Ethiopia Zare (አርብ ግንቦት 14 ቀን 2001 ዓ.ም. May 22, 2009)፦ በሶማሊያ የአልሻባብ እና የሂዝቡ እስላም ተዋጊዎች፣ በሌላ መጠሪያ ስማቸው “የሶማሊያ ዳግማዊ ነፃነት ኃይል” ተፋላሚዎች፤ መቋዲሾን ዋነኛ ዒላማቸው አድርገው በመዋጋት ላይ ሲሆኑ አስመራንና አዲስ አበባ በሱማሊያ ጉዳይ በስተጀርባ መወነጃጀል መቀጠላቸው ተዘገበ።

 

የአስመራው መሪ አቶ ኢሣያስ አፈወርቂ፦ “በሞቃዲሾ የሚገኘው የሠላም አስከባሪ ኃይል ይውጣ! ለሶማሊያ ችግር መባባስ ተጠያቂዎቹም የአዲስ አበባው አስተዳደር፣ ኢጋድ፣ የአፍሪካ ሕብረት ተብዬው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና አሜሪካ ናቸው” በማለት ወቀሳቸውን ሲያሰሙ። ረቡዕ ግንቦት 12 ቀን 2001 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ የጠራው የአፍሪካ ሕብረትም “የተባበሩት መንግሥታት ለሶማሊያ የነበረና ወቅታዊ ችግር ዘለቄታዊና አስተማማኝ መፍትሔ ይፈልግ፣ የሶማሊያን ጽንፈኞች በጦር መሣሪያ በምትረዳው አስመራም ላይ ጠጠር ያለ ማዕቀቡን ይጣል፣ ለረድኤት ተግባር ካልሆነ ወደ መቋዲሾ በሚያመሩ አውሮፕላኖች ላይ የበረራ ቁጥጥር ይደረግ” የሚሉ እና ሌሎች የአቋም መግለጫ ነጥቦችን አሰምቷል። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም የአፍሪካን ሕብረት ባለሥልጣኖች፣ ሚኒስትር ስዩም መስፍንን እና ተቀዳ አለሙን መላልሶ በማሳየት ለአስመራ አስተዳደር ማስፈራሪያ አዘል ንግግር ሲያሰሙ አስደምጧል።

 

አሥመራ “አንድነቷና ሠላሟ የተጠበቀ፣ የሌሎች ጣልቃ ገብነት የሌለባት፣ የህዝቧ ነፃነት እና የእምነት መብቱ የተከበረባት ሉዓላዊት ሶማሊያን ማየት እሻለሁ። ለዚህም ስኬት የበኩሌን ድጋፍ ከማድረግ አልቆጠብም” በማለት አቋሟን ስትገልጽ፤ አዲስ አበባ በበኩሏ “ኢትዮጵያ የሶማሊያ ጽንፈኛ የሙስሊም ኃይሎች ወደ መቋዲሾ የሚያደርጉትን ያልተቋረጠ እንቅስቃሴ በጥንቃቄ እየተመለከተች ነው። የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ህልውና አደጋ ላይ ወደቀ ማለትም ለአካባቢው ሠላም ጠንቅ ነው። ስለዚህ ችግሩን በቸልታ የምትመለከትበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም” እያለች ነው።

 

“አስመራ እና አዲስ አበባ በተለመደው ባህሪያቸው በሶማሊያ ጉዳይ የተካረሩ ይምሰሉ እንጂ ዋና አጀንዳቸው በመቋዲሾ ኪሣራ ፖለቲካዊ ትርፍ ማግኘትና የሥልጣን ዕድሜያቸውን ማራዘም ነው …” በማለት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊ ተንታኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

በተያያዘም የኢትዮጵያ ጦር የሽግግር መንግሥቱን ለመርዳት ወደ ሶማሊያ ድጋሚ መግባት ጋር በተያያዘ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኀን የዘገቡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያው አስተዳደር ግን ሁኔታው ከእውነት የራቀ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ