በብልጽግና የድጋፍ ሰልፍ ላይ በተፈጠረ ግጭት ሕይወት ጠፋ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና ብልጽግና ፓርቲ
መንግሥት ለጥቃቱ ትእዛዝ የሰጡና የፈጸሙ አካላት ላይ አስቸኳይ ምርመራ በማድረግ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድና ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ አብን ጠይቋል
ኢዛ (ዓርብ ግንቦት ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 21, 2021)፦ በአማራ ክልላዊ መንግሥት በምዕራብ ጎጃም ዞን መርአዊ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ በጠራው የድጋፍና የምርጫ ቅስቀሳ ሰልፍ ላይ በተፈጠረ ግጭት ሁለት ተማሪዎች ሲሞቱ 12 የሚኾኑ መቁሰላቸው ተሰማ።
የብልጽግና ደጋፊዎችን በመቃወም ወደ ሰልፍ የገቡ ወጣቶች እና የብልጽግና ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ነው የተባለ ሲሆን፤ ግድያው የተፈጸመው ደግሞ በጸጥታ ኃይሎች መኾኑም እየተነገረ ነው። የሟቾችን ቁጥር አራት እንደኾነ የሚገልጹ ወገኖችም አሉ።
በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥበትም፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቂ (አብን) መንግሥት ለጥቃቱ ትእዛዝ የሰጡና የፈጸሙ አካላት ላይ አስቸኳይ ምርመራ በማድረግ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድና ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ መግለጫ በማውጣት ጠይቋል። አብን ጉዳዩን በማስመልከት የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል። (ኢዛ)
ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ
በምዕራብ ጎጃም ዞን በመራዊ ከተማ ትላንት ግንቦት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ድምፃቸውን በሰላማዊ መንገድ ባሰሙ ተማሪዎች ላይ የጸጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት ደርሷል።
አብን በተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በጥብቅ እያወገዘ፤ መንግሥት ለጥቃቱ ትእዛዝ የሰጡና የፈጸሙ አካላት ላይ አስቸኳይ ምርመራ በማድረግ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደረግ እንጠይቃለን።
በተለይ አሁን ባለንበት የምርጫ ወቅት ከገዥው ፖርቲ የተለየ ሐሳብ በሚያራምዱና ለብልጽግና ፖርቲ ድጋፍ ለማድረግ በማይፈልጉ ወገኖቻችን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የሕዝባችንን እና የአገራችንን ሰላም የሚያናጉ በመኾናቸው መሰል ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ሊቆጠብ እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን።
ገዥው የብልጽግና መንግሥት ሕዝቡ የሚሰጠውን ፖለቲካዊ ድጋፍ ብቻ ሳይኾን ተቃውሞንም በአግባቡ ለማዳመጥ መዘጋጀት እና በርካታ ችግሮች ባሉበት ሕዝብ ላይ ተጨማሪ ተግዳሮቶችን ለመፍጠር መሞከር ኃላፊነት የጎደለውና አዋጭነት የሌለው መኾኑን መቀበል ይገባል።
አብን የተፈጠረውን ጥቃት በቅርበት እያጣራ ሲሆን፤ የጥቃቱ ፈጻሚዎችን ለሕግ ለማቅረብ በሚደረግ እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መኾኑን ማረጋገጥ ይወዳል።
አብን በጥቃቱ ሕይወታቸውን ባጡ ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅ ኀዘን እየገለጸ፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል። በደረሰባቸው ጥቃት ተጎድተው በሕክምና ክትትል ላይ የሚገኙ ወገኖቻችን በፍጥነት እንዲያገግሙም መልካም ምኞቱን ይገልጻል።



