ንብረትን በስጦታ የማስተላለፍ ውል አገልግሎት ዳግም ጀመረ

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ
የንብረት ሽያጭ ክፍያዎች የባንክ ደረሰኝ ይጠየቅባቸዋል
ኢዛ (ረቡዕ ታኅሣሥ ፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. December 16, 2020)፦ ከብር ኖት ቅያሬው ጋር ተያይዞ ተቋርጦ የነበረውን ንብረትን በስጦታ የማስተላለፍ የውል አገልግሎት እንደተጀመረ ተገለጸ። የሚንቀሳቀስም ኾነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ በባንክ በኩል የሚፈጸም እንደሚኾን ታወቀ።
የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ዛሬ ረቡዕ ታኅሣሥ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው የተቋረጠውን አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ ማስጀመሩንና የሚንቀሳቀስም ኾነ የማንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ክፍያ ግን የተፈጸመበት የባንክ ደረሰኝ የሚጠየቅበት ኾኖ የሚቀጥል ይኾናል ተብሏል።
ከመስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ንብረት ሽያጭ ሲከናወን ግብይቱ በባንክ በኩል ብቻ መፈጸም እንዳለበት ታውቆ፤ በዚሁ መሠረት ሲሠራበት የቆየ ሲሆን፤ ከዚህም በኋላ ተቋርጦ የነበረውም ንብረት በስጦታ የማስተላለፍ የውል አገልግሎትም ይኽንኑ መንገድ ተከትሎ ይሔዳል ተብሏል። (ኢዛ)