Ethiopian Parliament Building

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕንጻ

ለመከላከያ ስድስት ቢሊዮን ብር ለ2013 ተጨማሪ በጀት ተመድቦ ነበር
የ2014 የአገሪቱ በጀት ከአምናው 59.3 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው

ኢዛ (ማክሰኞ ሰኔ ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 15, 2021)፦ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት የ2014 በጀት ዓመት የአገሪቱ በጀት ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ እንዲኾን ውሳኔ ያሳለፈበትን ረቂቅ በጀት ላይ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ይወያይበታል። በጀቱንም ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2014 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 561.7 ቢሊዮን ብር እንዲኾን የወሰነው ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ በዚሁ ውሳኔ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወያይቶ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

በዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ የገንዘብ ሚኒስትሩ በ2014 በጀት ዝግጅት ላይ ማብራሪያ የሚሰጡ መኾኑም ታውቋል።

የ2014 ረቂቅ በጀት አገሪቱ ከፍተኛ በጀት የበጀተችበት እና ለመጀመሪያ ጊዜ ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ የተሻገረበት ነው።

የ2014 ረቂቅ በጀት ከ2013 አንጻር ሲታይም ከ85.7 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ነው። በ2013 በጀት ዓመት ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ተወስኖ የነበረው 476 ቢሊዮን ብር ነበር። ነገር ግን ባለፈው ሳምንት ለ2013 ተጨማሪ 26.4 ቢሊዮን ብር በጀት እንዲጸድቅ በመደረጉ የ2013 በጀት ዓመት በጀትን ወደ 502.4 ከፍ ስለሚያደርገው፤ የ2014 በጀት ከአምናው አንጻር ያለው ብልጫ 59.3 ቢሊዮን ብር መኾኑን ያመላክታል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2013 በጀት ዓመት 26.4 ቢሊዮን ብር ውስጥ ለእርዳታ 9.3 ቢሊዮን የሚውል ነው።

ስድስት ቢሊዮን ብር ደግሞ ለመከላከያ ኃይል የተመደበ ተጨማሪ በጀት ነው። ከዚህም ሌላ ለመጠባበቂያ 6.3 ቢሊዮን ብር፣ ለኮቪድ 19 መከላከያ ሁለት ቢሊዮን ብር፣ ለማዳበሪያ ድጐማ ሁለት ቢሊዮን ብር በጀት የተመደበበት ነው።

ቀሪው ደግሞ ለጐርፍ መከላከል 600 ሚሊዮን ብር፣ ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ 500 ሚሊዮን ብር፤ እንዲሁም ለከተማ የምግብ ዋስትና ሴፍትኔት ፕሮግራም 230 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት እንዲጸድቅ ተደርጓል።

ዛሬ በ2014 ረቂቅ በጀት መሠረት ከ561.7 ቢሊዮን ብር ውስጥ ለፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪዎች 162 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለታል። ለካፒታል ወጪዎች በረቂቅ በጀቱ ላይ የተያዘው 183.5 ቢሊዮን ብር ነው። ለክልሎች ድጋፍ ተብሎ የቀረበው በጀት ደግሞ 203.9 ቢሊዮን ብር ነው።

ከእነዚህ ሌላ በ2014 ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 12 ቢሊዮን ብር በጀት ስለመያዙ በዚሁ ረቂቅ ላይ ተመልክቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ