ሲሚንቶ

በ290 ብር ይገዛ የነበረው አንድ ኩንታል ሲሚንቶ፤ አሁን እስከ 700 ብር መድረሱ ታውቋል

ኮንስትራክተሮች ለሠራተኞች ደምወዝ ለመክፈል ተቸግረናል እያሉ ነው

ኢዛ (ረቡዕ መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 17, 2021)፦ የሲሚንቶ፣ የብረታብረትና የሌሎች የኮንስትራክሽን ግብአቶች ላይ የተፈጠረው እጥረት፤ በግንባታ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መኾኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር አስታወቀ።

በዚህም እጥረት ሳቢያ ግንባታዎችን በአግባቡ ማካሔድ ባለመቻሉ፤ ኮንስትራክተሮች ለሠራተኞቻቸው ደምወዝ ለመክፈል እንኳን እየተቸገሩ መኾኑን አስታውቆ፤ በአጠቃላይ ኢንዱስትሪው በግንባታ ግብአቶች አቅርቦት እጥረት ምክንያት ችግር ውስጥ ምግባቱንም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቋራጮች ማኅበር ምክትል የቦርድ ሊቀመንበር ኢንጂንየር የሱፍ መሐመድ ጨምረው እንደገለጹት፤ አሁን ባለው የግንባታ ግብአቶች እጥረት ሳቢያም ፕሮጀክቶች እየተቋረጡም ነው። ዘርፉ የገጠመው ሌላው ችግር፤ ከባንክ የገንዘብ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የተጣለው ገደብ፤ ሥራቸው ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል።

በአሁኑ ወቅት ያለው የግብአት እጥረት በመኖሩ እና በግንባታ ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ የሚባል የዋጋ ጭማሪ በመፈጠሩ ለኢንዱስትሪው አደጋ እየኾነ መምጣቱም ተመልክቷል።

የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ ጭማሪን በተመለከተ እንደምሳሌ የሚጠቀሰው ሲሚንቶ ነው። በ290 ብር ይገዛ የነበረው አንድ ኩንታል ሲሚንቶ፤ አሁን እስከ 700 ብር መድረሱ ያለውን ችግር ያሳያል ተብሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ