ቴዲ አፍሮ የዛሬ ወር ይፈታል

Ethiopia Zare (ሐሙስ ሐምሌ 9 ቀን 2001 ዓ.ም. July 16, 2009)፦ ዛሬ የዋለው የሰበር ቅሬታ ሰሚ ችሎት አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ላይ የሁለት ዓመት እና የ18 ሺህ ብር ቅጣት የወሰነበት ሲሆን፣ በዚህ የቅጣት ውሳኔ መሠረት ቴዲ አፍሮ የዛሬ ወር ይፈታል።
ሰበር ችሎቱ የተሰየመው በ5 ዳኞች የነበረ ሲሆን፣ ችሎቱን ሲከታተሉ የነበሩ በርካታ የቴዲ አፍሮ አድናቂዎች፣ ቤተሰቦቹና ወዳጅ ዘመዶቹ ፍርዱን ሲሰሙ ደስታቸውን በጩኸትና በዘፈን ገልፀዋል።
ዓቃቤ ሕግ የስድስት ዓመት እስራት ሊፀናበት ይገባል ብሎ የተከራከረ መሆኑን መዘገባችን አይዘነጋም። በቴዲ አፍሮ ላይ ዛሬ ፍርድ ቤቱ የሁለት ዓመት (24 ወራት) እስራት ስለወሰነበት እጁ ከተያዘበትና ከታሰረበት ከመጋቢት 8 ቀን 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ያለው ጊዜ ይቆጠራል። በዚህም መሠረት እስከዛሬ 15 ወራት ታስሯል።
በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት አንድ እስረኛ ከአንድ ዓመት እስር ላይ የ4 ወራት አመክሮ ተቀንሶለት 8 ወር ይታሰራል። ቴዲ አፍሮም ከሁለቱ ዓመት ላይ 8 ወራት ከተቀንሶለት የእስር ጊዜው 16 ወራት ይሆናል። በዚህ ስሌት መሠረት ልክ የዛሬ ወር ነኀሴ 8 ቀን ይፈታል።
ዳኞቹ ውሳኔያቸውን ከማሰማታቸው በፊት 21 ደቂቃ የፈጀ ሕጋዊ ትንታኔ ሰጥተዋል።



