አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ (በግራ)፣ አቶ ባጫ ጊና (ከላይ መሐል)፣ ወ/ሮ ያለም ፀጋይ (ከላይ በቀኝ)፣ ወ/ሮ ሒሩት ዘመነ (ከታች መሐል)፣ አቶ ነብያት ጌታቸው (ከታች በቀኝ)

አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ (በግራ)፣ አቶ ባጫ ጊና (ከላይ መሐል)፣ ወ/ሮ ያለም ፀጋይ (ከላይ በቀኝ)፣ ወ/ሮ ሒሩት ዘመነ (ከታች መሐል)፣ አቶ ነብያት ጌታቸው (ከታች በቀኝ)

የቀድሞ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በአውስትራሊያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኾነው እንዲሠሩ ተመደቡ

ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፲፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 26, 2020)፦ በቅርቡ ከተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነታቸው ተነስተው አምባሳደር እንዲኾኑ የተሾሙት 15ቱ ባለሥልጣናት ምደባቸውን አወቁ።

ኢትዮጵያን በተለያዩ አገሮች እንዲወክሉ የተሾሙት 15ቱ አዳዲስ አምባሳደሮች የሹመት ቦታቸው ዛሬ መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ሲሆን፤ የቀድሞ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በአውስትራሊያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኾነው እንዲሠሩ ተመድበዋል።

ከ15ቱ አምባሳደሮች ውስጥ ዘጠኙ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት የተመደቡ ሲሆን፤ የወጣቶችና ሕፃናት ሚኒስትር የነበሩት ያለም ፀጋይ ኩባ፣ አምባሳደሩ ሒሩት ዘመነ (የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ነበሩ) ቤልጅየም፣ የቀደሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ባጫ ጊና ሞሮኮ መመደባቸው ታውቋል።

አምባሳደሮቹ በቅርቡ ወደተመደቡባቸው አገራት በመሔድ ሥራቸውን በይፋ እንደሚጀምሩ ይፋ የኾነ ሲሆን፤ አጠቃላይ የ15ቱ አምባሳደሮች ሹመትና የምደባ ቦታቸው የሚከተለው ነው።

ባለሙሉሥልጣን አምባሳደሮች ኾነው የተሾሙት፤ ስም፣ አገር - ከተማ፤

1. ክቡር አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ አውስትራሊያ - ካንቤራ፤
2. ክብርት አምባሳደር ያለም ፀጋይ፣ ኩባ - ሃቫና፤
3. ክብርት አምባሳደር ሒሩት ዘመነ፣ ቤልጄም - ብራሰልስ፤
4. ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ማርቆስ ተክሌ፣ ግብጽ - ካይሮ፤
5. ክቡር አምባሳደር ባጫ ጊና፣ ሞሮኮ - ራባት፤
6. ክቡር አምባሳደር ይበልጣል አእምሮ፣ ሱዳን - ካርቱም፤
7. ክቡር አምባሳደር ምሕረታብ ሙሉጌታ፣ ኤርትራ - አስመራ፤
8. ክቡር አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፣ አልጀሪያ - አልጀርስ፤
9. ክቡር አምባሳደር ተፈሪ መለስ፣ እንግሊዝ - ለንደን፤

አምባሳደሮች ኾነው የተሾሙት፤ ስም፣ አገር - ከተማ፣ የሥራ ኃላፊነት፤

1. ክቡር አምባሳደር አድጎ አምሳያ፤ ስዊድን - ስቶክሆልም፣ ምክትል ሚሲዮን መሪ፤
2. ክቡር አምባሳደር ጀማል በከር፣ ባህሬን - ማናማ፣ ቆንስል ጄኔራል፤
3. ክቡር አምባሳደር አብዱ ያሲን፣ ሳውዲ ዐረቢያ - ጄዳ፣ ቆንስል ጄኔራል፤
4. ክቡር አምባሳደር ለገሰ ገረመው፣ ካናዳ - ኦታዋ፣ ምክትል ሚሰዮን መሪ፤
5. ክብርት አምባሳደር እየሩሳሌም አምደማርያም፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች - ዱባይ፣ ቆንስል ጄኔራል እንዲሁም፤
6. ክቡር አምባሳደር ሽብሩ ማሞ፣ አሜሪካ - ሚኒሶታ፣ ቆንስል ጄኔራል ኾነው እንዲሠሩ መመደባቸው ታውቋል።

በዛሬው ዕለት የምደባቸው ቦታ በይፋ የተገለጸው አስራ አምስቱ የቀድሞ ባለሥልጣናት ከበፊቱ የመንግሥት ኃላፊነታቸው መልቀቃቸው በይፋ የተገለጸውና አምባሳደርነት ሹመታቸው የተሠጣቸው የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም። በወቅቱ የአምባሳደርነት ሹመቱን የሠጡት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ናቸው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!