የኮሚሽነር አበረ አዳሙ የሕይወት ታሪክ
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በጣም ቆፍጣና ወታደር፣ ምሁር፣ ደራሲ፣ ገጣሚ እና የሕግ ባለሙያ ሲኾኑ፤ ከሦስት በላይ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው መናገርና መጻፍ የሚችሉ፣ በሁሉም ዘርፍ በሚባል ደረጃ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነበሩ
አማራ ሚድያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) - ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከአባታቸው ከአቶ አዳሙ መኮንን እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ጦቢያ ንጋቱ የካቲት 13 ቀን 1961 ዓ.ም. በቀድሞው የጎጃም ክፍለ አገር ቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ ደጋዳሞት ወረዳ መለስ ብሳና ሜዳ ቀበሌ ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምህርት እስኪደርስ በቤተሰቦቻቸው እንክብካቤ አድገው በ1973 ዓ.ም ወይን ውኃ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው እስከ 8ኛ ክፍል ተማሩ። ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ባላቸው ትምህርትን የመቀበል ተፈጥሯዊ ተሰጥዖ በአራት ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ አገር አቀፉን የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ 9ኛ ክፍል ተዛውረዋል።
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ሕወሓት በእብሪት የአማራ ክልልን በወረረችበትና ኢትዮጵያን በእናት ጡት ነካሽነት በወጋችበት ጊዜ ቁርጠኛ አመራር የሰጡና የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በሕግ ማስከበሩ ሒደት በአገር አቀፍ ደረጃ ያስመዘገበውን ዘመን ተሻጋሪ ገድል እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ተጠቅመው በመምራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ነበሩ
ኮሚሽነር አበረ ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ቅርብ የኾነ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ከትውልድ አካባቢያቸው ርቀው መሔድ ስለነበረባቸው፤ አጎታቸው ይኖሩበት ወደ ነበረበት አምቦ ከተማ በመሔድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በላቀ ውጤት በመጨረስ አጠናቀዋል። የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ኮሌጅ የሚያስገባ ነጥብ ያመጡ በመኾናቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ባወጣው የመኮንንነት ፈተና ተሳትፈው በማለፋቸው፤ በፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሚሰጠውን የመኮንንነት ትምህርት አጠናቀው በምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ በዲፕሎማ በ1986 ዓ.ም. ተመርቀዋል።
ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከተመረቁ በኋላ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዞን 2 ወረዳ 21 ቂርቆስ ፖሊስ ጣቢያ ተመድበው በወንጀል መከላከል፣ ወንጀል ምርመራና በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ለአምስት ዓመታት ያህል ሠርተዋል። በኃላፊነት በነበሩበትም ወቅት ወንጀልን በመከላከል፣ ሕዝብን በማገልገል ተደጋጋሚ ሽልማቶችን ተቀብለዋል።
በወቅቱ በነበረው ሥርዓት የመሪዎች መመሪያን አይቀበልም በሚል ሰበብ ከሦስት ጊዜ በላይ ለእስር ተዳርገው ነበር። ኮሚሽነር አበረ ጥቃትን የሚቀበል ሰብእና የሌላቸው በመኾኑ፤ ይህንን በደል በመጠየፍ በቀድሞው የደኅንነት ኃላፊዎች ከታሰሩበት ቦታ የተደገሰላቸውን ሞት በማምለጥ ከአገራቸው ለመሰደድ ተገደዋል። ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከአያቶቻቸው በወረሱት ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ሕወሓት መራሹን መንግሥት በኃይል ለመጣል ወደ ኤርትራ በረሀ በመውረድ “የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር” የሚባል ድርጅት ከትግል ጓደኞቻቸው ጋር በመመሥረት የወታደራዊ ክንፍ አዛዥ በመኾን ሲታገሉ ቆይተዋል።
ከዚያም ትግሉን ለማስፋትና ሕወሓት መራሹን መንግሥት ከሥልጣን በፍጥነት ለማውረድ ከኤርትራ በተጨማሪ በደቡብ ሱዳን፣ በኬንያ እና በዩጋንዳ ትግሉን ሲመሩ ቆይተዋል።
በኋላም ራሳችውን ከቀጥታ የትግል ተሳትፎ ለተወሰነ ጊዜ በማግለል በኬንያ ሊሙሩ ከተማ በሚገኘው የአሜሪካን ዩኒቨርስቲ የነፃ ትምህርት እድል በማግኘታቸው በሊደርሽፕ ማኔጅመንት ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፤ የአራት ዓመቱን ትምህርት በ2 ዓመት ብቻ በላቀ ውጤት አጠናቀዋል።
ከዚያም በመቀጠል በዓለም አቀፍ ስደተኞችና ሰብአዊነት ረጅ ተቋማት አማካኝነት ወደ ስዊድን አገር በማቅናት በስደተኝነት ይኖሩ ነበር። ከዚያም “ግንቦት ሰባት የነፃነትና የእኩልነት ንቅናቄ”ን ከመሥራች አባልነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ አመራርነት በመምራት ታግለው አታግለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በስዊድን አገር የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ፕሬዝዳንት በመኾን ሕዝባቸውን አገልግለዋል።
በስዊድን ቆይታችውም ከታዋቂው የሉንድ ዩኒቨርስቲ (Lunds University) ሕግና የማኅበረሰብ ሣይንስ ጥናት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (MSc in Sociology of Law) በከፍተኛ ውጤት ያገኙ ሲሆን፤ የመመረቂያ የምርምር ጽሑፋቸው በዩኒቨርስቲው ተመርጦ በመታተም ለገበያ ቀርቦላቸዋል።
መጽሐፋቸውም የበይነ-መረብ መገበያያ በኾነው በአማዞን በሽያጭ ላይ ይገኛል። ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከሌላኛው በስዊድን አገር አንጋፋና ታዋቂ ከኾነው ማልመ ዩኒቨርስቲ (Malmö University) ሌላኛውን ሁለተኛ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ስደተኞችና የማኅበረሰብ ግንኙነት (MA in Intomational Migration and Ethnic Relations) በከፍተኛ ማዕረግ አግኝተዋል።
ኮሚሽነር አበረ በስዊድን አገር እያሉ ተጨማሪ የመጀመሪያ ዲግሪ በሕግና በፖሊስ ሣይንስ (BA in Legal and Police Science) ከሌላኛው የስዊድን ታዋቂ ከኾነው ሊኔዮስ ዩኒቨርሲቲ (Linnaeus University) አግኝተዋል።
ከእነዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህታቸውን ጨርሰው፤ ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ አግኝተው፤ ልጆች ወልደው፤ ከትግሉ ጎን ለጎን የግል ኑሯቸውን ማጣጣም በጀመሩበት ወቅት በኢትዮጵያ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ በተደረገላቸው ጥሪ ሕዝባቸውን ለማገልገል ወደ አገራቸው ሊገቡ ችለዋል።
በአገር ደረጃ የመጣውን ለውጥ በመቀላቀል በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን ታሪክ የመጀመሪያው በፖሊስ ሣይንስ የተመረቀ ፖሊስ ኮሚሽነር በመኾን ከየካቲት 2011 ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ 2013 ዓ.ም. ድረስ በቅንነትና በታማኝነት አገልግለዋል። ኮሚሽነር አበረ አገራቸውን አንስተው የማይጠግቡ፤ ለሕዝባቸው ልዩ ፍቅር ያላቸው፤ ሁሉም ነገር ከአገር እና ከሕዝብ በታች ነው ብለው የሚያምኑ፤ በሕይወት እስከተለዩበት ጊዜ ድረስ አገራቸውን እና ሕዝባቸውን እንዳስቀደሙ የኖሩ እውነተኛና ሐቀኛ አርበኛ ናቸው።
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በጣም ቆፍጣና ወታደር፣ ምሁር፣ ደራሲ፣ ገጣሚ እና የሕግ ባለሙያ ሲኾኑ፤ ከሦስት በላይ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው መናገርና መጻፍ የሚችሉ፣ በሁሉም ዘርፍ በሚባል ደረጃ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነበሩ።
ኮሚሽነር አበረ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለተደረገው ሪፎርም ጥናት በማድረግና በመምራት የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድጋቸውም በላይ፤ ሪፎርሙን በቁርጠኝነት በመምራት አመርቂ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አድርገዋል።
በኮሚሽነር አበረ መሪነት ከተመዘገቡ የሪፎርሙ ውጤቶች መካከል ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያህል፡-
• ከለውጡ በፊት የነበሩ የአሠራር ችግሮችን በማስቀረት በኮሚሽኑ ውስጥ የሥራ ምደባ በበቂ ችሎታና ክህሎት ላይ የተመሠረተ ብቻ እንዲኾን በመደረጉ በሠራዊቱ ውስጥ ከፍተኛ የኾነ በራስ መተማመን እንዲፈጠር አድርገዋል፤ በዚህም በርካታ ተተኪ ወጣት ወንድና ሴት መኮንኖች ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ አድርገዋል።
• የፖሊስ ሪፎርም በተለያዩ ችግሮች እንዲቆም ተደርጎ የነበረውን ችግሩን በመፍታት ሪፎርመን ወደ ኋላ ከመመለስ አደጋ በመታደግ ሪፎርሙ ተግባራዊ በመደረጉ ለሌሎች ክልሎችና ለፌደራል ፖሊስ በተሞክሮነት እየተወሰደ ያለ ነው።
• የክልሉ ፖሊስ አባላትን ልዩ ልዩ የጥቅማጥቅም መመሪያ እንዲዘጋጅ እና ሥራ ላይ እንዲውል አድርገዋል።
• በኮሚሽኑ በተለያዩ መዋቅር የተደራጁ የሥራ ክፍሎችን በአንድ ዘርፍ ሥር በማደራጀት የወንጀል መከላከል አቅማቸው እንዲያድግና በተለይም የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ከክልል አልፎ አገራዊ የሕግ ማስከበር ሥራ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የኃላፊነት ሚናቸውን ተጫውተዋል።
• የክልሉ ፖሊስ ልዩ ልዩ መመሪያዎች ለበርካታ ዓመታት ሳይፀድቁ የቆዩቱን እንዲፀድቁ በመደረጉ በአባላት ውስጥ ይታይ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታ ሠርተዋል።
• ሪፎርሙ የሴቶችን ተሳትፎ በእጅጉ ያሳደገ መኾኑ እና ሌሎችም በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል።
ኮሚሽነር አበረ ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን ከብዙ ንባብ እና ልምድ ያገኙትን እውቀት በመቀመር “የሕግ የበላይነት ለአገራዊ ልማት” በሚል ርዕስ መጽሐፍ በመጻፍ የሕግ የበላይነት ለአገር ዘላቂ ልማትና ሰላም ያላቸውን አስተዋጽኦ በማሳየት ለትውልድ አበርክተዋል።
በአጠቃላይ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ባላቸው ጥልቅ የአገርና የሕዝብ ፍቅር የተነሳ የራሳቸውን ቤተሰብ መሥዋዕት በማድረግ ከተመቻቸ የውጭ አገር ኑሮ፤ ሕዝቤን አገለግላለሁ በሚል ከለውጡ ዋዜማ ጀምረው በወኔና በፍጹም የአገር ፍቅር ስሜት ወደ አገር ቤት መጥተው በአልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ኾነው የአማራ ብሔራዊ ክልልን ከጸጥታ ቀውስ የታደጉ፤ በሠራዊቱ አመራሮችና አባላት ዘንድ ተቀባይነት የነበራቸው፤ አስተዋይ፣ ቅንና ተግባቢ እንዲሁም ሙያዊ ብቃትና ክህሎት የነበራቸው፤ ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ-ምግባር የተላበሱ ባለምጡቅ አዕምሮ ባለቤት ነበሩ።
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ የልዩ ኃይሉን፣ የመደበኛ ሠራዊቱንና በተቋሙ ሥር ያሉትን ሠራተኞች የሚመዝኗቸው በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በእውቀታቸው፣ በሥነ- ምግባራቸውና በሥራ ብቃታቸው እንጂ ሌሎች መመዘኛዎችን አምርረው የሚጠሉ ብቻ ሳይኾን አድሏዊ አሠራርንና ኢ-ፍትሐዊነትን በመቃወም ነፍጥ አንስተው በረሃ የወረዱና በሚችሉት ሁሉ የታገሉ ጀግና መሪ ነበሩ።
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ሕወሓት በእብሪት የአማራ ክልልን በወረረችበትና ኢትዮጵያን በእናት ጡት ነካሽነት በወጋችበት ጊዜ ቁርጠኛ አመራር የሰጡና የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በሕግ ማስከበሩ ሒደት በአገር አቀፍ ደረጃ ያስመዘገበውን ዘመን ተሻጋሪ ገድል እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ተጠቅመው በመምራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ነበሩ። ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች አባት እንዲሁም የበርካቶች ወንድም የነበሩ ሲሆን፤ ሚያዝያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ድንገት ባጋጠማቸው ሕመም ሆስፒታል ገብተው በሕክምና እየተረዱ እያሉ በተወለዱ በ52 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፏል።
የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖችና አባላት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ዛሬ (ሐሙስ ሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም.) ተፈጽሟል።



