የሶማሊያ ጉዳይ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን ነው
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ኅዳር 13 ቀን 2001 ዓ.ም. November 22, 2008)፦ ኢትዮጵያውያን መሥዋዕት የሆኑበትና በርካታ ገንዘብና ንብረት የጠፋበት የሶማሊያ የሠላም ጥረት፣ ከቁጥጥር ውጪ በመሆን ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ባለፈው ማክሰኞ በአዲስ አበባ የተደረገው፣ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ሚኒስትሮች ም/ቤት 30ኛ ልዩ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ፤ የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን እንዳስታወቁት፣ የሶማሊያ መሪዎች፣ የሶማሊያ ህዝብና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተለያዩ ተቋማት በሶማሊያ ሠላም ለማምጣት ቁርጠኝነታቸውን ባላሳዩበት በአሁኑ ወቅት፣ የኢትዮጵያ ጦር መሥዋዕትነት እየከፈለ አይቀጥልም ብለዋል።
አቶ ስዩም መስፍን ይህን ይበሉ እንጂ፤ በሰሞኑ የኢጋድ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ የመውጣቱ ጉዳይ መልስ እንዳላገኘ ታውቋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ሲመሠረት፣ በኢትዮጵያ የሶማሊያ አምባሣደር የነበሩትና፣ በአሁኑ ወቅት በሰባት አፍሪካ ሀገራት የሶማሊያ አምባሣደር የሆኑት አብዲ ካረን ፋራህ ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለፁት፤ የአልሻባብ ታጣቂዎች አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት፣ በሽግግር መንግሥቱ ድክመት በተለይ በፕሬዝዳንቱና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል አለመግባባት በመኖሩ ነው ብለዋል።
አምባሣደር አብዲ ካረን ፋራህ ጨምረው እንደተናገሩት፤ ”በአሁኑ ሰዓት ፕሬዝዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርስ በርሳቸው ተነጋግረው የማይሠሩበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው” በማለት ገልፀዋል። አያይዘውም ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ትብብር ካላደረገላቸው ”ሶማሊያ ወደ የርስ በርስ ጦርነት ልታመራ ትችላለች” ብለዋል።
በሌላ በኩል ”ቀስ በቀስ መላውን የሶማሊያ ግዛት እየተቆጣጠሩ የመጡት የአልሻባብ ታጣቂዎች፣ ወደ መቋዲሾ እየገሰገሱ ነው” በማለት ስጋትቸውን የገለፁት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ዩሱፍ አህመድ በኬንያው የኢጋድ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
ከአስራ አምስት ቀናት በፊት ኢጋድ በናይሮቢ በሶማሊያ ጉዳይ መደበኛ ያልሆነ ስብሰባ ባካሄደበት ወቅት የሽግግር መንግሥቱና ተቃዋሚ ፓርቲዎች አዲስ የካቢኔ ሹመትና የጋራ ሀገራዊ ደኅንነት ለማቋቋም መስማማታቸው ይታወሳል፤ ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች የተስማሙበት ሃሳብ ሳይተገበር የወጣለት የግዜ ሠሌዳ አልፏል።
የኬንያ ስምምነት ተፈፃሚ ሊሆን ባለመቻሉ የሶማሊያን መሪዎች ለሠላም ያላቸውን ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን፣ በአዲስ አበባ የኢጋድ የሚኒስትሮች ስብሰባ ንግግራቸው እንደጠቀሱት፤ ”የሽግግር መንግሥቱና ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በኬንያ የተደረገውን የኢጋድ ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈፀም አልቻሉም፤ እርስ በርሳቸው ጦርነት ለማድረግ እንደመረጡ ማወቅ አለባቸው፣ እኛ ከጎናቸው ነን ልንረዳቸው እንችላለን እንጂ የሶማሊያን ችግር በነሱ ቦታ ሆነን አንጋፈጥም” ብለዋል።
በሶማሊያ ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል ያለው አለመግባባት ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ የቻለው፣ በባይደዋ የፀጥታ ችግር ምክንያት የፓርላማ አባላቱ ተሰብስበው ለመነጋገር ባለመቻላቸው መሆኑን የጠቀሱት አምባሣደር ፋራህ፤ የኢጋድ የመሪዎች ስብሰባ በኬንያ ሲካሄድ፣ ከ250 በላይ የሶማሊያ የፓርላማ አባላት ተገኘተዋል። በአራት ዓመት ውስጥ ይህን ያህል የፓርላማ አባላት ሲገኙ የመጀመሪያቸው ቢሆንም፤ በወቅቱም ቢሆን አንድ ላይ ተሰብስበው ስለሀገራቸው ጉዳይ ለመነጋገር አለመቻላቸውን አምባሣደሩ ተናግረዋል።