በሽብርተኛ ክስ ውብሸት ጥላሁን፣ ርዮት አለሙ እና ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞች ክስ ተመስርቶባቸዋል

Ethiopia Zare (አርብ ጳጉሜን 4 ቀን 2003 ዓ.ም. September 9, 2011)፦ ታዋቂው የጥበብ ባለሙያና የቅንጅት ለአንድነትና ዲሞክራሲ አመራር አባል እንደነበር የሚታወቀው አርቲስት ደበበ እሸቱ በኢህአዴግ መንግስት “ሽብርተኛ” ተብሎ ከተፈረጀው ግንቦት 7 ንቅናቄ ጋር ግንኙነት አድርጓል በሚል ማእከላዊ እስር ቤት መግባቱ ተገለጸ።

 

አርቲስት ደበበ በሀገር ክህደት ከተወነጀሉትና በ1997 ዓ.ም ምርጫ ዋና ተቃዋሚ የነበረው ቅንጅት ለአንድነትና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን ይሰራ እንደነበርና በ’ምህረት’ ተለቀቁ ከተባሉት የአመራር አባላት አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

 

አርቲስት ደበበ በወይዘሪት ብርቱካን ይመራ የነበረው አንድነት ፓርቲ ምስረታ ላይ ከፍተኛ ሚና ይጫወት እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን የፓርቲው መሪ ወ/ት ብርቱካን በታሰረች ወቅት በፓርቲው አመራር አባላት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ዝም አንልም በማለት ይንቀሳቀስ ከነበረው አካል ጋር ይሰራ እንደነበር ይታወቃል።

 

በአቶ ደበበ እሸቱ ላይ በ48 ሰአት ውስጥ ክስ እንመሰርታለን ያሉት የኮሙኒኬሽን ጉዳይ ባለስልጣኑ አቶ ሽመልስ ከማል አርቲስት ደበበን የ’ሽብርተኛ ድርጅት’ ካሉት ግንቦት 7 ንቅናቄ ጋር ግንኙነት እንደነበረው ደርሰናበታል ከማለት ውጭ ማብራሪያ አለመስጠታቸው ተመልክታል።

 

በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅት አመራር አካላት በተለይ በአሁኑ ጊዜ አዲሱን የሽብርተኝነት ህግ ከለላ በማድረግ በተቃዋሚዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ወከባ፣ እንግልትና እስር በእጅጉ እያሳሰባቸው መሆኑንና ተቃዋሚዎች በመሸማቀቅ ላይ መሆናቸውን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ድምጻቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

 

በተያያዘ ዜና በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በዚሁ የሽብርተኝነት ክስ የተመሰረተባቸው የአውራምባ ታይምስ ምክትል አዘጋጅ ውብሸት ታየ እና የፍትህ ጋዜጣ አምደኛ ርዮት አለሙን ጨምሮ ሁለት ስዊድናዊ ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት መቅረባቸው ታውቋል።

 

በተለይ በምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ጋር በተደረገ ውጊያ ተማርከዋል የተባሉት ፎቶግራፍ አንሺው ጀሃን ፐርሰንና ማርቲን የተባለ ሪፖርተር ሲሆኑ የሲውድን መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት እሰረኞቹን በተመለከተ ምንም አይነት ማብራሪያ እንዳላገኘና በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።የሽብርተኝነት ክሱ በአሜሪካን ሀገር መሰረት ያደረገውን የኢትዮጵያን ሪቪው ድረ ገጽ ባለቤት አቶ ኤልያስ ክፍሌን የሚያካትት ሲሆን በተለያዩ የተቃዋሚ መሪዎችና ጋዜጠኞች ላይ ማነጣጠሩ እንዳሳሰባቸው በርካታ አለም አቀፍ የሰበአዊ መብትና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች መግለጫዎችን በማውጣት ላይ ይገኛሉ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ