Prosperity Party

ብልጽግና ፓርቲ

የጽ/ቤቱ ኃላፊም መድቧል “ሕዝቡ ለውጡን ይፈልጋል”

ኢዛ (ማክሰኞ መጋቢት ፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 17, 2020)፦ በቅርቡ የተቋቋመው የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱን መክፈቱን አስታወቀ። የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ኾነው እንዲሠሩ አቶ ነብዩ ስሑል ሚካኤል ተመድበዋል።

በትግራይ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት መከፈትን አስመልክቶ በተሠጠ መግለጫ፤ ፓርቲው አገር አቀፍ ፓርቲ በመኾኑ በሁሉም ክልሎች ጽሕፈት ቤት እንደሚከፍት ባስታወቀው መሠረት፤ በመቀሌም የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት መክፈቱን አስታውቋል።

የትግራይ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኾነው የተመደቡት አቶ ነብዩ፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት ለትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚነት ሲታገሉ የቆዩና አሁን ደግሞ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የመጣውን ብልጽግና ፓርቲን በመቀላቀል የትግራይ ሕዝብን ወደ ብልጽግና ለማድረስ ይሠራሉ ተብሏል።

አቶ ነብዩም በበኩላቸው “ለውጡ መደመርን ይዞ የመጣና ይህን እሳቤ ደግሞ ለኢትዮጵያ አንድነት ትልቅ መስዋእትነት ለከፈለው የትግራይ ሕዝብ ብልጽግና ትልቅ ድል ነው” ብለዋል።

“ሕዝቡ ለውጡን ይፈልጋል፣ በምንቀሳቀስበት ወቅትም ከጐናችን እንደሚኾን እናምናለን” ያሉት አቶ ነብዩ፤ የብልጽግና ፓርቲ ዓላማቸው ምርጫውን ማሸነፍና ሕዝቡን የለውጡ ተጠቃሚ ማድረግ እንደኾነ መግለጻቸውን የጽሕፈት ቤቱን መከፈት አስመልክቶ የፓርቲው መረጃ አመልክቷል።

የትግራይ የብልጽግና ፓርቲ የሚመሩት ዶ/ር አብርሃም በላይ እንዲኾኑ መገለጹ አይዘነጋም። በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ በአመራር ደረጃ የተቀመጡ ናቸው።

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ በመቀሌ ከከፈተው ቅርንጫፍ ሌላ ለሁሉም የትግራይ ወረዳና ዞኖች በቅርቡ ይከፍታል ተብሏል። በአዲስ አበባም ተመሳሳይ ቅርንጫፍ ከፍቶ እንደሚንቀሳቀስም ለማወቅ ተችሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ