Ethiopia Zare (ኀሙስ ሰኔ 18 ቀን 2001 ዓ.ም. June 25, 2009)፦ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከመድረክ ለምክክር ጋር በጋራ ሊያሠሩ ይችላሉ ተብለው በታመኑባቸው ነጥቦች ላይ በቅርቡ ውሳኔ እንደሚሰጥ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገለጹ።

 

ፓርቲው ነጥቦቹን የያዙትን ከ60 ገጽ በላይ ሰነድ ለምክር ቤት አባላቶቹ የበተነ ሲሆን፣ አባላቶቹም ሰነዶቹን ከመረመሩ በኋላ በቅርቡ ለውሳኔ ጉባዔ እንደሚቀመጡ ለመረዳት ተችሏል። አንድነት ከመድረክ ጋር ተቀራርቦ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ያደረገ ቢሆንም፤ በአባላቶች በተነሱ ጥያቄዎች ምክንያት ዲሞክራሲያዊ ውሳኔ ለመስጠት በጋራ የሚያሠሩ ነጥቦችን አዘጋጅቶ ለአባላቶች በመበተን ጠቅላላ ውሳኔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

 

በተያያዘም አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በየክልሎቹ ካቋቋማቸው ከ58 በላይ ጽ/ቤቶቹ ሠራተኞችና አባላት ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት ከዕለት ዕለት እየጨመረ ከመምጣቱም በላይ የክልል ባለሥልጣናት አንድነት ፓርቲ ሕገ ወጥ ነው በማለት አባላቶቹን እንደሚያስፈራሩና እንደሚያስሩ ተገልጿል።

 

የአንድነት አካሄድ ገዥውን ፓርቲ አስጨንቆታል ያሉት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ፤ መጭውን ምርጫ በሚመለከት ሙሉ በሙሉ ዝግጅት እንደሚያደርጉና በምርጫው በመሳተፍ ወይንም ባለመሳተፍ ጉዳይ ገዥው ፓርቲ ነው ተጠያቂ የሚሆነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ