በመስቀል አደባባይ የአፍጢር መርኀ ግብር ተካሔደ

በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ የአፍጢር መርኀ ግብር
በግብጽ ተይዞ የነበረው የጎዳና ላይ አፍጢር ክብረ ወሰን ዛሬ በኢትዮጵያ ተሰበረ
ኢዛ (ማክሰኞ ግንቦት ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 11, 2021)፦ በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ የአፍጢር መርኀ ግብር በርካታ ሕዝብ በተገኘበት ተካሔደ። ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር በመርኀ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ከዚህ ቀደም ተደርጎ የማያውቅ መኾኑን በመጥቀስ፤ አስደሳች ዝግጅት እንደኾነ ገልጸዋል። የመርኀ ግብሩ አዘጋጆች ለኾኑት ለአዲስ አበባ መስተዳድር እና ለጸጥታ ኃይሎችም ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል።
በግብጽ ተይዞ የነበረውን እና 7 ሺህ ሰዎች የተካፈሉበትን የጎዳና ላይ አፍጢር ክብረ ወሰን ለመስበር ታቅዶ የነበረው ዓላማ ተሳክቷል ተብሏል። በዛሬው ዕለት (ማክሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም.) በመስቀል አደባባይ የተደረገው የጎዳና ላይ አፍጢር የግብጹን ክብረወሰን ለመስበር እንዳስቻለ ተገልጿል።
ባለፈው እሁድ ግንቦት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በጸጥታ ችግር ምክንያት መሰረዙን አስመልክቶ፤ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመንግሥት ወጪ ለዛሬ አስተላልፈውት እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም።
በነገው ዕለት ሊውል ይችላል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የዘንድሮው የረመዳን በዓል ዛሬ ማምሻውን ጨረቃ ባለመታየትዋ ምክንያት፤ ከነገ ወዲያ ሐሙስ ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚውል ታውቋል። የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ኢድ ሙባረክ! ይላል። (ኢዛ)