አንድነት የወ/ት ብርቱካንን እስር በመቃወም የጠራው ሠላማዊ ሰልፍ ተፈቀደ
ሰልፉ ነገ ጠዋት ይደረጋል
Ethiopia Zare (ረቡዕ ሚያዝያ 7 ቀን 2001 ዓ.ም. April 15, 2009)፦ የዓለም ፓርላማ አባላቶች ስብሰባ በአዲስ አበባ ይካሄዳል በሚል ምክንያት ተሰርዞ የነበረው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የወ/ት ብርቱካንን እስር በመቃወም ያዘጋጀው የሠላማዊ ሰልፍ ተፈቅዶ፤ ነገ ሚያዝያ 8 ቀን 2001 ዓ.ም. (April 16, 2009 እ.ኤ.አ.) ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ምንጮቻችን አረጋገጡ።
ሠላማዊ ሰልፉ የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆነችውን የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን የእስር ሁኔታ በመቃወም የተጠራ ሲሆን፣ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮችና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የከፍተኛና የወረዳ ተጠሪዎችን ያካተተ እንደሚሆን ታውቋል።
የወ/ት ብርቱካንን እስር በመቃወም ህዝባዊ ሠላማዊ ሰልፍ ድርጅቱ ቢጠራ ቁጥሩ እጅግ በብዙ የሚገመት ህዝብ ሊገኝ እንደሚችል በመገመትና ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን በመስጋት ቁጥሩ 250 ሰው ያልበለጡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በሠላማዊ ሰልፉ ላይ ተገኝተው ተቃውሞውን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለማሰማት ድርጅቱ መወሰኑን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ ገልጸዋል።
የሠላማዊ ሰልፉ መነሻ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 18 የቤት ቁጥር 045 በተምዶ ባምቢስ ድልድይ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ሲሆን፣ መድረሻው ደግሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት እና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት እንደሆነና ለሚያዚያ 1 ቀን ታቅዶ በነበረው ፕሮግራም መሰረት እንደሚካሄድ ታውቋል።



