የአንድነት ሠላማዊ ሰልፍ ተከለከለ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2001 ዓ.ም. April 7, 2009)፦ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮችና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ተጠሪዎችን በማካተት ወ/ት ብርቱካን የታሰረችበትን ሂደት በመቃወም የፊታችን ኀሙስ ሚያዝያ 1 ቀን 2001 ዓ.ም. (April 9, 2009) ጠርቶት ነበረው ሠላማዊ ሰልፍ በመንግሥት በኩል ፈቃድ በመከልከሉ በዕለቱ ሰልፉ እንደማይካሄድ ታወቀ።
ፓርቲው የጠራው ሰልፍ የድርጅቱ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን የታሰረችበትን ሁኔታ በመቃወምና ለወ/ሪቷ ተሰጥቶ የነበረው ይቅርታ መነሳት አግባብነት የሌለው መሆኑን ለመግለጽ የታሰበ ከመሆኑም በላይ የዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያደርግ ለማሳሰብም ጭምር የታቀደ ነው።
ከፍተኛ አመራሮች ሰልፍ በመውጣት ተቃውሟቸውን ለማሰማት ውሳኔ በማሳለፍ ሚያዝያ 1 ቀን 2001 ዓ.ም. የጠሩት ሰልፍ የመንግሥት ባለስልጣናት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው የዓለም ፓርላማዎች ሕብረት ስብሰባ ምክንያት ምንም አይነት ሠላማዊ ሰልፍ ማካሄድ እንደማይቻልና፤ አንድነት የጠራው ሠላማዊ ሰልፍም ሊካሄድ እንደማይችል መከልከሉን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልፀዋል።



