ፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ

አዋጅ ቁጥር ፩ሺ፩፻፸፮/፪ሺ፲፪፤ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ

ይህ የ48 ሰዓታት ማስታወቂያ የወጣው ለመጀመሪያ ጊዜ መኾኑ ነው

ኢዛ (ሰኞ ሚያዝያ ፳፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 3, 2021)፦ ሕወሓት እና ኦነግ ሸኔ በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተቃውሞ ያላቸው በ48 ሰዓት ውስጥ ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ። ይህ የ48 ሰዓታት ማስታወቂያ የወጣው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

መጋቢት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በተሻሻለው የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ (ፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ) ቁጥር 1176/2012 መሠረት፤ አንድን ድርጅት በአሸባሪነት ለመሰየም የሚቻለው፤ ሀ) ድርጅቱ የሽብር ወንጀልን ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀስ እንደኾነ፤ ወይም ለ) የድርጅቱ የሥራ አመራር ወይም ውሳኔ ሰጭ አካል ወንጀሉን በአሠራርም ኾነ በግልጽ የተቀበለው ወይም አፈጻጸሙን የመራ እንደኾነ፤ ወይም ሐ) በአሠራር ወይም በአፈጻጸም ወንጀሉ የድርጅቱ መገለጫ ሲሆን፤ ወይም አብዛኛው የድርጅቱ ሠራተኛ ወንጀሉን በሚያውቁት አኳኋን የሚንቀሳቀስ እንደኾነ ድርጅቱን ሽብርተኛ ብሎ ለማስየመ እንደሚቻል በዋጁ አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ተደንግጓል።

በዚሁ በተሻሻለው ሕግ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 1 አንድ ላይ ደግሞ፤ “የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አንድ ድርጅት በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፲፱ / 19 ንዑስ አንቀጽ (፩) / (1) ከተጠቀሱት ሁኔታዎች አንዱን በሚያሟላ ሁኔታ የሽብር ወንጀል መፈጸሙን ወይም እየፈጸመ ስለመኾኑ ሲያምን፤ ድርጅቱ በአሸባሪነት እንዲሰየም የውሳኔ ሐሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀርባል።” ይላል።

በዚሁ በአንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ደግሞ፤ “የሚኒስትሮች ምክር ቤት በፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ሲያጸድቀው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል።” ሲል ይደነግጋል።

ጥሪ ስለማድረግ እና ውሳኔ ማስተላለፍ በሚለው አንቀጽ 21 ሥር በንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ፤ “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድርጅትን በአሸባሪነት እንዲሰየም የውሳኔ ሐሳብ ሲቀርብለት፤ ድርጅቱ አስተያየቱን የሚያቀርብበትን በቂ ጊዜ በመስጠት እና የጊዜ ገደብ በመግለጽ አግባብ ባለው መገናኛ ዘዴ ጥሪ ማስተላለፍ አለበት።” ሲል ሕጉ ይደነግጋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ይህንኑ የሕግ አካሔድ ተከትሎ ነው ዛሬ ያስተላለፈውን ጥሪ ለመገኛና ብዙኀን እና በራሱ የማኅበራዊ ገጾች ያስተላለፈ። ለዚህ ጥሪ ሕወሓትም ኾነ ኦነግ ሸኔ “ሽብርተኛ አይደለንም” በሚል አደባባይ ወጥተው ምላሽና መከራከሪያ ያቀርባሉ ተብሎ ባይታመንም፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥሪውን አስተላልፏል። ምክር ቤቱ ዛሬ ያስተላለፈው ጥሪ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተላለፈ ማስታወቂያ

የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 2ዐ ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዝያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሔደው 23ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ሕዝበ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና “ሸኔ” ድርጅቶች በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሐሳብ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አቅርቧል።

በዚህ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአዋጁ አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ 1 በተደነገገው መሠረት፤ ሁለቱ ድርጅቶች የውሳኔ ሐሳቡን ለመቃወም የሚያስችል ማንኛውም ማስረጃ ካላቸው ይህ ማስታወቂያ በመገናኛ ብዙኀን ከተነገረበት ሰዓት ጀምሮ ባሉት 48 ሰዓታት ውስጥ በም/ቤቱ ጽ/ቤት በአካል በመገኘት እንድታቀርቡ ጥሪ እናስተላልፋለን።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!