ከኃላፊነታቸው በተነሱት የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አዲስ ኮሚሽነር ተሾሙ
አዲሱ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ (በግራ) እና የቀድሞው የክልሉ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ
አዲሱ ተሿሚ የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር የነበሩት ተኮላ አይፎክሩ ናቸው
ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 28, 2021)፦ በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ዘር ተኮር ጥቃት ይብቃ በሚል ከተደረጉት የተቃውሞ ሰልፎች ማግስት ለግምገማ የተቀመጠው የክልሉ ምክር ቤት እና የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች፤ የክልሉን የፖሊስ ኮሚሽነር ከኃላፊነት እንዲነሱ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ አዲስ ኮሚሽነር ተሹሟል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩት ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ከተደረገ በኋላ፤ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኾነው እንዲሠሩ ተሰይመዋል ተብሏል።
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከኃላፊነታቸው መነሳት ከሰሞኑ ሲነገር የነበረ ሲሆን፤ ከክልሉ መንግሥት ግን እስካሁን ይፋዊ ማረጋገጫም ኾነ ለምን እንደተነሱ የተሰጠ ማብራሪያ የለም።
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ግን፤ የሰሞኑን የአማራ ክልል ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ባደረጉት ግምገማ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ውሳኔ እንዲተላለፍ ኾኗል የሚል ነው።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር በመኾን መሰየማቸውና በትናንትናው ዕለት ሥራ መጀመራቸው የተነገረላቸው ተኮላ አይፎክሩ፤ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ በአማራ ክልል በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው።
በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኾነው ማገልገላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በወሎ የኮምቦልቻ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኾነው መሥራታቸውም የሚጠቀስ ነው። ከዚህም ሌላ የክልሉ የማረሚያ ቤቶች ዋና ኮሚሽነር ኾነውም ሠርተዋል። በአማራ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች እና ከተሞች ፖሊስ መምሪያዎችንም በመምሪያ ኃላፊነት አገልግለዋል። (ኢዛ)



