የመድረክ አመራር አንዷለም አራጌና ሌሎች 3 አባላትም በማዕከላዊ ናቸው

Serkalem Fasi and Eskinder Nega with their sonEthiopia Zare (ረቡዕ መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም. September 14, 2011)፦ በደፋርነቱና ለሀገሪቱ መጻኢ ዕድል ያለውን ዕይታ ነጻ የሆኑ ሃሳቦቹን በመግለጽ የሚታወቀው እስክንድር ነጋ እና የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዷለም አራጌ ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት በደህንነቶች ታፍነው መወሰዳቸው ተገለጸ። 

 

በአንድነት ጽሕፈት ቤት አካባቢ በሚገኝ ካፊቴርያ የነበሩ ሌሎች አቶ ዘመነ ሞላ፣ አሳምነው ብርሃኑ እና ናትናኤል መኮንን የተባሉ የፓርቲው አባላትም በመጥፎነቱ ወደሚታወቀው ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት ተጥለዋል።

 

ባሳለፍነው ወራቶች በርካታ ጋዜጠኞችና በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅት አባላት በመታፈስ ላይ እንደሆኑ ይታወቃል።

 

አዲስ በወጣው የሽብርተኝነት ሕግ ሰበብ ምክንያት ብቻ ሁለት የስዊድን ዜግነት ያላቸው ጋዜጠኞችን ጨምሮ የፍትህ ጋዜጣ አምደኛ ርዕዮት አለሙ፣ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ ውብሸት ታዬ እና የአንድነት ፓርቲው አርቲስት ደበበ እሸቱ የተከሰሱ ሲሆን፤ እስክንድር ነጋ ዛሬ በዚሁ ክስ ወደ ማዕከላዊ መግባቱ ታውቋል። ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አካላትና አባላት ደግሞ የኦብኮ አመራር አባላት አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ኦልባና ሌሊሳ የተባሉና ሌሎች በርካታ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ አባላትና የኦሮሞ ተወዳጅ ዜጎችን ጨምሮ ዛሬ የታሰሩት አቶ አንዷለም አራጌና ሦስቱ የድርጅቱ አባላት እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል።

 

እስክንድር ነጋና ሌሎች አራት በዛሬው ዕለት ማዕከላዊ እስር ቤት የገቡ እስረኞች ሀገርን ለማሸበርና ሠላም ለማደፍረስ ሲሰሩ ተገኝተዋል በሚል በሽብርተኝነት ክስ እንደሚፈለጉ ፖሊስ አስታውቋል።

 

እስክንድር ነጋ እና ባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል በ1997 ዓ.ም. በተፈጠረው የምርጫ ውዝግብ ታስረው እንደነበርና ሳተናው፣ ወንጭፍ እና ምኒልክ የተሰኙ በህትመትና በአንባብያን ብዛት የሚታወቁት ጋዜጦች አሳታሚ ድርጅታቸው የተዘጋባቸው መሆኑ ይታወቃል።

 

ወ/ሮ ሰርካለም እስር ቤት በነበረች ሰዓት ወንድ ልጇን ናፍቆት እስክንድርን በእስር ቤት በመውለዷና ያለፍትህ በመሰቃየቷ በርካታ ዓለምአቀፍ ሽልማቶችን እንዳገኘች ይታወሳል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!