አቶ ልደቱ በተከሰሱበት ክስ መቃወሚያቸውን አቅረቡ
አቶ ልደቱ አያሌው
የዋስትና ጥያቄው በሕይወት መኖርና ያለመኖር ነው አሉ
ኢዛ (ዓርብ መስከረም ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 18, 2020)፦ አቶ ልደቱ አያሌው ትናንት በተመሠረተባቸው የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት ክስ ላይ መቃወሚያቸውን አቀረቡ። ባቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ላይ ትእዛዝ ለመስጠት ለመስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
ዛሬ ዓርብ መስከረም 8 ቀን 2013 ዓ.ም. በጠበቆቻቸው በኩል የቀረበው መቃወሚያ በዋናነት የሚያመለክተው፤ አቶ ልደቱ በክሱ በተጠቀሰው የጦር መሣሪያ አስተደደር አዋጅ መሠረት እስከ አንድ ዓመት መገልገል ይቻላል፤ የመጠቀሚያ ጊዜ አለው በማለት፤ በዚህም አዋጅ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢነት የለውም በማለት በዚህ አዋጅ መከሰስ የለባቸው የሚል ነው።
ካለባቸው የጤና ችግር አንጻር በውጭ አገር መታከም እንደሚገባቸው በመጥቀስ፤ በዛሬውም ችሎት የዋስትና ጥያቄ ለፍርድ ቤት ቀርቧል።
የአዳማ ዓቃቤ ሕግ ጠበቆቹ ላቀረቡት መቃወሚያ ምላሽ የሰጠ ሲሆን፤ የጤና ሁኔታቸውን በተመለከተም አቶ ልደቱ በአገር ውስጥ ሕክምና ያገኙ በመኾኑ ወደ ውጪ ቢወጡ በዛው ሊቀሩ ስለሚችሉና ለዚህም ማረጋገጫ ስለሌለ የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል።
የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ያደመጠው የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን መርምሮ ትእዛዝ ለመስጠት ለመስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል።
የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ በተመለከተ የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ እንዳመለከቱት ደግሞ፤ አቶ ልደቱ ከልብ ሕመማቸው ጋር ተያይዞ የሚቀርበው የዋስትና ጥያቄ በሕይወት መኖር እና ያለመኖር ነው ብለው ለፍርድ ቤቱ ገልጸው፤ ውጭ አገር ሔዶ የመታከም ጉዳይ ደግሞ፤ ፕሮፌሰር አስራት እንኳን የ20 ዓመት ፍርደኛ ኾነው በጊዜው በነበረው የፍትሕ ሥርዓት እንዲታከሙ ተፈቅዷል ማለታቸውንም አክለዋል። (ኢዛ)



