የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት የቦርድ አባላት በአዲስ ተተኩ

አዲሶቹ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት የቦርድ አባላት
በቦርድ አባላነቱ የቀጠለው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ነው፤ ኦባንግ ሜቶ ቦርዱን ተቀላቅሏል
ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 12, 2020)፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን በቦርድ አባልነት ሲያገለግሉ የቆዩትን አብዛኞቹን በመሻር፤ አዲስ የቦርድ አባላትና የቦርድ ሰብሳቢ ተሰየመ። ይህም ሹመት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል። የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለቦርድ አባልነት መቅረብ ከፍተኛ ቅሬታ ገጥሞታል።
ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው ከጸደቀላቸው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባላት ውስጥ ታዋቂው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ኦባንግ ሜቶ ተካትቷል። በሹመቱ መሠረት አቶ አወሉ አብዲ የቦርዱ ሰብሳቢ ሲሆኑ፤ የቦርድ አባል ኾነው የተሾሙት ደግሞ ዶ/ር አጋረደች ጀማነህ፣ አቶ ማንያዘዋል እንደሻው፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ ዶ/ር ወዳጄነህ ማህርነ፣ ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ መሐመድ እና አቶ ጌትነት ታደሰ ናቸው።
ይህ ሹመት ከቀድሞዎቹ የቦርዱ አባላት ውስጥ በቦርዱ አባልነታቸው የቀጠሉት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ብቻ ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ሰባቱ የቀድሞ የቦርድ አባላት በሙሉ በአዲስ ተተክተዋል።
የዲያቆን ዳንኤል ክብረት የቦርዱ አባል ኾነው መቅረብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ቅሬታ ቀርቦበት ስለነበር፤ የእሳቸውን አመራረጥ በተመለከተ ምክር ቤቱ ለይቶ ለማየት ተገድዶ እንደነበር ታውቋል። ለዲያቆን ዳንኤል ለብቻ ድምፅ የተሠጠ ሲሆን፤ በዚህም መሠረት በ126 ተቃውሞ፣ በ24 ድምፀ ተአቅቦና በ148 ድጋፍ በአብላጫ ድምፅ የቦርድ አባልነታቸው ጸድቋል።
የቀድሞውን ቦርድ በሰብሳቢነት የሚመሩት አቶ ካሳሁን ጎንፌ እንደነበር የሚታወስ ነው። በአቶ ካሳሁን ጎንፌ ሰብሳቢነት ይመራ የነበረው የቀድሞዎቹ የቦርድ አባላት ወ/ሮ አበበች ሺከቻ፣ ወይዘሮ ጀሚላ ሺምብሩ፣ አቶ በቀለ ሙለታ፣ አቶ ዮናስ አስናቀ፣ አቶ ወንድወሰን አንዷለም፣ አቶ ተካ አባዲ እና ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ነበሩ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከ70 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው መንግሥታዊ የፕሬስ ተቋም ሲሆን፣ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም ሥርዓቶች ሳይቋረጥ የሚታተሙትን አዲስ ዘመን፣ ኢትዮጵያን ሔራልድና ሌሎች በተለያዩ ቋንቋዎች የሚታተሙትን ጋዜጦች በማሳተም ዛሬ የደረሰ ድርጅት ነው። (ኢዛ)