By Matias Ketema (Sweden)

የዓለም የሠራተኞች ቀን በስዊድን, Mayday in Sweden 2009

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሚያዝያ 24 ቀን 2001 ዓ.ም. May 2, 2009)፦ በትናንትናው ዕለት የዓለም የወዛደሮች ቀን (ሜይዴይ) በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም በሾሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲና በሠራተኛው ማኅበር በተዘጋጀው የወዛደሮች ቀን በዓል ብዙ ሺህ ሰልፈኛ በተገኘበት ተከብሮ የዋለ ሲሆን፣ የስዊድን የሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር ባንኛ ቬድን የወ/ት ብርቱካን እስር እንዳሳሰባቸው ባደረጉት ንግግር ላይ ገልፀዋል።

 

በዚህ የስዊድንን ማኅበረሰብ ጨምሮ የተለያዩ ሀገር ዜጎች በወጡበት ሰልፍ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያንም ተገኝተዋል። ኢትዮጵያውያኑ በ13 ሰዓት በሰርገልስ ቶሪ በመገናኘት ወደ ሁመልጎርደን አምርተው በዓሉን ለማክበር ከወጣው ሰልፈኛ ጋር በ14 ሰዓት ተቀላቅለዋል።

 

የዓለም የሠራተኞች ቀን በስዊድን, Mayday in Sweden 2009

 

ሰልፈኛው ከቦታው በመነሳት በከተማው ዋና ዋና አደባባይ ባደረገው ሰልፍ ላይ ኢትዮጵያውያኑም የወ/ሪት ብርቱካን ምስል ያለበትን ካኒተራ በመልበስ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብና መፈክሮችን በመያዝ ”ብርቱካን ሚደቅሳ ትፈታ! በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትና የዲሞክራሲ መብት ይከበር! ነፃ ምርጫ ይኑር! የሕግ የበላይነትና የፕሬስ ነፃነት ይጠበቅ! ...” በማለት ድምፃቸውን እያሰሙ የሰልፈኛው የመጨረሻ መቆሚያ በሆነው በኖራባንቶርየት ደርሰዋል።

 

በዚሁ አደባባይ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ተሰብስቦ የነበረ ሲሆን፣ በ14፡45 ሰዓት (በኢትዮ. አቆጣጠር 8፡45 ሰዓት) የስቶክሆልም ኮሚዩን የተቃዋሚ ፓርቲ ከንቲባ የሆኑት ካሪን ጀምቲን ንግግር አድርገዋል። ከሳቸው በመቀጠል ብቅ ብለው ሲታዩ ገና ሰልፈኛው በሞቀ ጭብጨባ የተቀበላቸው በኋላም ስማቸውን እየጠራ አድናቆቱን የገለጸላቸው የስዊድን የሠራተኛ ማኅበርና የወቅቱ የአውሮፓ የሠራተኞች ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት ባንኛ ቬድን ንግግር አድርገዋል።

 

 

የዓለም የሠራተኞች ቀን በስዊድን, Mayday in Sweden 2009
 

 

ባንኛ ቬድን እጅግ በሞቀና ሰልፈኛውን በተደጋጋሚ በአድናቆት ባስጮኸና ባስጨበጨበ ንግግራቸው ጣልቃ የኢትዮጵያ መንግሥት በዜጎቹ ላይ በሚያደርገው የመብት ረገጣና የዲሞክራሲ አፈና እጅግ እንደተበሳጩና እንዳዘኑ ገልጸው፤ አግባብ ባልሆነ መንገድ ታስረው የሚገኙት የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው በመናገር አለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

 

ከሳቸው ንግግር በኋላ ሰልፈኛው የዓለም ሠራተኞች መዝሙር የሆነውን ”ኢንተርናሲዮናል”ን በአንድነት በመዘመር በ16 ሰዓት (በኢትዮ. አቆጣጠር 10 ሰዓት) ላይ ሰልፉን አጠናቅቆ ተበትኗል።

 

”ኢንተርናሲዮናል” በብዙ ሀገሮች ቋንቋ ተተርጉሞ ለረጅም ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሠራተኛው፣ በሶሻል ኮምዩኒስት እና በሶሻል ዲሞክራቶች የሚዘመር ሲሆን፣ ይሄንን መዝሙር ፈረንሣዊው ዩጂኒ ፖቲየር በ1871 እ.ኤ.አ. ጁን ወር ላይ እንደጻፉት ይታወቃል።

 

የዓለም የሠራተኞች ቀን በስዊድን, Mayday in Sweden 2009

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ