Ethiopia Zare's weekly news digest, week 22, 2012 Ethiopian calendar

ከጥር 25 - የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሃያ ሁለተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከጥር 25 - የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ያሳለፍነው ሳምንት በመጀመሪያው ቀን ሰኞ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወቅታዊ ጉዳዮች ማብራሪያ የተጀመረ ነበር። በፓርላማ ተገኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ከሁለት ሰዓት ላቅ ላለ ጊዜ ማብራሪያና ምላሽ ሠጥተዋል። በዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የተለያዩ ጉዳዮች ተዳሰዋል።

በሳምንቱ ቀዳሚ ከኾነው ከዚህ ዜና ባሻገር አሁንም ለአገሪቱ ፈተና እየኾነ የመጣው ሕይወት እያሳጡ ያሉ ግጭቶች በደቡብ ክልል ቴፒና አዲስ አበባ ላይ ተከስተዋል።

የህዳሴ ግድብና የዋሽንግተኑ ስምምነት አሁንም አነጋጋሪ ኾኖ ቀጥሏል። በዚህ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ አቋሜን እወቁልኝ ያለችበትንም መግለጫ ሠጥታለች። የኢትዮጵያን ጥቅም ሊነካ የሚችል አንድም ስምምነት ልትፈራረም እንደማትችልም የገለጸች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ጥቅሟን አሳልፎ የሚሠጥ ስምምነት ልትፈርም እንደኾነ በመጥቀስ የሚራገበውም ወሬ ትክክል አለመኾኑን በይፋ ያሳወቀችው ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

ከቀዳሚው ሳምንት አነጋጋሪ ወሬዎች ውስጥ ለፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች መንግሥት ሲያደርግላቸው ነበር የተባለውን ጥበቃ ማንሳቱ ሲሆን፤ አቶ ጃዋር መሐመድም እስካሁን ሲደረግላቸው የነበረው ጥበቃ ስለመነሳቱ የተገለጸበት ነው። ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቻይና በረራውን ቢያቆም ይሻላል የሚለውን ምክረ ሐሳብ እንደማይቀበል ያሳወቀበትንና የቻይና በረራውን እንደማያቋርጥ በይፋ የተገለጸው በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ነው።

ከአንድ ሳምንት በፊት በፓርላማ ቀርበው ሹመታቸው የጸደቀላቸው የሦስት ሚኒስትሮች የሹመት ፊርማ ሳይደርቅ ከደኅንነትና ከጸጥታ ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉ ተቋማትን የሚመሩ አምስት ሹመቶች መሥጠታቸውም ከሳምንቱ ዜና ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን፤ ሹመቱ የተሠጠባቸው የኃላፊነት ቦታዎች ግን ሰዎች የሚፈራረቁባቸው የመኾናቸው ነገር ማስደመሙ አልቀረም።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ በጥርጣሬ ማቆያ ማዕከል እንዲቆዩ የተደረጉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር ከፍ ማለቱም ከሳምንቱ ወሬዎች የሚጠቀስ ነው። ከቻይና የሚመጡ መንገደኞች ለብቻ እንዲመረመሩ ውሳኔ ተላልፎ፤ ይኸው እየተተገበረ ነው። ኢሕአዴግ በይፋ በምርጫ ቦርድ መፈራረሱ የተነገረበት፣ ሕወሓትም ንብረት ክፍፍል እሻለሁ ብሎ ባመለከተው መሠረት ምርጫ ቦርድ ውሳኔ የሠጠው በዚሁ ሳምንት ነው።

በፓርላማ የጥላቻ ንግግርን የተመለከተው ሕግ መጽደቅ የለበትም ተብሎ ሙግት የተገባበት ወሬም የተሰማው በዚሁ ሳምንት ነው። የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔም የሳምንቱ ዜና አካል ነው።

ከኢኮኖሚ ዜናዎች ውስጥ በአፍሪካ ትልቁን የመድሃኒት ማምረቻ ለመክፈት መታሰቡንና በዚህም እንደ መነሻ አንድ ቢሊዮን ታብሌቶችን ለማምረት አቅም ያለውን የመድሃኒት ማምረቻ ለመክፈት የመሠረት ድንጋይ መቀመጡና ከ460 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የወጣበት የገናሌ ዳዋ ግድብ ከመጠናቀቂያ ጊዜው ከሰባት ዓመታት በላይ ዘግይቶ መመረቁ የሚጠቀሱ ናቸው። ከሳምንቱ ክንውኖች የተወሰኑት በዚህ መልኩ በኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፓርላማው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በፓርላማ ተገኝተው ከፓርላማ አባላት ለተነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ የሠጡት ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሰኞ ጥር 25 ቀን ነበር። ከፓርላማ አባላቱ ወቅታዊ ናቸው የተባሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሠጡት ኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት የነበረችበትን አደገኛ ሁኔታና ከለውጡ በኋላ የተሠሩትን ሥራዎች ወደኋላ መለስ ብለው በማብራራት ነበር። ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ እንደ አገር መቀጠል የማትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳ እንደነበርና ከለውጥ በኋላ እስረኞች መፍታት ተችሏል፤ በተለያዩ አገራት ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን በማስፈታት ወደአገር እንዲመለሱ ተደርጓል። በውጭ የነበሩ ፖለቲከኞች ወደ አገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ መደረጉም ሌላው የለውጡ ውጤት እንደነበር፤ ነገር ግን እንዲህ ያሉ እርምጃዎች ሲወሰዱ በአገሪቱ ከላይ እስከታች ተደራጅቶ የነበረው አደገኛ ኔትዎርክ ሊፈጥር የነበረው እንቅፋት ቀላል እንዳልነበር ገልጸዋል። ሚዲያዎች ብሎክ እንዳይደረጉና ሰዎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ማድረግ ተችሏል።

አገረ መንግሥቱ በግለሰቦች እጅ ላይ ወድቆ ነበር፤ የነበረውን መንግሥታዊ ጥልፍልፍ ለመፍታት ተሞክሯል፤ መንግሥታዊ ጥልፍልፎሹ ከለውጡ ማግስት የነበረውን መንግሥታዊ ሥራ አደጋ ላይ ጥሎት እንደነበርም አብራርተዋል። በለውጡ ማግስት ከከፍተኛ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ የመንግሥት ሥልጣንን ተቆጣጥሮ የነበረ ያልተገባ ኔትወርክ በለውጡ በመጀመሪያዎቹ ወቅቶች ሙሉ በሙሉ መለየት አልተቻለም ነበር በማለት፤ ሲገጥማቸው የነበሩትን ተግዳሮቶች ገልጸዋል። ይህንን ያልተገባ ኔትወርክ በረጅምና አጭር ዕቅድ ለማስቆም ሥራዎች ተለይተው ወደ ሥራ በመግባት ውጤት መገኘቱን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ለነበሩት አብዛኛዎቹ ችግሮች ምንጭ ራሱ ገዢው ፓርቲ እንደነበር በመገለጹም፤ አፋኝ ናቸው የተባሉ ሕጐች እንዲሻሻሉ መደረጉንም አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ካጋጠሙ ችግሮች ውስጥ ወቅታዊና አንገብጋቢ እንደኾነ የሚነገርለትና ብዙዎች ሲጠብቁት በነበረው የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እገታ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሠጡት ምላሽ ውስጥ፤ ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ ብሎ ራሱን ያቀረበ አካል አለመኖሩን፤ ነገር ግን መንግሥት አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን እርምጃዎች በመውሰድ፤ ታገቱ የተባሉትን ተማሪዎች ለማግኘት የተደረጉ ጥረቶችን በዝርዝር አቅርበዋል። እንደ ቦኮሃራም ያሉ የሽብር ቡድኖች ሲያግቱ፤ አግተናል ብለው የሚናገሩ መኾኑን በማስታወስ፤ እዚህ የተፈጠረው ግን የአጋቾቹን ማንነት ለማወቅ ያልተቻለ ራሱንም ያልገለጠ መኾኑ መንግሥትን የፈተነ መኾኑን ከገለጻቸው መረዳት ይቻላል። የተማሪዎችን እገታ ኃላፊነት የወሰደ አካል ባለመኖሩም “የደረሱንን መረጃ ስናጣራ በቆየንበት ጊዜ የታገተ የለም የሚል አቋም እንድንወስድ ግፊት ሲደረግብን ነበር፤ እኛ ግን የጠራ መረጃ ሳይኖረን ተጣድፈን ይህን ማለት አልፈለግንም” በማለት በጉዳዩ ላይ መንግሥታቸው የነበረበትን ሁኔታ አስረድተዋል።

የሕግ ማስከበር ችግር፣ ሥርዓት አልበኝነትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ውስጥ ከሠጧቸው ምላሾች ውስጥ፤ በአገሪቱ ላይ የሴራ ፖለቲካ ለሥርዓት አልበኝነት ምክንያት መኾኑን ገልጸዋል። ይህን የሴራ ፖለቲካ በተለያየ መንገድ በማብራራት፤ በዚህ ዙሪያ የገጠሙ ችግሮችንም ጠቃቅሰዋል። ኾኖም የሴራ ፖለቲካውን መፍትሔ ለመሥጠት እየተደረገ መኾኑ በመግለጽ፤ ኢትዮጵያ እንደ አገር እንደምትቀጥል ጥርጣሬ ሊገባን አይገባም የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል። ከለውጡ ወዲህ የአገርን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑ የተለያዩ ሁኔታዎች አጋጥመው እንደነበር በፓርላማ ማብራሪያቸው የገለጹ ሲሆን፤ እንደ ምሳሌ የጠቀሱትም አልሸባብ በኢትዮጵያ ሊፈጽም የነበረውን ጥቃቶች ነው። ይህ ግን በጸጥታ ተቋማት መከላከል መቻሉን ነው። በዕለቱ ባቀረቡት ማብራሪያ ላይ ግልጽ ባያደርጉትም፤ አገሪቱን አደጋ ላይ ሊጥሉ የነበሩና ታቅደው የነበሩ ጥቃቶችን የሚያመላክቱ ናቸው ያሉዋቸውን ተግባራት በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ፤ ወደ ግል የሚዛወሩ ድርጅቶችን የተመለከተ ነበር። ይህ ጉዳይ ብዙ የተነገረለት፣ ብዙ አስተያየት የተሠጠበት ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ1980 አጋማሽ ጀምሮ ላለፉት 20 ዓመታት 287 የመንግሥት ድርጅቶች ወደ ግል መዛወራቸውን በመጠቆም፤ ከለውጡ በኋላ ግን አንድም ወደ ግል የተዘዋወረ የመንግሥት ድርጅት ያለመኖሩን ገልጸዋል። የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በሁለት እግራቸው እስኪቆሙ ድረስ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዳይኾኑ ስለመደረጉ ጠቁመዋል። ከሪፎርሙ በኋላ ከተከናወኑ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ እንደምሳሌ የጠቀሱት ኢትዮ ቴሌኮምን ነው። በአንድ ዓመት ውስጥ 8 ሚሊዮን አዳዲስ የሞባይል ደንበኞች ማፍራት መቻሉንና የቴሌኮም አገልግሎት ላይ ዋጋ ቅናሽ መደረጉም ኢትዮ ቴሌኮም ገቢውን ማሳደግ መቻሉን ነው።

ለውጡን የሚመራው ቡድን ትግራይን ያገለለ ተግባራት ይፈጽማል የሚል አንደምታ የነበረው ጥያቄ ከምክር ቤቱ ቀርቦ ነበር። የትግራይ ሕዝብ ያገለለ ሥራ እየተሠራ ነው ለሚል ጥያቄ የትግራይን ሕዝብ ያገለለ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠር አይችልም የሚለውን አፅንኦት በመሥጠት፤ የትግራይን ሕዝብ ያገለለ ሥራ ይሠራል፣ የፌዴራል መንግሥቱ ጫና ያደርጋል የሚለው ሐሳብ ትክክል አለመኾኑን ገልጸዋል። ከዚህ ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚከተለውን መልሰዋል።

“በመንግሥት የተመረጠ ፓርቲን በሚመለከት በምርጫ ሕጉ አንድ ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ሕብረት ሲያደርግ ቀድሞ የፓርቲውን ሁለንተናዊ ነገር ይወርሳል። የብልጽግና ፓርቲ ወርሶ ገዥው ፓርቲ የብልጽግና ፓርቲ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ መደናገር አያስፈልግም። የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ብልጽግና ነው። ሕዝብ የመረጠው እናንተን ነው። እናንተ ውስጥ ያለ አብላጫ ድምፅ ያለው መንግሥት መመሥረት ይችላል። የብልጽግና ፓርቲ በምክር ቤቱ አብላጫ ድምፅ ስላለው መንግሥት እሱ ነው። በትግራይ ክልል TPLF አብላጫ ድምፅ ስላለው መንግሥት TPLF ነው። በፌደራልና በትግራይ መንግሥት መካከል ሕጋዊ የኾነ ትስስሮችና የሥራ ግንኙነቶች ይኖራሉ። በፌዴራል መንግሥት የትግራይ ተወላጆች እየተገፉ ነው የሚለው ላይ ምናልባት አንድ ሚኒስትር ከሥራቸው ተነስተዋል።

“በአሥራዎቹ የሚቆጠሩ ሚኒስትር ዴታዎች አሉን አንድም አልተነሣም። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አሉን። ያውም ሥራ አስፈፃሚ ናቸው። አልተነኩም። ሌላም ሚኒስትር አሉን፤ አልተነኩም። የትግራይ ሰዎች ተጐዱ ከኾነ ድሮም በካቢኔ የነበራቸው ቁጥር አሁንም እዛው ነው ያለው። ወደፊትም ብልጽግናም ይሁን የሌላ የትግራይን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ያገለለ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ መፍጠር አይችልም፤ የሚያስብ ካለም ስሕተት ነው። የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ የመሳተፍ ሙሉ ብቃትና መብት አለው። ይህንን አብረን ስለኖርን ወደፊትም አብረን ልንሠራ ስለምንችልና ስለምናስብ እንደተቃዋሚ ብናስብ ኖሮ የብልጽግና ፓርቲ የፈለገውን ሰው ካቢኔ ማደራጀት ይችላል። በዚህ ጥርጣሬ አይግባችሁ።

“ፓርላማው መንግሥት ማድረግ አይችልም ካለ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠርቶ ማውረድ ይችላል። ይሄ መብታችሁ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከመረጣችሁ በኋላ የራሱን ካቢኔ መመሥረት ሕገመንግሥታዊ ሥልጣኑ ነው። እዚህ ጋር መዛባት አያስፈልግም ማለት ነው” የሚል ምላሽ ነው።

ሕወሓትን የመግፋት ሥራ አልተደረገም፤ አይደረግምም የሚል ሐሳባቸውን የሰነዘሩት ዶ/ር ዐቢይ፤ ምናልባት ከሥራ ጋር በተያያዘ ማስተካከያዎች ተደርገው ይኾናል እንጂ በጥቅል መወሰድ እንደሌለበት አክለዋል።

በኢትዮጵያ ነፃና ገለልተኛ ከኤሌክትሪክ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ዘንድሮ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ቢኖርም፤ ወደ ፈረቃ ያልገባነው ተጨማሪ ግድብ ገንብተን ተገንብቶ ያለመኾኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከማኔጅመንት ብቃት ጋር በተያያዘ ነው ብለዋል።

የግል ዘርፉን በተመለከተ ደግሞ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ ከለውጡ በፊት ከነበረው የተሻለ ነው፤ የፋይናንስ ሴክተሩ በታሪኩ አይቶት የማያውቀው ድጋፍ ከመንግሥት ተደርጎለታል፤ በዚህም ከፍተኛ መነቃቃት ስለመታየቱ አስረድተዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በተመለከተ ከተናገሩት ውስጥ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሐሳብ አመንጪ መኾን ያለባቸው መኾኑን ገልጸው “ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዋና ፍላጐታቸው መቃወም ከኾነል፤ መንግሥት መኾን አይችሉም” ብለዋል።

የምርጫና የምርጫ ቦርድ ጉዳይም በዕለቱ ከተነሡ ጥያቄዎች መካከል ይገኙበታል። በዚህ ማብራሪያቸው ውስጥ በምርጫ ቦርድ አሠራር ላይ እርሳቸው ምንም ነገር ያለማድረጋቸውንና የምርጫ ቦርድ የሕግ ማሻሻያ ሲያደርግ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ካቢኔ ሳያየው ማሻሻያ ረቂቁን ቀጥታ ለፓርላማው አቅርቦ ማስወሰኑን ጠቅሰዋል። “እኔ እንደማንኛውም ዜጋ ክርክሩን በሚዲያ ከመሥማት ውጭ ደንቡ ተልኮልኝ በካቢኔ ተወያይቼ ይህንን ረቂቅ እንደሌላው አዋጅ አጽድቁ አላልኳችሁም። ምርጫ ቦርድን እንደ መንግሥት በቢሮ በበጀትና በሚያስፈልግ ነገር የጠየቀውን አግዘናል” በማለት፤ መንግሥት በምርጫ ቦርድ አሠራር ላይ ጣልቃ ያለመግባቱን የሚያሳይ ምላሽ ሠጥተዋል። በዚህ ጉዳይ መንግሥት እጁን ያለማስገባቱን ያከሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ስለዚህ ሕጉ ይሻሻል ካላችሁ ይቀጥልም ካላችሁ ትችላላችሁ፤ እኛ ግን ምንም ሚና አልነበረንም በማለት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሌለው ሥራ እየሠራ መኾኑን አመላክተዋል። የምርጫውን ጊዜ በተመለከተ ግን “የምርጫ ቦርድ መንግሥት ከመመሥረቱ አንድ ወር ቀድሞ ምርጫ መፈጸም አለበት፤ ያ ጊዜ ግንቦት ሊሆን ይችላል። ሰኔ ወይም ሐምሌ ወይም ነኀሴ ሊሆን ይችላል። ከዚያ ጊዜ በኋላ ግን ሊሆን አይችልም። አንድ ወር ቀድሞ መፈጸም አለበት። ይሄ ሕገ መንግሥታዊ ነው። ምርጫ ግንቦት ወይም ሰኔ ነው የሚለውን ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተነጋግሮ የሚወስነው ይሆናል። ትክክለኛውን ቁርጥ ያለ ውሳኔ የተወሰነ አይመስለኝም” ብለዋል። አያይዘውም፤ “በትክክል ጊዜውን አላውቅም። እሱን ምርጫ ቦርድን ብታነጋግሩ መልካም ይሆናል” የሚል ምላሽ ሠጥተዋል።

ምርጫውን ለማድረግ ሰላም የለም ከሚል አንደምታ ለተነሳው ጥያቄ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እርግጠኛ ነኝ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ጊዜ ሰላም ይመጣል ብሎ ጋራንቲ መሥጠት የሚችል አንድ ግለሰብ የለም። ስድስት ወር፣ ዓመት ወይም ሁለት ዓመት ይሁን ከዚያም በኋላ የተሟላ ሰላም ይፈጠራል ብሎ የሚያስብ ምንም ፋውንዴሽን የለም። ምርጫው ትናንትም ቢደረግ ዛሬ መልኩ ይለያያል እንጂ ችግር አለ። ይህ ችግር የሚፈታው ምክር ቤቱ ምርጫ ቦርድን በማገዝ፤ ፓርቲዎች በፈረሙት ሰነድ ልክ ለዲሲፕሊን ተገዝተው ተባባሪ በመኾን፤ ዜጐች ምርጫው ድምፅ ማሰሚያ እንጂ መጋደያ እንዳይኾን ጥበቃ በማድረግል መንግሥት አስፈላጊውን ሎጂስቲክስ፣ ጥበቃና ድጋፍ በማድረግል ሁሉም ባለድርሻ ከተባበረ ምርጫው ቻሌንጂንግ ቢሆንም፤ ሊሳካ ይችላል” ብለዋል። (ኢዛ)

የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የመንግሥት ጥበቃ መነሳት

ከለውጡ ወዲህ ወደ አገር እንዲገቡ ጥሪ ተደርጐላቸው ለገቡ የፖለቲካ መሪዎች መንግሥት ጥበቃ ሲያደርግ መቆየቱ በተደጋጋሚ ተነግሯል። በመንግሥት ጥበቃ ሲደረግላቸው ከቆዩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የኦነጉ አቶ ዳውድ ኢብሳ ይገኙበታል።

አቶ ጃዋር መሐመድም በዚህ እድል ተጠቃሚ በመኾን ጥበቃ ሲደረግለት ነበር። ከሰሞኑ የወጡ መረጃዎች ግን እነዚህ ጥበቃ ሲደረግላቸው የቆዩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ግለሰቦች መንግሥት ሲያደርግላቸው የነበረውን ጥበቃ ማንሳቱን አሳውቋል።

በፌዴራል ፖሊስ በኩል የተላለፈው ይህ መልእክት ከተነገረ በኋላ አቶ ጃዋር መሐመድ በራሱ ፌስቡክ ገጹ ላይ ጥበቃው ስለመነሣቱ ገልጿል።

ከጥቂት ወራት በፊት አቶ ጃዋር ይደረግልኝ የነበረ ጥበቃ ተነስቷል በሚል ባሠራጨውና “ተከብቤአለሁ” የሚል ይዘት ያለው መልእክት በፌስቡክ ማሠራጨቱን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ብጥብጥ 86 የሚኾኑ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱና ቤተ እምነቶች የተቃጠሉ፣ እንዲሁም ለብዙዎች መፈናቀልና የአካል ጉዳት መንስኤ ኾኖ እንደነበር አይዘነጋም።

ከሰሞኑ ግን አቶ ጃዋር መንግሥት ሲያደርግለት የነበረውን ጥበቃ መነሣቱን ተከትሎ ያስተላለፈው መልእክት ጥበቃው መቅረቱን አረጋግጧል። (ኢዛ)

የአዲስ አበባና የቴፒ ግጭት

ኢትዮጵያ ውስጥ እዚህም እዚያ ተፈጠሩ በሚባሉ ግጭቶች የሰው ሕይወት ጠፋ፣ ንብረት ወደመ የሚሉ ዜናዎች ተደጋግመው ይሰማሉ። አንዱ ጋር ተረጋጋ ሲባል፤ በሌላ ሁኔታ ሌላ ቦታ ችግር ተፈጠረ ይባልና በኢትዮጵያ መኾን የማይገባው ነገር ሲሆን ይሰማል። ባሳለፍነው ሳምንትም በደቡብ ክልል በቴፒ ከተማ ተፈጠረ በተባለ ግጭት ከስምንት በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ20 በላይ ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል። ሳምንቱን በውጥረት ያሳለፈችው ቴፒ አሁንም የተረጋጋች እንዳልኾነች መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የግጭቱ መነሻ በገለልተኛ ወገን ባይጣራም፤ በግጭቱ መነሻ ዙሪያ የተለያዩ ምክንያቶች እየተሠጡ ይገኛሉ። ባሳለፍነው ሳምንት ለተፈጠረው ግጭት መነሻ ተደርገው ከሚጠቆሙት ውስጥ የጸጥታ ኃይሎች በሕግ የሚፈለጉ ናቸው የተባሉትን ግለሰቦች ለመያዝ በተደረገ እንቅስቃሴ፤ በሕግ የሚፈለጉ ናቸው በተባሉትና በታጣቂዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባትና ግጭት ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ኾኗል የሚለው አንዱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ለዓመታት የቆየ ጥያቄ መልስ ባማግኘቱ የተፈጠረው ግጭት መነሻ መኾኑና ለተከሰተው የሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እንደኾነ የሚጠቅሱ አሉ። የአካባቢው ኃይል ያልተገባ ተግባር በመፈጸሙ በተፈጠረ ተቃውሞ ግጭቱ ሰፍቷል ብለው የሚገልጹም አሉ። በቤንች ሸኮ ዞኖች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች የመዋቅር አደረጃጀት ጥያቄን ወደ ግጭት ለመውሰድ ፍላጐት ያላቸውና በተደራጁ ቡድኖች የተፈጠረ እንደኾነም ይነገራል። የደቡብ ክልላዊ መንግሥት ወደዚህ ያደላ አመለካከት እንዳለው ይነገራል።

የቴፒ ከተማ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በአካባቢው በተነሳው የአደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ግጭቶች የተስተናገደባት ከተማ ኾናለች። የጸጥታ ሥጋት እያየለባት የመጣችው ቴፒ፤ ባሳለፍነው ሳምንት ግጭት የከተማዋና የአካባቢዋ ነዋሪዎች እንቅስቃሴ መገታትና የንግድና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ተስተጓጉለዋል። አካባቢው በኮማንድፖስት ሥር ያለ ቢሆንም፤ የጸጥታ ችግሩ ሲደጋገም ታይቷል። በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መኾኑንና ለግጭቱ መንስኤ ናቸው የተባሉትን በሕግ ይጠይቃሉ ተብሏል።

ይህ በእንግዲህ እንዳለ በአካባቢው የተፈጠረውን ችግር ለማጣራትና መረጋጋትን ለመፍጠር የደቡብ ክልል የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ነው ተብሏል። እንደ ቴፒ ሁሉ በአዲስ አበባ በ22 አካባቢ ከአንድ የቤተክርስቲያን ግንባታ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ግጭት የሦስት ሰዎች ሕይወት አልፏል። የአካል ጉዳት ያጋጠማቸውም አሉ። የታሰሩም አሉ።

በታጠቁ ኃይሎች የተፈጸመው ይህ ድርጊት በእጅጉ የተወገዘ ሲሆን፣ ሕገወጥ ግንባታ እንኳን ቢከሰት በሌሊት የሰው ሕይወት ባሳጣ መልኩ መፈጸሙ ተቃውሞ አስነስቷል። ይህ ድንገት የኾነ ነገር በከተማ አስተዳደሩ በኩል ድንጋጤ የፈጠረ ሲሆን፤ ይህንን ድርጊት እንዲፈጸም ምክንያት የኾኑ አካላትን ለሕግ እናቀርባለን ተብሏል። ቤተክህነትም የችግሩ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቃለች። ግጭቱ በተደረገ ማግስት ከኢንጅነር ታከለ ኡማ እንደተገለጸው ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፤ ማንነታቸው ግን አልተገለጸም። (ኢዛ)

የህዳሴ ግድብና ሰሞናዊው ጉዳይ

በቀዳሚው ሳምንት ትኩረት ከተሠጣቸው አገራዊ ጉዳዮች አንዱ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሦስቱ አገራት (ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን) በዋሽንግተን ዲሲ ያደረጉት ውይይት ነው። ይህ ውይይት የመጨረሸ ነው ተብሎ ይጠበቅ የነበረ በመኾኑ ምን ተገኘ? የሚለው ጥያቄ ላይ ምላሽ ይጠበቅ ነበር። አንዳንድ ወገኖች ከድርድሩ የተገኘ መልካም የሚባል ውጤት የመኖሩን ያህል በፍጹም መግባባት ያልተደረሰባቸው ነጥቦች እንደነበሩም ይጠቅሳሉ።

ከዋሽንግተን ውይይት በኋላ ኢትዮጵያን በመወከል ዋነኛ ተደራዳሪ ከኾኑት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መካከል የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂንየር ስለሺ በቀለ በሠጡት መግለጫ፤ የኢትዮጵያን በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብት በዘላቂነት በማያስጠበቅ ሁኔታ አንድም ቃል በስምምነት ውስጥ ቢካተት የማትፈርም መኾኑን ነው።

በግድቡ ዙሪያ በሚደረገው ስምምነት ላይ የኢትዮጵያን በዓባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም መብት በዘላቂነት በማያስጠብቅ ሁኔታ ካለ ፈጽሞ ኢትዮጵያ የማትስማማበት እንደሚኾን በመጠቆም፤ እየተደረገ ካለው ድርድር የአገራችንን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ እየተካሔደ ስለመኾኑም ገልጸዋል።

አሜሪካና የዓለም በንክ በታዛቢነት በተገኙበት በአራት የተለያዩ ዶክመንቶች ላይ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር ድርድር አካሒደው ውጤታማ ሥራ ስለመከናወናቸው የገለጹት ዶ/ር ኢንጂንየር ስለሺ በዋናነት የግድቡ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅን በሚመለከተው ነጥብ ላይ አሁንም ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በቴክኒካዊ፣ በሕጋዊ፣ በግጭት አፈታትና በትብብር ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በአጭር ጊዜ መፈራረም እንችላለን የሚል እምነት እንዳላቸው የሠጡት መግለጫ ያመለክታል።

በዚህ ጉዳይ ላይ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ ጥቅሟን አሳልፎ የሠጠ ስምምነት ልታደርግ ነው የሚለው መረጃ ፈጽሞ ስሕተት ስለመኾኑም ሳይገልጹ አላለፉም።

ከሰሞኑ ግድቡን በተመለከተ ከተሠጡ ማብራሪያዎች መረዳት እንደተቻለው፤ የህዳሴ ግድብ ተርባይነሮች ወደ 13 እንዲቀንሱ መደረጉንና ይህም 5 ሺሕ 150 ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚያመነጭ መገለጹ አንዱ ነው።

ከግንባታው መዘግየት ጋር በተየያዘ የአሌክትሮ መካኒካል ሥራው ለሜቴክ መሠጠቱ አገሪቱን ዋጋ ስለማስከፈሉ፤ እንዲሁም ሜቴክ በጊዜው ባለመሥራቱ የፈጠረው ችግር የግንባታ ወጪ እንዲጨምር ያደረገ ሲሆን፤ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁም የኤሌክትሪክ ኃይልን ወደ ውጭ በመላክ ይገኝ የነበረ እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር እንደታጣም ተጠቁሟል። (ኢዛ)

የኮሮና ቫይረስ ሥጋት በኢትዮጵያ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዕለቱ ስሙ የሚነሳውና ስለአደገኝነቱም የሚወሳ ቃል ቢኖር “ኮሮና” የሚለው ነው። ዛሬ የዓለማችን ቁጥር አንድ ሥጋት ወደመኾን የተሸጋገረው የኮሮና ቫይረስ በቻይና ሳይወሰን የመዳረሻ አገሮቹን ቁጥር እየጨመረ ነው። የዓለም የጤና ድርጅትም ኮሮና የዓለም ሥጋት ስለመኾኑ የማወጁ ምክንያትም፤ የወረርሽኙን የመሠራጨት ፍጠነትና ገዳይነት ከግምት አስገብቶ ነው። እስከ ሳምንቱ አጋማሽ ድረስ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በሳምንት ልዩነት በእጥፍ የመጨመር ሁኔታ እየታየበት ነው።

በቻይና እስከ ሐሙስ ጥር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በቫይረሱ ተጠቂ ሰዎች ቁጥር 31 ሺሕ ደርሷል። ይህ ቁጥር ከአንድ ሳምንት በፊት 14 ሺሕ እንደነበር የተጠቀሰ ሲሆን፤ ይህም በሳምንት ልዩነት ከእጥፍ በላይ መኾኑን ነው። በአሁኑ ወቅት ከ25 አገሮች ቫይረሱ ታይቶባቸዋል።

ይህ መረጃ የቫይረሱ በአጭር ጊዜ በፍጥነት እየተዛመተ መኾኑን የሚያመለክት ሲሆን፤ አገራትም ይህንን ቫይረስ ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። በኢትዮጵያም ቫይረሱን ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ቢሆንም፤ የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገባ ይችላል የሚል ሥጋት እየጨመረ መጥቷል። በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚየደርገውን በረራ ያለማቆሙ ሥጋቱን ከፍ ማድረጉ አልቀረም። በአንፃሩ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ጋር ተያይዞ በቫይረሱ የተጠረጠሩና በማቆያ ማዕከል እንዲቀመጡ የሚደረጉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር ከፍ እያለ መምጣቱ ደግሞ ኢትዮጵያን በሥጋት ቀለበት ውስጥ እንድትገባ ያደርጋታል።

በወቅታዊው የኮረና ቫይረስና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በተሠጠ ሳምንታዊ መግለጫ ላይ፤ እስካሁን 29 ጥቆማዎች ለኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ደርሰውታል። በጥቆማው መሠረት በ29ኙ ላይ በተደረገ ማጣራት 14ቱ በቫይረሱ የመያዝ ምልክት በማሳየታቸውቱ በቫይረሱ የመያዝ ምልክት በማሳየታቸው ተለይተው ወደ ማቆያ ሥፍራ እንዲገቡ መደረጉን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል። እስካሁን ወደ ደቡብ አፍሪካ የ14ቱም ተጠርጣሪዎች የደም ናሙናዎች መላካቸውንና ከዚህ ውስጥ 11ዱ ከቫይረሱ ነፃ መኾናቸው ተረጋግጧል ተብሏል። የሦስቱ ተጨማሪ ናሙናዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ የምርመራው ውጤት እየተጠበቀ ነው ተብሏል። ከመረጃው መገንዘብ እንደሚቻለው ከሰሞኑ ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ ተጠርጣሪ ኾነው በአግሎ ማቆያ ማዕከሉ እንዲገቡ ከተደረጉት ስድስቱ ውስጥ አንዱ ቻይናዊ ቀሪዎቹ ኢትዮጵያዊ መኾናቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፈው ቅዳሜ ጥር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳስታወቀው ደግሞ፤ የላቦራቶሪ ምርመራውን በተቋሙ ማድረግ ጀምሯል። የቀሪዎቹ ሦስቱ ተጠርጣሪዎች ናሙና በተቋሙ ምርመራ ተደርጎላቸው ነፃ መኾናቸውንም ለሕዝብ ይፋ ባደረገው መረጃ ላይ ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ የምርመራ ሥራዋን ስለማጠናከሯ የተገለጸ ሲሆን፤ ቁጥጥሩን ለማጥበቅ የተለያዩ አዳዲስ አሠራሮችን እንዲተገበሩ እያደረገች ነው።

በተለይ ከቻይና “ዉሃን” ከተማ የሚመጡ ማናቸውም መንገደኞች ወደ ለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲገቡ መወሰኑ አንዱ ነው።

ከዚህ ውሳኔ ሌላ ከየትኛውም የቻይና ግዛት የሚመጡ መንገደኞች አዲስ አበባ ሲደርሱ፤ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከሌሎች መንገደኞች ጋር ሳይቀላቀሉ የሙቀት ምርመራ የሚደረግላቸው እንደኾነም ተጠቅሷል። እንዲህ ያለው አሠራረ ከቻይና የሚመጡ መንገደኞች ብቻ የሚስተናገዱበት ልዩ የኢሚግሬሽን መስኮት እንዲሰናዳ በማድረግ ምርመራውን በማጥበቅ ቫይረሱን መከላከል እየተሠራ ነው።

መንግሥት ካለው ሥጋት አንፃር እንዲህ ባለው መልኩ ቫይረሱን ለመቆጣጠር እየሠራ ቢሆንም፤ በሌላ በኩል በሳምንት 35 በረራዎችን ወደ ቻይና የሚያደርገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን አላቋርጥም ማለቱ ግን አነጋጋሪ ኾኖ ቀጥሏል። አየር መንገዱ በዚህ ሳምንት በይፋ እንዳስታወቀውም በረራ ማቆሙ መፍትሔ ያለመኾኑን ነው። ስለዚህ ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎች ጥንቃቄ ታክሎባቸው እንደሚቀጥሉ አስታውቋል። ይህ የአየር መንገዱ ውሳኔ ግን ብዙዎችን እያሠጋ ነው። በተለይ ከቫይረሱ ፈጣን የመዛመት ባሕርይ ጋር ተያይዞ በአንድ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢገባ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት እንዲህ በቀላሉ የሚመለስ አይሆንም በሚል፤ የሚያቀርቡት ሙግት ግን ሰሚ ያገኘ አይመስልም። በሌላ በኩል ደግሞ አፍሪካውያን በረራዎችን ማቆማቸው ተገቢ እንዳልኾነ ለአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ አዲስ አበባ የተገኙ የሕብረቱ አባላት መግለጻቸው ደግሞ፤ ጉዳዩ እንዴት ታይቶ ይሆን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

ሐሙስ ጥር 28 ቀን በወጣ መረጃ ከ31 ሺሕ 500 በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 15 በመቶ ወይም 4825 ሰዎች አስጊ ሁኔታ ላይ ናቸው። በመረጃው መሠረት እስከ ሐሙስ ድረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 638 ደርሷል። ያገገሙት ደግሞ 1,652 እንደኾነ ተገልጿል።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሌላው ዜና ኾኖ በሳምንቱ ውስጥ የተሠራጨ መረጃ፤ በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወደ አገራቸው ይመለሱ ዘንድ የተማሪዎቹ ወላጆች ለመንግሥት አቤት ማለታቸው ነው። በቻይና በተለይም በዉሃን ግዛት ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወላጆች፤ መንግሥት ልጆቻቸውን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የጠየቁት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአካል ተገኝተው ነው። የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ አሳሳቢነት የዓለም መኾን ከጀመረ ሰነባበተ። የዓለም ሁለተኛዋ የኢኮኖሚ ባለቤት የኾነችው ቻይና የቫይረሱ መነሻ መኾኗ ብቻ ሳይሆን፤ ከቫይረሱ ተጠቂዎች 99 በመቶ የሚኾኑት በአገሪቷ መኾናቸው ነው። (ኢዛ)

ሰሞናዊ ሹመትና አነጋጋሪው ጉዳይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ላይ አምስት ሹመቶችን ሠጥተዋል። በዚህ ሹመት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሠጡት ሹመት መሠረት አቶ መስፍን መላኩን በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አርገው ሾመዋል።

ከዚህ ሹመት ባሻገር ለኢንፎርማሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋናና ምክትል ዳይሬክተር በመኾን የሚያገለግሉ አዲስ ተሿሚዎችን ሰይመዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞናዊ ሹመት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ኾነው እንዲያገለግሉ የተሾሙት ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ናቸው። ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኾነው የተሾሙት ደግሞ አቶ ከፍያለው ተፈራ ናቸው። ሌሎች ሁለቱ ደግሞ አቶ ወርቁ ጋቸና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ምርምርና ልማት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ ዘላለም መንግሥቴ ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽን ምክትል ኮምሽነር ኾነው ተሹመዋል።

የሰሞኑ ሹመት ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገው፤ በተለይ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ከለውጡ ወዲህ አራት የሚኾኑ ዳይሬክተሮች የተፈራረቁበት መኾኑ ነው።

ከለውጡ ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋና ዳይሬክተርነት ተሹመው ከነበሩት ውስጥ አሁን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ይጠቀሳሉ። ከዚያም በኋላ ወይዘሮ ኢፍራህ አሊ በዋና ዳይሬክተርነት ያገለገሉ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ዶክተር ሹመቴ ኃላፊነቱን እንዲወስዱ ተደርጓል። ዶክተር ዐቢይ ይህንን ሹመት ከመሥጠታቸው ቀደም ብሎ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አፍራህ ወደ አዲስ አበባ አስተዳደር እንዲዘዋወሩ ተደርጓል። ከአንድ ወር በፊት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳዲስ አመራሮችን ሲሰይም ወ/ሮ አፍራህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ በመኾን መሾማቸው ይታወሳል። ወይዘሮ ኢፍራህ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊነቱን የተረከቡት ከታዋቂው የጥበብ ባለሙያ ነብዩ ባዬ ነበር። ከሰሞኑ ሹመት ጋር ተያይዞ ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ኾነው የተሰየሙት አቶ ከፍያለው ተፈራ ከለውጡ ወዲህ አራተኛው ሹመታቸው መኾኑ ነው።

የሰሞኑን ሹመት ከማግኘታቸው በፊት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ነበሩ። አዲስ ለተቋቋመው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር በመኾን የተሾሙት አቶ ወርቁ ጋቻና ይህንን ኃላፊነት ከመረከባቸው ቀደም ብሎ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኾነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። እነዚህ ተሿሚዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነት ላይ መዘዋወራቸው ግን ለምን?

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመኾን የተሰየሙት ዶ/ር ሹመቴ፤ በሥራው ዓለም በቀድሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአካዳሚክና ምርምር ተቋማት ዳይሬክተር ጄኔራል ኾነው ሠርተዋል። በዲላ ዩኒቨርሲቲ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ኾነውም አገልግለዋል። ዶክተር ሹመቴ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመኾን ያገለገሉ መኾናቸው ይጠቀሳል። (ኢዛ)

የገናሌ ዳዋ 3 ኃይል ማመንጫ ምረቃና ቀጣዩ ግድብ

የገናሌ ዳዋ 3 የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ከመጠናቀቂያ ጊዜው ከሰባት ዓመት ዘግይቶ የተመረቀ ፕሮጀክት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ላይ የተመረቀው ይህ የኃይል ማመንጫ፤ የተገነባው በኦሮሚያ ክልል በጉጂና ባሌ ዞኖች መካከል ሲሆን፤ አጠቃላይ የግንባታ ወጪው 461 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው።

ከጠቅላላ የፕሮጀክቱ ወጪ ውስጥ 60 በመቶ የሚኾነው ከቻይና ኤክዚም ባንክ በብድር የተገኘ ሲሆን፤ ቀሪው 40 በመቶ የሚኾነው ወጪ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሸፈነ ነው። ፕሮጀክቱ በአራት ዓመት እንዲጠናቀቅ ስምምነት ተፈርሞ የነበረው በ2003 ዓ.ም. ነበር። ኾኖም በኮንስትራክሽን ውሉ መሠረት ግንባታው በተያዘለት ጊዜ አልተጠናቀቀም። ከመጠናቀቂያ ጊዜው ሰባት ዓመታት ዘግይቶ ነው የተጠናቀቀው። ዓመታትን ተሻግረው ከሔዱ ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ አድርጐታል።

ለገናሌ ዳዋ 3 የግንባታ ፕሮጀክት መዘግየት የተለያዩ ምክንያቶች ቢጠቀሱም፤ በዋናነት ግን የግንባታው አካል የኾነ የሁለት ኪሎ ሜትር ዋሻ ቁፋሮ በሚካሔድበት ጊዜ ባጋጠሙ አለቶች፤ እንዲሁም ከካሳ አከፋፈል ጋር በነበረ ችግር ግንባታው ሊጓተት ችሏል።

ዶ/ር ዐቢይ ከግድቡ ምረቃ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በፓርላማ ተገኝተው፤ ገናሌ ዳዋ ከለውጡ በፊት ነው የግድቡ ሥራ ያለቀው፤ ነገር ግን ውኃ መያዝ የሚቻልበት ስፍራ ላይ ያሉ አርሶ አደሮች ጋር መስማማት ባለመቻሉ ሁለት ዓመት ያለሥራ ቆይቷል ብለዋል። አሁን ግን ከእነሱ ጋር ተነጋግረን ተገቢውንካሳ ከፍለን ለምረቃ አዘጋጅተነዋል ማለታቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ይህንን በተናገሩ ማግስት በግድቡ በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ፤ “የጀመርነውን ጨርሰን ሪባን እንቆርጣለን እንጂ፤ ተስፋ አንቆርጥም ብለን ነበር፤ የዛሬው የገናሌ ዳዋ 3 የውኃ ኃይል ማመንጫ ምረቃ የዚህ አንድ ማሳያ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ግድቡ ከኃይል ማመንጨት በተጨማሪ በመስኖ ልማት በርካቶችን የመመገብ አቅም አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀጣይ ትኩረታቸው የገናሌ ዳዋ ስድስት የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብን እንዴት መጀመርና መጨረስ አለብን የሚለው ላይ መኾን አለበት ብለዋል።

እንደጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ የገናሌ ዳዋ ስድስት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ወጪን የሚጠይቅ ነው። በግድቡ ልማት ላይ በርካታ የውጭ ባለሀብቶች ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን፤ መንግሥት ግን ከኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ጋር የማልማት ፍላጎት እንዳለው በዚሁ ምረቃ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች ከመንግሥት ጋር በመኾን በሽርክና የገናሌ ዳዋ ስድስት የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብን እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ 4 ሺሕ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ ግድቦች ያሉት ሲሆን፣ የህዳሴ ግድብና ኮይሻን ጨምሮ ከሌሎች ታዳሽ ኃይሎች 7 ሺሕ 300 ሜጋ ዋት ለማምረት እየሠራች መኾኑን በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የገናሌ ዳዋ 3 ውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብ 254 ሜጋዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ነው። የገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ 2 ነጥብ 57 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የመያዝ አቅምም እንዳለውም ተገልጿል። (ኢዛ)

በቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የመጀመሪያው የመድሃኒት ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

በኢትዮጵያ ለፋርማሲዩቲካል ታስቦ በተገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የመጀመሪያ የኾነው የመድሃኒት ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት የፋብሪካው ግንባታ የመሠረት ድንጋይ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ተጥሏል። ይህ ፋብሪካ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ነው።

ግንባታውን የሚያካሔደው አፍሪኪዩር ፋርማሲዩቲካል ማኑፋክቸሪንግ የተባለ ኩባንያ ሲሆን፤ ይህም በፓርኩ የመጀመሪያው የመድሃኒት ማምረቻ ፋብሪካ ይኾናል። አጠቃላይ የግንባታ ወጪው በ10 ሚሊዮን ዶላር እንደኾነም የመሠረት ድንጋዩ በተጣለበት ወቅት ተገልጿል።

ፋብሪካው በአገር ውስጥና በውጭ ባለሀብቶች ጥምረት የሚገነባና ምርት ሲጀምር ለ109 ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር መኾኑን ታውቋል። የሥራ እድል ከሚፈጠርላቸው ዜጎች 95 በመቶ የሚኾኑት ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ የተቀሩት ደግሞ የውጭ ዜጎች ይኾናሉ።

በሒደት የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያውያንን በማሠልጠን የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ኢትዮጵያውያን በሁሉም ደረጃ ማስተዳደር የሚችሉበት ፕሮግራም መቀረጹን ታውቋል። (ኢዛ)

የዳያስፖራ ማኅበር የተለያየ ፓስፖርት የያዛችሁ አገር አትበጥብጡ አለ

ባሳለፍነው ሳምንት ለየት ብሎ የሚታይ መግለጫ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ማኅበር ተሰምቷል። የማኅበሩ መሪዎች ሰሞኑን ይካሔዳል ተብሎ የሚጠበቀውን የሰላም ኮንፈረንስ አስመልክቶ በሠጡት መግለጫ ላይ፤ የተለያየ ፓስፖርት ይዘው አገር የሚበጠብጡ ይታቀቡ ብለዋል። ፖለቲከኛም ይሁን አክቲቪስት፤ የሁለት አገር ፓስፖርት ይዞ አገር በሚበጠብጡ ተግባራት ላይ መሳተፋቸውን ያቆሙ በማለትም አመልክተዋል።

በተለይ በውጭ አገሮች ፓስፖርት እየኖሩ አገር መበጥበጥ እንደማይቻል ጭምር የጠቀሱት የማኅበሩ መሪዎች፤ በአገሪቷ ለሚታዩ አንዳንድ አላስፈላጊ ግጭቶች ምክንያት እየኾኑ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሕግ መቅረብ እንደሚኖርባቸው በዚሁ መግለጫቸው አመልክተዋል።

ማኅበሩ የካቲት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ለማካሔድ ያቀደው ኮንፍረንስ፤ ዳያስፖራው በሰላም ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲኾን የሚመክርበት ጭምር እንደኾነ ተገልጿል።

መንግሥት ለሚያደርገው ሰላም የማስከበር ሥራ ማኅበሩ መንግሥትን ከጎኑ ኾኖ የሚደገፍ መኾኑንም አመራሮች ገልጸዋል። (ኢዛ)

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰናዳው ረቂቅ አዋጅ አሁንም እያነጋገረ ነው

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበው ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀት ከጀመረ ሰነባብቷል። አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክርና በሕዝቦች መካከል መከባበርንና መቻቻልን፣ የጥላቻ ንግግሮችንና ሐሰተኛ መረጃዎች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ ለመቀነስና ለመቆጣጠር ታልሞ የተዘጋጀው ይህ ረቂቅ፤ ባሳለፍነው ሳምንት ፓርላማ ቀርቦ ውይይት ተደርጐበታል።

በዚህ ረቂቅ ላይ በፓርላማ ይፋዊ ውይይት ሲደረግ የሰሞኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በዚህ ረቂቅ አዋጅ ከፓርላማው ውጭ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን፤ የዚህ ረቂቅ ሕግ መሰናዳት የመናገር መብትን የሚጋፉ መኾኑን በመግለጽ፤ አስፈላጊ አለመኾኑን ሲሞግቱ ቆይተዋል። በሰሞኑ የፓርላማ ውይይቱ ላይም በሕገመንግሥትና በፕሬስ አዋጁ ላይ የተቀመጡ ሕግጋቶች እያሉ፤ ይህንን አዋጅ ማሰናዳት ተገቢ ያለመኾኑን የገለጹም አሉ።

ረቂቅ አዋጁ በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጠው የመናገር መብት ጋር ይቃረናል በሚል ጭምር ሐሳብ የተሰነዘረ ሲሆን፤ በሕገ መንግሥቱ ላይ በመናገር መብት ላይ የተወሰነ ገደብ የተቀመጠ ቢሆንም፤ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃን ማሠራጨት የሚሉት ከተቀመጡት ገደቦች ውጪ ናቸው የሚለውም ይህ ረቂቅ አዋጁ ከዚህ ቀደም ከወጡት የኮምፒውተርና የብሮድካስት አዋጆች ምን የተለየ ነገር አለው? የሚዲያ ተቋማት ይህ የሐሰት መረጃ ነው፤ ይህ የጥላቻ ንግግር ነው፤ እያሉ ወደ ሳንሱር ሥራ እንዲገቡ አያደርጋቸውም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች የቀረቡበት እንደነበር ውይይቱን አስመልክቶ ፓርላማው ያሠራጨው መረጃ ያስረዳል።

በእነዚህና በውይይቱ ላይ ለተነሱ አስተያየትና ጥያቄዎች ላይ በወቅቱ በውይይቱ ላይ የነበሩት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተወካይ ምላሽ መሥጠታቸውን ያመለክታል። ምላሻቸውም ረቂቅ አዋጁ በሕገ መንግሥቱ ላይ ከተቀመጠው የመናገር መብት ጋር እንደማይቃረን፣ በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጡት ገደቦች ውስጥም አንዱ ምክንያት ሰብዓዊ ክብርን መጠበቅ ሲሆን፤ የጥላቻ ንግግር ሰብዓዊ ክብርን የሚነካ ዋነኛው በመኾኑ ከተቀመጠው ገደብ ጋር የሚገናኝ መኾኑን የሚያመለክት ምላሽ ሠጥተዋል ይላል።

ረቂቅ አዋጁ ከዚህ በፊት ከወጡት አዋጆች በምን እንደሚለይ በሠጡት ማብራሪያም፤ ረቂቅ አዋጁን በዚህ መልኩ ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት በተበጣጠሰ ሁኔታ ሳይሆን አንድ ቦታ ሰብሰብ ብሎ ማስቀመጥ በማስፈለጉና ከዚህ በፊት ያልተካተቱ ሐሳቦችን ለማካተት እንደኾነ ስለመጠቆማቸው በዚህ ውይይት ዙሪያ ፓርላማው ያሰፈረው መረጃ ያመለክታል። እንዲህ ያለውን አዋጅ ማዘጋጀት ሚዲያዎችን ወደ ሳንሱር ሥራ እንዲገቡ ሊያደርጋቸው ይችላል በሚለው ጥያቄና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር ይችላል ለተባው ሥጋ፤ት የሳንሱርና አርትኦት ሥራዎች የሚለያዩ መኾናቸውን ጠቁመው፤ ሚዲያዎች አንድን መረጃ ከማስተላለፋቸው በፊት የአርትኦት ሥራ መሥራት እንዳለባቸውና ይህም የተለመደ አሠራር መኾኑን ጠቁመው፤ ስለኾነም መረጃዎች እውነት ስለመኾናቸው ማጣራት የሳንሱር ሥራ ነው ሊያስብለው እንደማይችል አብራርተዋል ተብሏል። የጥላቻ ንግግር እርስ በርስ ለማጋጨትና ዘር ለማጥፋት እንደማሟሟቂያ ኾኖ የሚያገለግል በመኾኑ፤ ይህ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ እንዲህ ያሉትን መሰል ችግሮችን ከመመከቱም በላይ አገራዊ አንድነትን የማያጠናክርና በሕዝቦች መካከል መከባበርንና መቻቻልን የሚያሰፍን መኾኑንም ነው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተወካዩ ያብራሩት።

በዕለቱ በፓርላማው የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ውይይት 10 የሚኾኑ ማሻሻያዎች ተደርገው የቀረበ መኾኑ ተገልጿል። አሁንም ግን ይህ ረቂቅ ተጨማሪ ውይይት የሚደረግበት ይኾናል። ኾኖም የዚህ አዋጅ አስፈላጊነት ላይ አሁንም ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ