ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ

የኢፌዴሪ አገር መከላከያ ሠራዊት የሠራዊት ግንባታ ዘርፍ ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ

የሕወሓት አመራርና አባላት ከአገር ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል

ኢዛ (ማክሰኞ ሚያዝያ ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 13, 2021)፦ በትግራይ ክልል በስምንት የተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ የነበረ የሕወሓት የሽፍታ ቡድን በአገር መከላከያ ሠራዊት እርምጃ እንደተወሰደበት ተገለጸ።

በትግራይ የሚንቀሳቀሰውን የሕወሓት ቡድን በማስመልከት በኢፌዴሪ አገር መከላከያ ሠራዊት የሠራዊት ግንባታ ዘርፍ ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፤ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ ነበር ያሉት የሕወሓት ሽፍታ ቡድን ላይ እርምጃ ከመወሰዱም በላይ፤ ማሠልጠኛዎችም መውደማቸውን አስታውቀዋል።

እንደ ጄኔራል ባጫ የዛሬው መግለጫ፤ ጥቂት የሕወሓት ቡድን አባላት እና አመራሮች ተስፋ በመቁረጥ ከኢትዮጵያ ለመውጣት ሙከራ አድርገው ነበር። ነገር ግን በመከላከያ ሠራዊት አባላት በቁጥጥር ሥር ሊውሉ መቻላቸውንም በዚሁ መግለጫቸው ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊት በተለያዩ ቦታዎች ተበትኖ የነበረውን የቡድኑን ታጣቂዎች በማዳን እርምጃ የወሰደባቸው አካባቢዎች ስምንት መኾናቸውን ጠቁመዋል። እነርሱም በምሥራቅ ትግራይ በአጽቢ፣ በሐይቅ መሳል፣ በዴስኦ፤ በደቡብ ራያ ግንባር ላይ በዋጅራት እና በቦራ፤ በሰሜን ምሥራቅ መቀሌ በጽጌረዳ፣ በሐውዜ፣ ውቅሮ ማርያምና ዛና መኾናቸውን ጠቅሰዋል።

በእነዚህ በስም በተጠቀሱት ስምንት አካባቢዎች ትናንሽ ማሠልጠኛዎች የነበሩባቸውና የጁንታው መሪዎች ራሳቸውን ጠባቂ ወታደሮች እንደነበራቸው የገለጹት ጄኔራሉ፤ ሰፋ ያለ ዘመቻ ተካሒዶባቸው አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሠራዊቱ፣ ጠባቂዎቻቸው እና ማሠልጠኛዎቹ መደምሰሳቸውን አስረድተዋል።

ከአገር ሊወጡ ሲሉ ተይዙ የተባሉት አባላት እና አመራሮች በዚህ መግለጫ ላይ በስም አልተጠቀሱም። እነዚህን ሰዎች ለመያዝ ከበው የሚጠብቃቸውን ኃይል በማጥቃት መደምሰስ መቻሉንም ገልጸዋል።

ይህ በመከላከያ ሠራዊቱ የተወሰደው እርምጃም በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን በመጠቀም የታገዘ ሲሆን፤ ከአሁን በኋላ የሕወሓት ሽፍታ ቡድን ሠራዊት አደራጅቶ ለመዋጋት በማይቀጥልበት ደረጃ ስለመመታቱም አክለው ገልጸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ