የአውራምባ ታይምስ አዘጋጆች የክስ ደብዳቤ ደረሳቸው
Ethiopia Zare (ረቡዕ ኅዳር 3 ቀን 2001 ዓ.ም. November 12, 2008)፦”አውራምባ ታይምስ” የተሰኘው በሀገር ውስጥ የሚታተመው ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ እና ምክትል ዋና አዘጋጁ ጋዜጠኛ ወንድይራድ ደብረጽዮን የዓቃቤ ሕግ የክስ ደብዳቤ የደረሳቸው ሲሆን፣ ፍርድ ቤት ለኅዳር 17 እንዲቀርቡም ጥሪ ደርሷቸዋል።
የአንድነት ፓርቲ ም/ሊቀመንበርና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ከአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ ”ቅንጅት የሚለው ስም አግባብ ባልሆነ መልኩ ለመንገደኛ ተሰጠ በሕጋዊ መንገድ የተሰጠንን ፓርቲ አናንቀዋል” በማለት አቶ አየለ ጫሚሶ በጋዜጣው አዘጋጆችና በዶ/ር ያዕቆብ ላይ ክስ መመስረታቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።
በዚሁ ክስ ምክንያት ጋዜጠኞቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ቃላቸውን ሰጥተው በዋስ ተለቅቀው ነበር። ያሰራቸውና ቃላቸውን የተቀበላቸው የአዲስ አበባ ፖሊስም ምርመራውን አጠናቅቆ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ አስተላልፏል።
ነገር ግን ለጋዜጠኖቹ የደረሳቸው የክስ ደብዳቤ፤ ”የሐሰት ወሬ በማሰራጨት፣ ህዝብን በመንግሥት ላይ በማነሳሳት እና የሀገሪቱን ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥል ነገር እንዲፈጠር ህዝቡን በማነሳሳት” የሚል መሆኑ ከአቶ አየለ ጫሚሶ ክስ ጋር በምን መልኩ እንደሚያያዝ ለተከሳሾቹ ጋዜጠኞችም ሆነ ለብዙዎች ግልጽ አልሆነም።
ክሱ ምናልባትም የግንቦት 7 ፓርቲን አስመልክቶ በጋዜጣው ላይ ከቀረቡ ዘገባዎች ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ ካሰባሰብነው አስተያየት ለመረዳት እንደቻልነው ከሆነ፤ ኢህአዴግ በሀገር ውስጥ ጭል ጭል እያሉ ያሉትን በጣት የሚቆጠሩ ጋዜጦች ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞችን በትንሹም በትልቁም ነገር በመክሰስ፣ በማሰር፣ በመቅጣት፣ ... ጫና እያሳደረባቸው ከጋዜጠኝነቱና ከሀገር እንዲሸሹ ለማድረግ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ የግንቦት 97ን ምርጫ ተከትሎ ከቅንጅት መሪዎች ጋር ታስረው ከነበሩት ጋዜጠኞች ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ በ1998 ዓ.ም ከመታሰሩ በፊት የ”ሓዳር” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እንደነበር ይታወቃል።