግኘት እንዲችል፤ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ አሳውቋል።

ጽሕፈት ቤቶቹ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማና በባህር ዳር ከተማ በሰፈረ ሰላም እንደሚገኙ የገለጸው ምርጫ ቦርድ፤ በኢዴፓ ጽሕፈት ቤቶች ሊጠቀምበት የሚገባው ፓርቲውን እየመራ የሚገኘው የአቶ አዳነ ታደሰ አመራር እንደኾነ ለኮርፖሬሸኑ በጻፈው በዚሁ ደብዳቤ ላይ አመልክቷል። በመኾኑም ኮርፖሬሽኑ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግ ማሳሰቢያውን ጨምሮ ሠጥቷል።

ኢዴፓ ከእነ አቶ ልደቱ አላግባብ በገዥው ፓርቲ (የቀድሞው ኢሕአዴግ) ተነጥቆ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ለሚመሩት፣ ራሳቸውን ጨምሮ አራት የፓርቲው የቀድሞ አመራሮች ተሠጥቶ እንደነበር አይዘነጋም። አዲሱና በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው ምርጫ ቦርድ ታኅሣሥ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሔደው ስብሰባ እነ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ያሉበት ሕጋዊ አለመኾኑን መወሰኑ ይታወቃል። በዚያው ውሳኔ ላይ አቶ ልደቱ ያሉበት ኢዴፓ ሕጋዊ እውቅና ያለው ከመኾኑም በላይ ቀድሞውኑም ያልፈረሰ መኾኑን ማስታወቁ ይታወሳል።

ኢዴፓ የዘንድሮው ምርጫ 2012 የሚካሔድ ከኾነ የሚሳተፍ መኾኑን የገለጽ ቢኾንም፤ ምርጫው መካሔድ የለበትም ከሚሉት በርካታ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ እንደኾነ ይታወቃል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ