የአብን መግለጫ፤ የትሕነግ ማንሰራራት የደኅንነታችን አደጋ ነው
የአገርን ደኅንነት ለመጠበቅና የሚፈለግበትን ለማድረግ ቁርጠኛ መኾኑንም ገልጿል
ኢዛ (ሰኞ ሰኔ ፳፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 5, 2021)፦ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአገራችን ላይ የተደቀነውን ጽኑ የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ለመመክትና ከምንም በላይ የሕዝብ ጥቅምና ክብር፤ እንዲሁም የአገረ መንግሥቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ድርጅታዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ ቁርጠኛ ነኝ አለ። የትሕነግ ማንሰራራት የደኅንነት ሥጋት መኾኑንም ገልጿል።
አብን ይህንን ያለው ሰኔ 26 እና 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ያካሔደውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከተሰበሰበ በኋላ ዛሬ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው።
ሥራ አስፈጻሚው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ አቋም ላይ የደረሰባቸውን ጉዳዮች በዚሁ መግለጫው ላይ ያመለከተ ሲሆን፤ በተለይ በወቅታዊ የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋና እጅግ አሳሳቢ እየኾነ መምጣቱን እንደሚገነዘብ አስታውቋል።
የብልጽግና አገዛዝ የአገሪቱን፣ የዜጎችና የመንግሥቱን ሰላምና ደኅንነት፣ ጥቅምና ክብር በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ ክፍተቶች እየተስተዋለበት መኾኑን በመግለጽ፤ ትሕነግ ተመልሶ በማንሰራራት በብሔራዊ ደኅንነታችን ላይ ተቀዳሚ አደጋ ሊኾን በቅቷል የሚለው የአብን መግለጫ፤ መወሰድ ይኖርባቸዋል ያላቸውንም እርምጃዎች በመግለጫው አካትቷል።
የአብን ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)
ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣
ለሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች፤
የኢትዮጵያ ጉዳይ ለሚያሳስባችሁ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን፤
በመላው ዓለም ለምትገኙ ሰላም ወዳድ ኃይሎች በሙሉ!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሰኔ 26 እና 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅና ዙሪያ መለስ ውይይት በማድረግና፤
• የሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ መሠረት ለመጣልና በሕዝብ ይሁንታ ብቻ ሥልጣን የሚይዝ ሥርዓት ለመፍጠር የተደረገውን 6ኛውን አገራዊ የምርጫ ሒደት በመገምገም፤
• የታላቁን የዓባይ ግድብን በማጠናቀቅና እንደ አገር የተፈጥሮ ጸጋችንን ተጠቅመን የመልማት መብታችንን ለማረጋገጥ በተያያዝነው ጥረት ረገድ የተጋረጡብንን ተግዳሮቶች በመገንዘብ፤
• ሕዝባችን በሰላምና ደኅንነት እጦት፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና መረን በለቀቀ የኑሮ ውድነት እየደረሰበት ያለውን ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት ግምት ውስጥ በማስገባት፤
• ከሁሉም በላይ አገራችን ከውስጥ በከሃዲያንና እኩያን ኃይሎች ቅንጅት፣ ከውጭ በታሪካዊ ጠላቶቻችንና ዓለም አቀፍ አጋሮቻቸው አይዞህ ባይነትና ድጋፍ የተደቀነባትን የሕልውና ሥጋት ተቀዳሚ ትኩረት በመስጠት፤
የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ የደረሰባቸውን አቋሞች ለተከበረው ሕዝባችን፣ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና በአጠቃላይም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ ይወዳል።
1. 6ኛውን አገራዊ ምርጫ 2013 በተመለከተ
አብን እንደ ድርጅት የመጀመሪያው ዐቢይ የፖለቲካ ተመክሮው በኾነው በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ውስጥ ለመሳተፍ ሲያቅድ፣ ገና ከመነሻው አገራችን የምትገኝበትን የፖለቲካ አውድ በመገምገም በምርጫው የመሳተፉን ውሳኔ ያደረገው በዋነኝነት ከድርጅታዊ ፋይዳዎች ይልቅ ለአገራዊ ፖለቲካው መረጋጋትና ለዴሞክራሲያዊ ተመክሮ ግንባታ ከሚኖረው ፋይዳ አንጻር እንደኾነ በይፋ አሳውቋል።
አብን አገራዊ ፓርቲ እንደመኾኑ መጠን የምርጫ ዘመቻውን ስትራቴጂክ ግቦችና ማስፈጸሚያ ስልቶችን በዝርዝር በመንደፍ፣ አማራጭ ፖሊሲዎቹን በማኒፌስቶ በመሰነድና ሙሉ ድርጅታዊ ኃይሉን በማንቀሳቀስ በምርጫ በሚሳተፍባቸው በአማራና ሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች 510 እጩዎችን በማቅረብ ሰፊውን መራጭ ሕዝብ ለመድረስ ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል።
በዚህም መሠረት የምርጫ ዘመቻው ከነተግዳሮቶቹ ተጠናቅቆ፣ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ፓርቲያችን በሚወዳደርባቸው ክልሎች ድምፅ ተሰጥቶና በከፊል ጊዜያዊ ውጤት ተገልጾ በድኅረ ምርጫ ሒደት ላይ እንገኛለን።
ፓርቲያችን በመላ አገሪቱ በተወዳደረባቸው አካባቢዎች በምርጫው ሒደት የተፈጸሙትን ዐበይት ጥሰቶች በማሰባሰብና በዝርዝር ቅሬታዎችን በመሰነድ በሕግ አግባብ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርቧል። የምርጫ ቦርድ ከተጣለበት ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት አኳያ ከሰው፣ ከፋይናንስ፣ ከተመክሮና ከሎጂስቲክ አቅም ውሱንነት ቢታይበትም በአጠቃላይ ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ አንጻራዊ አዎንታዊነት እንዳሳየ እናምናለን። በቦርዱ የበላይ አመራር የታየው ገለልተኝነት፣ ግልጽነትና ፍትሐዊነት መንፈስ እንደ ተቋም የሚፈተንበት ወቅት እንደኾነም እንገነዘባለን።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሕዝባችን ይህንን ሁሉ ጫና ተቋቁሞ በምርጫው ሒደት ውስጥ በመሳተፍ ላሳየው ጽናት ልባዊ አድናቆቱን በመግለጽ፣ የመራጩ ድምፅ እንዲከበር ተገቢውን ሰላማዊና ሕጋዊ ጥረት እንደሚያደርግና የሕዝባችንንም ሐቀኛ ውሳኔ ያለማወላወል እንደሚቀበል ለማሳወቅ ይወዳል።
በሌላ በኩል 6ኛው አገራዊ ምርጫ የሥርዓቱን እውነተኛ ባሕርይ በተግባር መፈተንና ማጋለጥ መቻሉን ትልቁ ውጤት አድርጎ መውሰድ ይቻላል። በምርጫው ሒደት የታየው ጎዶሎነትና ክፍተት ከምርጫ ውጤት አኳያ የምንመዝነው ከኾነ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የሐሳብ ብዝኀነት የማያመለክት መኾኑን መናገር ይቻላል።
አብን እንደ ድርጅት በምርጫ በመሳተፉ ምን አገኘ፣ አሳካ የሚለውን ስንገመግም አንዳንድ ተስፋ ሰጭ ነገሮች እንዳሉ መካድ አይቻልም። ከሁሉም በላይ የሕዝባችን እውነተኛ ወኪል ስለመኾናችን ሕዝባችን የነበሩትን ጫናዎች ተቋቁሞ በሰጠን የመተማመኛ ድምፅ በቂ ማረጋገጫ አግኝተናል። ይህም የመጪው ዘመን ፓርቲ መኾናችንን ይመሰክራል። በአገር አቀፍ ደረጃ በተሻለ ሕዝብን የማስተባበር አቅም እንዳለንና ጠንካራ ተገዳዳሪ የፖለቲካ ኃይል መኾናችንን በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጠናል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የምርጫው ሒደት አጠቃላይ ድርጅታዊ ቁመናውን የሚፈትሽበት መልካም አጋጣሚ መኾኑንም ይገነዘባል። በቀጣይም ከሒደቱ ያገኛቸውን ተመክሮዎችና ትምህርቶች በማካተትና ሁለገብ የማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰድ ለብሔራዊ ፖለቲካችን ሁነኛ ሚና መጫወቱን እንደሚቀጥል አያጠራጥርም።
2. ብሔራዊ ደኅንነትን በተመለከተ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በተለይ በአገር ሉዓላዊነትና አንድነት፣ በሕዝብ ጥቅምና ክብር፣ በአገረ መንግሥቱ ቀጣይነት ረገድ ግልጽና የማያሻማ አቋም ያራምዳል። በገዥው ፓርቲ ግልጽ ፍረጃ፣ ወከባና ጥቃት እየደረሰበትም ቢኾን የፖለቲካ ማዕከሉ እንዲረጋጋና በአፍሪካ ረዥሙንና ደም አፋሳሹን የእርስ በርስ ጦርነት ያደረገች አገር ተመልሳ ወደ ቀውስ እንዳትገባ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
አብን ወቅታዊው የአገራችን ብሔራዊ ደኅንነት ከጊዜ ጊዜ እየከፋና እጅግ አሳሳቢ እየኾነ መምጣቱን ይገነዘባል። የውጭ ወራሪዎችና የውስጥ ቦርቧሪዎች ከተቻለ ኢትዮጵያን ለየዘውጉ አምበሎች በታትኖ ከዓለም ካርታ ለማጥፋት፤ ካልኾነ ደግሞ ውስጣዊ አንድነት የሌላት፣ ደካማና ፍላጎታቸውን ያለማንገራገር የምትቀበል አድርገው ለማሽመድመድ እየተረባረቡ ይገኛሉ።
ከዚህ አንጻር የብልጽግና አገዛዝ የአገሪቱን፣ የዜጎችና የመንግሥቱን ሰላምና ደኅንነት፣ ጥቅምና ክብር በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ ክፍተቶች እየተስተዋለበት ነው። በአሁኑ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረገው ከፍተኛ ተጋድሎ ከአፈናና ጭቆና መንበሩ የተባረረውና በአገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ እና አፋር ልዩ ኃይልና ሕዝባዊ ሚሊሺያ ድባቅ የተመታው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) ተመልሶ በማንሰራራት በብሔራዊ ደኅንነታችን ላይ ተቀዳሚ አደጋ ሊኾን በቅቷል።
አብን ማዕከላዊ መንግሥትና በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት አገሪቱ ከተደቀነባት የሕልውና አደጋ ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የራሳቸውን ሚና በግልጽ ከመወሰን አንስቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ የብሔራዊ ደኅንነት እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ ያቀርባል።
መንግሥት ልዩ የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ፤ በተለይም አሸባሪው የትሕነግ ቡድን መልሶ በተቆጣጠረው በትግራይ የተማሪዎችንና የሲቪል ዜጎችን፤ በአጠቃላይም የትግራይን ሕዝብ ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ይጠይቃል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ሁኔታ አብንን በእጅጉ ያሳስበዋል። የትግራይ ሕዝብ በመካከሉ ለሚገኙ ተማሪ ልጆቹ አስፈላጊውን ጥበቃና ክብካቤ እንዲያደርግ ጥሪ እናደርጋለን።
አብን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ አገር ወዳድ ዜጎችና በተለይም ወጣቱ የሕብረተሰብ ክፍል አገራችን ስለገጠማት የብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ኢትዮጵያን ለመታደግ በአንድነት እንዲሰለፉ ጥሪ ያደርጋል።
በወታደራዊ ኃይል የሚገኘው ድል ዳግም በዲፕሎማሲው አውድማ እንዳይነጠቅ መላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የአገራቸው አምባሳደር በመኾን በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ትግል እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀርባል።
በተለይም ደግሞ በፀረ-ኢትዮጵያው ጎራ በጠላትነት ተፈርጆ ዘርፈ ብዙ ጥቃት የተሰነዘረበት የአማራ ሕዝብ የሚገኝበትን ወቅታዊ የሥጋት ደረጃ በውል ተገንዝቦ የበኩሉን ጥንቃቄና ዝግጅት እንዲያደርግ፣ የአማራ ዲያስፖራ በሕዝባችንና በአገራችን ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመቀልበስ ሁለገብ የሐሳብ፣ የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲ ተሳትፎውን አጠንክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀርባል።
አብን አፍሪካውያን ወንድሞቻችን፣ መላው የኢትዮጵያ ወዳጆችና አጋሮች የጥንታዊ ሥልጣኔ፣ አኩሪ የነፃነት ታሪክ ያላት አገር በእኩያን ኃይሎች የተከፈተባትን ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥቃት ለመመከት ከጎናችን እንዲሰለፉ ጥሪ ያደርጋል። በዚህ ረገድ በአካባቢው ጉዳይ ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት በአፍራሽ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እንዳይደለሉና የችግሩን ዙሪያ ገብ በፍትሐዊነት በመገምገም እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ያቀርባል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በአገራችን ላይ የተደቀነውን ጽኑ የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ለመመከትና ከምንም በላይ የቆመለትን የአገር አንድነትና ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ጥቅምና ክብር እንዲሁም የአገረ መንግሥቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሁሉ ድርጅታዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን በአጽንኦት ለመግለጽ ይወዳል።
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም.