አቢሲኒያ ባንክ ካፒታል አሥር ቢሊዮን ብር እንዲኾን ወሰነ

አቢሲኒያ ባንክ
ከብሔራዊ ባንክ ጫና ነበረበት
ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 1, 2021)፦ ከግል ባንኮች ውስጥ ቀድመው ከተቋቋሙ ባንኮች መካከል አንዱ የኾነው አቢሲኒያ ባንክ፤ በዛሬው ዕለት ባካሔደው ድንገተኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ፤ የባንኩን ካፒታል አሥር ቢሊዮን ብር ለማድረግ ወሰነ።
ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. የአቢሲኒያ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ለባንኩ ባለአክሲዮኖች የባንኩን ካፒታል መጠን በዚህ ያህል ደረጃ ለማሳደግ አስፈላጊነት ላይ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ፤ ባንኩ እስካሁን የነበረውን የተፈቀደ የ4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ወደ አሥር ቢሊዮን ብር እንዲኾን ውሳኔ ሊያሳልፍ ችሏል።
እስከ አሁን የተከፈለ ካፒታል መጠኑ ደግሞ 3.5 ቢሊዮን ብር (ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር) እንደኾነ ይነገራል። ባንኩ በዚህ ያህል ደረጃ ካፒታሉን ለማሳደግ የብሔራዊ ባንክም ጫና እንደነበረበት የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጸዋል።
በዛሬው የአቢሲኒያ ባንክ ውሳኔ መሠረት ከግል ባንኮች የተፈቀደ ካፒታሉን 10 ቢሊዮን ብር በማድረስ ከአዋሽ ባንክ ቀጥሎ አራተኛው ካፒታል የሚኖረው ባንክ ያደርገዋል። የአዋሽ ባንክ ካፒታል 12 ቢሊዮን ብር ነው። (ኢዛ)