በትግራይ ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ይፈጠራል ተብሎ ተሰግቷል

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ
የሕወሓት የሽብር ቡድን በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ገብቶ ግድያዎች እየፈጸመ ነው
ኢዛ (እሁድ ሰኔ ፳፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 4, 2021)፦ በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል (የአንድ ወገን) የተኩስ አቁም እወጃ ካደረገ በኋላ ወደ መቀሌ እና ሌሎች የክልሉ ከተሞች በመግባት በነዋሪዎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ መኾኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ እንዳስታወቀው፤ ቡድኑ የተለያዩ ከተሞች በመግባት በነዋሪዎች ላይ ግድያ እየፈጸመ ያለው የአገር መከላከያ ሠራዊትን እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ተባብራችኋል በሚል ነው።
ይህ በንጹኀን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያ በክልሉ ያለውን የሰብአዊ አቅራቦቶች ችግሮችን የሚያባብስና በክልሉ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እንዲፈጠር የሚያደርግ ስለመኾኑም ገልጿል።
ዛሬ እሁድ ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማጣሪያ ባወጣው መግለጫ፤ “የሽብር ቡድኑ መንግሥት ያደረገውን ዐይነት የተኩስ አቁም ከማድረግ ይልቅ፤ የኢትዮጵያን እና የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በሐሰተኛ የድል ፕሮፓጋንዳዎቹ ለማታለል እና ትኩረት ለማግኘት በሚያደርገው መፍጨርጨር የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪዎችና የዜጎች ደኅንነት በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ እያስገባ እንደኾነ ኢትዮጵያውያን እና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሊረዳ ይገባል” በማለት ያለውን ሁኔታ አስታውቋል። (ኢዛ)