የ2012 ዓ.ም. 34ኛ ሳምንት አንኳር ወሬዎች
ከሚያዝያ 19 -25 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ
የዓመቱ ሠላሳ አራተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች
ኢዛ (ከሚያዝያ 19 - 25 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ያሳለፍነው ሳምንት በአገራችን ወሳኝ የሚባሉ አገራዊ አጀንዳዎች ለምክክር የቀረቡበት ነበር ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተደራራቢ ችግሮች ከፊቷ የተደቀኑባት እንደመኾኑ መጠን፤ እነዚህን ችግሮች እከሌ ከከሌ ሳይባል በጋራ መምከርና ይህንን ችግር እንዴት እንሻገር ብሎ አጀንዳ ቀርፆ መነጋገርም ግድ ነው።
ባሳለፍነው ሳምንትም በተለይ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አስገዳጅነት የተራዘመው አገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ መንግሥት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የመከረበት አጀንዳም ዐቢይ ጉዳይ ኾኖ የሚጠቀስ ነው። በዚህ የውይይት መድረክ ላይ መንግሥት በሕግ ባለሙያዎች ተሰናድቶ የቀረበለትን የመፍትሔ ሐሳቦች ይዞ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል። ምርጫው እንዴት መደረግ ይኖርበታል? አሁን አገሪቱ የገጠማትን ችግር ለመሻገር ምን እናድርግ የሚል ቀዳሚ ጥያቄዎችን የያዘው በዚህ የውይይት መድረክ መንግሥት ምርጫውን ለማካሔድ አራት አማራጮችን ያቀረበበት ነው። በዚሁ መድረክ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የቀረቡ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድም ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውበታል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ ግን ብዙ ጉዳዮችን ያመለከተ ነበር። ከፖለቲካ እንቅስቃሴው ጋር በተያያዘ አስረግጠው ያሳሰቡዋቸውና ያስጠነቀቁባቸው ጉዳዮችም ነበሩ። በተለይ የሽግግር መንግሥት ይመሥረት ጥያቄ የማይታሰብ መኾኑን፤ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ከጠላት ጋር ኾነው የባንዳ ሥራ እየሠሩ መኾኑንም የጠቀሱበት ነበር። ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደ አሁን ተደራራቢ ችግር የገጠማት ጊዜ ያለመኖሩን አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት ዶክተር ዐቢይ፤ ከአገር ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ግን ምንም ችግር ላይ ቢኾንም መንግሥታቸው በአገር ሉዓላዊነት ላይ ፈጽሞ እንደማይደራደር ጠንከር ባሉ ቃላት ደጋግመው ገልጸዋል። ሌሎችም በርከት ያሉ ጉዳዮችንም 40 ደቂቃ በፈጀው ማብራሪያና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች በቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
ሌላው ከዚሁ ጋር ሊለያይ የሚችለው የሳምንቱ ዐበይት አጀንዳ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጣዩን ምርጫ በተመለከተ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ውሳኔ ማሳለፉ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ምክክር ባደረገበት የምክር ቤቱ ስብሰባ ዕለት፤ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ማብራሪያ የሰጡበትም ነበር።
ሥጋታቸው የአገር ጉዳይ የኮሮና ቫይረስ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል፣ ዜጐች ለመደገፍ ብሎ ኢኮኖሚውን ከበለጠ አደጋ ለመጠበቅ የኮሮና ወረርሽኝን ከተነገረበት ጊዜ ወዲህ ሰፋ ያለና ወሳኝ የሚባሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን የወሰነበት ሳምንት ነው።
በዚህ ውሳኔው በርካታ ጉዳዮች ተዳሰዋል። የግብር ቅናሽ ጨምሮ በርካታ ማሻሻያዎች የተደረጉበት ሰነድ ነው። በእነዚህ ሦስት የሳምንቱ በቀዳሚነት ሊቀመጡ የሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት የሚያደርገው የኢትዮጵያ ዛሬ ትንተና ባሻገር፤ በሳምንቱ ሊጠቀሱ ከሚችሉ ጉዳዮች ውስጥ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በሕክምና ላይ ከሚገኙት የበለጠ ያገገሙት መብለጡ የተሰማበት፣ የመመርመር አቅም በቀን 5 ሺሕ መድረሱ የሚጠቀስ ነው።
አብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ) ሕገመንግሥቱን ማሻሻያ ጊዜ አሁን ነው ብሎ ያወጣሙ መግለጫም ከሳምንቱ ጉዳዮች አንዱ ነበር። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በርከት ያሉ እርምጃዎች የተወሰዱበት ሳምንት ኾኗል።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የዓለም የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የ411 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማጽደቁ ከሰሞኑ የተሰማ መልካም ዜና ኾኗል። የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል ከሳምንቱ ዐበይት ዜናዎች የተወሰኑትን እንደሚከተለው አዘጋጅቶ አቅርብዎሎታል። እነኾ!
የጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ማብራሪያ
ለውይይቱ መነሻ የኾነው ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም አስተያየት ሰጥተውበታል፤ ጥያቄ አቅርበውበታል። ማጠቃለያውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያና ለቀረቡ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተውበታል።
እንደ ምክትል ዓቃቤ ሕጉ ማብራሪያ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በዚህ ዓመት ምርጫው መደረግ ቢኖርበትም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያም ተፅእኖ ማሳደሩ፤ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ምርጫን ማከናወን እንደማይችል በማስታወስ፤ የአገሪቱን ሕግና ወቅታዊውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት በዕለቱ አራቱን አማራጮች ለውይይት እንዲቀርቡ መደረጉን ገልጸው፤ በእነዚህ አራት አማራጮች ላይ ትንታኔ ሰጥተዋል።
በእርግጥም ኮሮናን ጨምሮ ሌሎች ተደራራቢ ችግሮችን እየተፋለመች ላለች አገር ወቅታዊውን ሸክም ለማቅለል ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እንደመክሩበት ማድረግ ግድ ነበር። ስለዚህ መንግሥት በሕግ ባለሙያዎች ተመክሮበትና ተሰናድቶ የተዘጋጀውን አራት አማራጮች የያዘ ሰነድ ለመወያያ አቅርቧል። ቀጣዩን ምርጫ ለማካሔድ በመንግሥት የቀረቡት አራት አማራጮች፤
አማራጭ አንድ፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፣
አማራጭ ሁለት፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፤
አማራጭ ሦስት፦ ሕገ መንግሥት ማሻሻል እና
አማራጭ አራት፦ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉ ናቸው። በእነዚህ አማራጮች ላይ ሰፊ ትንታኔ የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ እነዚህ አማራጮች የተሰናዳበትን አካሔድም አስረድተዋል። (ኢዛ)
ምርጫ፣ ኮሮናና ተፎካካሪ ፓርቲዎች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችና ተወካዮች ጋር በአንድ አዳራሽ ተሰብስበው የመከሩበትና “ኮቪድ-19፣ ምርጫን ማራዘምና የሕግ አማራጮች” በሚል ርዕስ የተካሔደው ውይይት የሳማንቱ ዐበይት ክንውን ነበር።
ሚያዚያ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. የተካሔደው የዚህ የውይይት መድረክ ዋነኛ ዓላማ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተጓጐለውን አገራዊ ምርጫ እንዴት ማካሔድ እንደሚቻልና መፍትሔ ለማበጀት የታለመ ነው ማለት ይቻላል። በዕለቱ በቀረበው አማራጭና በተሰጠው ማብራሪያ ላይ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የተለዩ አስተያየቶች የሰጡ ሲሆን፤ ሥጋቶቻቸውንና ጥያቄዎቻችንም ያቀረቡበት ነበር። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ረዥም ጊዜ ቆይታ ካላቸው የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች መካከል አንዱ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ነበሩ። “መንግሥት ይህንን ትኩረት ሰጥቶ ይህንን ማድረጉ ተገቢ ነው” ያሉት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ መፍትሔ መሻት የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነን። መፍትሔዎቹም ዋዛ እንዳልኾኑም መረዳት ይቻላልም ብለዋል። አንድ እንደ ደካማ ጐን አድርገው የሚወስዱት ግን፤ ይህንን ሰነድ ቀድመው አለማግኘታቸውን ነው። ቀድመን ብናውቀው ኖሮ የተሻለ ለመወያየት ይቻል ነበር በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በውይይቱ ላይ ከተገለጸውና ከተነገረው በመነሳት በአማራጭ አንድ እና ሁለት የማያስማሙ መኾኑን ገልጸው፤ ሦስተኛ ደረጃ የተቀጠውን ማሻሻያ ሐሳብ በተመለከተ ሕግ መንግሥቱ ብዙ ጥያቄ የተነሳበት በመኾኑ፤ ሕግ መሻሻል አለባቸው መባሉ ትክክል ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት በዚህ አጣዳፊ በኾነ ሁኔታ ውስጥ እንደሕገ መንግሥቱ ሁሉ ብዙ ጥያቄ የሚቀርብባቸው ሁለቱም ምክር ቤቶች (የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን)፤ ግን ነባራዊ ሁኔታውን ተቀብለን የምንኖርባቸው ሁለቱም ምክር ቤቶች በማሻሻሉ ሒደት ላይ መሳተፍ ይኖርባቸዋል። ሁለቱም ምክር ቤቶች ሌላ ምርጫ ተካሒዶ እምነት በሚያሳድር መልክ ከመዋቀራቸው በፊት፤ ስለሕገ መንግሥት ማሻሻል ማሰብ፤ ያው የድሮውን ስሕተት መድገም ስለሚኾን፤ ሕገ መንግሥት ማሻሻል የሚለውን ሦስተኛው አማራጭም ተገቢ እንዳልኾነ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ገልጸዋል።
አራተኛው አማራጭ የኾነው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ የመጠየቅ ጉዳይ ለእኛ አዲስ ነገር ነው ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ ከተጻፈው ውጭ ሕገ መንግሥቱ ይተርጐም የሚል ነውና ተርጓሚዎቹ የሚፈተሹበት ይኾናል። ነገር ግን የትኛው ነው የሚተረጐመው የትኛው አንቀጽ፣ የትኛው መንፈስ፣ … የሚለውን ከቀረበው ማብራሪያ ላይ አለማየታቸውንና በተሰጠውም ማብሪሪያ ስለማያመለክት ብዥታ የፈጠረ ስለመኾኑ ጠቁመዋል። የሚጠየቀው ትርጉም የትኛው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽና መንፈስ ጋር እንደኾነ ቢብራራ ለማነጻጸር መልካም ይኾናል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
“ዋናው ጉዳይ ታሪካዊ ስሕተት ሠርተን እንዳንሔድ ነው” ያሉት ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና በበኩላቸው፤ ኮሮና ላይ ሁሉም መስማማታቸውን ገልጸው፤ ነገር ግን ቀጣይ የፖለቲካ እድላችን ምን መኾን አለበት የሚለው ላይ ነው ልዩነት ስላለ፤ ይህንን ልዩነት መፍታት የሚያስፈልግ መኾኑን ተናግረዋል። ስለዚህ ለብሔራዊ መግባባቱ አስተዋጽኦ በሚያደርጉበት ደረጃ ዶክሜንቱ ለፓርቲዎች ይሰጥና ተነጋግረው እንዲመጡ እድል መሰጠት አለበት፤ ካልኾነ ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ እንዳይፈታ እንዳይኾን ድጋሚ መወያየቱ አስፈላጊነት ላይ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። አገራዊ ስምምነት ሲመጣና ከአገራዊ መግባት ውጭ ምንም ምርጫ የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ ፖለቲካ ጉዳይ ግን ተወያይተን ብንወስንና በድጋሚ ብንነጋገር ይሻላል ብለዋል። ከዚያ በኋላ ለሕገመንግሥቱ ትርጉም እውቀቱ ያላቸው ሰዎች ሊተረጉሙልን ይችላሉ፤ ይሄ ብዙ አስቸጋሪ እንደማይኾን ገልጸዋል።
የኦነጉ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከወቅታዊው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ተፈጽሟል ያሉትን የመብት ጥሰት ቅድሚያ ሰጥተው ጥያቄ አቅርበዋል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይታያሉም ብለዋል።
በዚህ የውይይት መድረክ፤ ምርጫን በተመለከተ የፓርቲዬ አቋም ነው ብለው አስተያየቶቹን የሰጡት የሕወሓት ተወካይ ዶክተር አዲስ ዓለም ባሌማ፤ አጉልተው የገለጹት መንግሥት ቀድሞም ቢኾን ምርጫውን ለማካሔድ ፍላጐት አልነበረውም የሚለውን ሐሳባቸውን ነበር።
ዶክተር አረጋዊ በርሔ ደግሞ፤ “በእኔ አመለካከት ስለምርጫ ጉዳይ በተለያዩ መድረኮች ላይ ስለምርጫ ተነጋግረናል። አሁን ደግሞ ስለኮሮና ቫይረስ ትኩረት አድርገን እንሥራ ብለን ተስማምተናል። በኮሮናው ላይ ቅድሚያ እንስጥ፤ ምርጫው ሁለተኛ ጉዳይ ይሁን” ብለዋል። ዶ/ር አረጋዊ አክለውም፤ አሁን የምናየው ግን በአንዳንድ ተናጋሪዎችን ይህንን ትኩረት የሚያስት ነገር ይታየኛል በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።
“ሁላችንንም የሚያጠፋ በሽታ መጥቶ፤ ትኩረቱ ኮሮና ላይ መኾን አለበት” በማለት፤ በሌላ መንገድ የሚመጡ አፍራሽ አመለካከቶች ግን ተገቢ አለመኾናቸውንና ይህንን የሚያደርጉትም የራሳቸው ዓላማ ስላላቸው መኾኑን ገልጸዋል። እንዲህ ካለው አስተያየታቸው ቀጥለው ከቀረቡት አማራጮች ውስጥ አማራጭ ሦስትና አራት ሊቀናጁ ይችላሉ ብለዋል። “ይህ ካልሆነ ግን የሕገ መንግሥቱ ትርጓሜው የሚለው አራተኛውን አማራጭ በመውሰድ፤ ይሄ የኮቪድ 19 ጦርነት እስክንቋቋመው ድረስ የሚውል የማሻሻያ ሕግ ብንፈልግ ይሻላል” ብለዋል።
ውይይቱ ሌሎች ጥያቄዎችና አስተያየቶችም የተሰነዘሩበት ነበር። በዚህ ውይይት ላይ የኢዜማ አቋምን የሚያመለክተው ሌላው መረጃ፤ የተካሔደውን ውይይት መንግሥት እኔ ብቻ ነኝ የመፍትሔ ሐሳብ አመንጪ ከሚል ወጣ ብሎ የሚመለከታቸውን አካላት ማነጋገሩ መልካም እንደኾነ በመጥቀስ ፓርቲያቸው መንግሥት ካቀረበው አራት አማራጮች ሦስቱ ላይ ተመሳሳይ ሐሳብ እንደነበረው፤ ነገር ግን የሕግ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ በሚለው አራተኛ አማራጭ ላይ ግን የተለየ ሐሳብ እንዳለው አመልክተዋል። ነገር ግን ፓርቲያቸው መንግሥት ባቀረባቸው አራት ውሳኔዎች ላይ ዛሬ ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ውሳኔ ያሳልፋል። (ኢዛ)
የአገሪቱ እስካሁን ያልታዩ አራት ፈተናዎች
ሰፋ ያለ ጊዜ በወሰደው የተፎካካሪ ፓርቲዎች አስተያየትና ጥያቄ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል። ከሰጡት ምላሽ ውስጥ አንዳንዶቹን እንዲህ ከፋፍለን አቅርበነዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተጋረጡባት አራት ዋና ዋና ፈተናዎች ያሉባት ስለመኾኑ በገለጹበት ማብራሪያቸው፤ ይህንን ችግር ለመቋቋም መንግሥት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመልክተዋል። አራቱ የአገሪቱ ፈተናዎችና ጠላቶች ናቸው ብለው የገለጹዋቸው ኮሮና፣ የበረሃ አንበጣ፣ የዓባይ ጉዳይ እና ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ሊገጥም ይችላል ብለው የገለጹት የኢኮኖሚ ጉዳይ ናቸው። ይህንንም “በመንግሥት በኩል በከፍተኛ ጥረትና ትጋት ዜጎችን ለመታደግና የመጣብንን ጠላት ለመዋጋት እጅግ ከፍተኛ ጥረት እያደግን ነው” ብለዋል። በዚህም መንግሥታቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብና ከዓለም መንግሥታት በግልጽ ምስጋና እንደተቸረው በማስታወስ፤ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ መንግሥታቸው እያደረገ ያለውንም እንቅስቃሴ ለማሳወቅ ሞክረዋል።
ወቅታዊውን አገራዊ ችግር አጉልተው ለማሳየት “በኢትዮጵያ ታሪክ አንድም መንግሥት በዚህ ልክ እንዳሁኑ የተደራረበ ፈተና ያጋጠመው የለም” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ የምርጫ ጉዳይን በምሳሌት ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ መንግሥታት ታሪክ ምርጫ እንደ አሁኑ አጀንዳ ኾኖ እንደማያውቅና ወይም አልነበረም። ካለም ለይስሙላ የሚደረግ እንጂ የሚያጨቃጭቅ ጉዳይ እንዳልነበርም በማመልከት፤ ከዚህ ቀደም ምርጫ ብዙም አጀንዳ እንዳልነበረም አብራርተዋል። “ከኤርትራ ጋር እየተዋጋንም ማድረግ ይቻል ነበር፤ የሚፎካከር ኃይል ስላልነበረ። ግማሹ አውሮፓ ናቸው፣ ግማሹ ኤርትራ ነው የነበረው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ግን በውጭ አገራት ያሉ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰባሰባቸው ምርጫ በጉጉት የሚጠበቅ እንዲኾን አድርጓል በማለት ወቅታዊውን የምርጫ ጉዳይና የምርጫ እሳቤውን አስረድተዋል። (ኢዛ)
ሰብዓዊ መብት ጥሰትና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ
በዕለቱ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መሪዎች ውስጥ አንዱ የኾኑት የኦነጉ አቶ ዳውድ ኢብሳ፤ ከወቅታዊው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸማል በማለት ጥያቄ አቅርበው ነበር።
ፕሮፌሰር መራራ ጉዲናም በተመሳሳይ በአባሎቻቸው ላይ እስራት ስለመፈጸሙ አንስተው ነበር። እንዲህ ባሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ዶ/ር ዐቢይ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት መንግሥት አፋጣኝ ኾኖ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያስከተለ ነው የሚለውን ክስ በተቃራኒ ቢታይ የሚሹ መኾኑን ገልጸዋል።
የጥያቄውን አቅራቢ ከዚህ ስብሰባ በኋላ ወደ መርካቶ ቢሔዱና ቢያዩ፤ በከፍተኛ ደረጃ ምንም እንዳልታወጀ፣ ምንም በሽታ እንደሌለ ሰው ሲንቀሳቀስና ሲተቃቀፍ የሚታየው ብለዋል። ራሳቸው ተንቀሳቅሰው እንዳዩትም፤ ችግር መኖሩን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዋናው ችግር ግን ይህንን ሕግ ማስፈጸም ላይ መኾኑን አስረድተዋል። ውስንነት የሚታየው ተገን በማድረግ የሚፈጸም አፈና የለም። ይህ ሁሉም በቀላሉ የሚገነዘበው ጉዳይ እንደኾነ በመጥቀስ፤ “ምናልባት እናንተን በሚመለከት የተለየ በደል የሚፈጸም በደል ካለ መነጋገርና ማስተካከል ይቻላል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ነገር ግን እርስዎም እንዲገነዘቡ የሚያስፈልገው (አቶ ዳውድን)፤ ሁለት ቦታ መጫወት ግን አይቻልም” ብለዋቸዋል። “ሰላማዊና ሕጋዊ ፖለቲካ እከተላለሁ ብለው፤ በእኛ መካከል ካሉ ሁሉም ነገር በዚያ መንገድ ይኾናል። አንድ እግሩ እዚህ ተቀምጦ፤ በሌላ እግሩ ሌላ ነገር የሚጫወቱ ከኾነ ለመንግሥት ያስቸግራል። ሕግ ማክበር፣ ሽፍታ ያለመኾን፣ በመሣሪያ ማድረግ መተውና ሁሉንም በውይይትና በሕግ ማድረግ ከመጣ፤ ከዚህ ቀደም ብዙዎችን ጥያቄዎች ለመመለስ ሙከራ እያደግነው በመነጋገር ሊፈታ ይችላል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህ ጥያቄ መልስ ላይ ማሰሪያ ያደረጉት ደግሞ፤ “በመንግሥት በኩል ወንጀል የሠራ ሰው የእርስዎም ኾነ የእኛም ድርጅት አባል ቢኾን፤ የሌላ ፖለቲካ ድርጅት አባል ቢሆን መጠየቅ አለበት” የሚል ነው። ነፃ የሚያደርገው ወንጀል ያለመሥራት ብቻ ነው። (ኢዛ)
በዘመነ ኮሮና ኢኮኖሚው ጉዳይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት
በሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወቅታዊውና በቀጣይ ሊኖር ስለሚችለው ኢኮኖሚ ጉዳይ አንስተዋል። ከወረርሽኙ በኋላ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማምጣት ተችሏል። ይህንን ገንዘብ ከተለያዩ አጋር አገሮች ወገኖች ጋር በመደራደር የመጣ ነው።
ሰፊ ሥራ ውስጥ ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜ የለንም የሚለውንም አክለዋል። ኢኮኖሚው እንዳይሰበር፣ አፍሪካ ውስጥ እየደረሰ ያለው ኢኮኖሚያዊ ስብራት ኢትዮጵያ ውስጥም እንዳያጋጥም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገም መኾኑን ተናግረዋል።
አንዳንድ አገራት ከኔጌቲቭ አሥር በላይ የኢኮኖሚ ድቀት ያጋጥመናል የሚል ግምት ሐሳብ ያነሳሉ። አሁን ባለው ሁኔታ ከኔጋቲቭ አሥር በላይ የኢኮኖሚ ድቀት ካጋጠመ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ብልጽግናም አሸንፎ ቢቀጥል፤ እናንተም ብታሸንፉ ትርጉም የለውም ብለዋል።
በዚህ አባባላቸው ምክንያት ደግሞ ችግሩ ለአንድ ሁለት ተርም (የምርጫ ዘመን) የሚቀጥል እንደሚኾን አስረድተዋል። አያይዘውም የሚመረጠው ኃይል ተስፋ ሰጥቶ አገር የማያሻሻልም ከኾነ ወይም ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ለውጥ የማያመጣ ከኾነ መቆየቱ ብቻ ጠቃሚ አይደለም ብለዋል።
እንደ የዓለም ገንዘብ ድርጅትና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትም ቢኾኑ፤ ቢያንስ እድገት የመቀነስ ችግር እንጂ ኢትዮጵያ ኔጌቲቭ ውስጥ አትገባም የሚል ትንታኔ እንዳላቸው በማመልከት፤ አፍሪካ ውስጥ ዩኒክሊ ይህንን ችግር ማኔጅ ማድረግ እያደረጉ ካሉ አሉ ጥቂት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ መኾኗን ጠቁመዋል።
“ድሃን መመገብ ራሱን የቻለ ችግር ነው። ማክሮ ኢኮኖሚውም የደረሰበት ድቀት መቀነስና እድገቱ ከሚጠበቀው በላይ ሔዶ ለዓመታት የሚሻገር ችግር እንዳይኾን ማድረግ ራሱ አደጋ አለው።
"ኢኮኖሚው ላይ ዲፕሬሽን ሲመጣ በራሱ የኢኮኖሚ ፎርሙላ አይፈታም። ዲፕሬሽን በኤክስተርናል ብትር ኢኮኖሚን የሚመታና የሚያደቅ ጉዳይ ስለኾነ፤ በኢኮኖሚ ሞዴል ብቻ ያንን ነገር ማየት ስለማያስፈልግ፤ ሁለገብ የኾነ ሞያ፣ ጥበብና አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚን ዲማንድ ማድረግ ይጠይቃል።”
ከዚህ አንፃር ውጤታማ ሥራ እየተሠሩ በመኾናቸው ውጤት እየመጣ ነው ብለዋል። ከዚህ አንፃር የፖለቲካ ድርጅታችን ምንም አስተዋጽኦ የላቸውም ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል። (ኢዛ)
የፖለቲካ ፓርቲዎች አለመተማመንና በባንዳነት መፈረጅ
የፖለቲካ ፓርቲዎች መተማመን አልቻሉም የሚል አመለካከት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ እንዲህ ነበር።
“መታመን ማለት ሁለት ወገን የሚቀባበሉት ጉዳይ እንጂ ከአንዱ ወገን የሚጠበቅ ጉዳይ አይደለም” ብለዋል።
አሁን ባለው የተፎካካሪ ፓርቲዎች ልምምድ ውስጥ 50 ዓመት ሙሉ አንትሪክ፣ 50 ዓመት ሙሉ ኮንስፓይሬሲ፣ 50 ዓመት ሙሉ ማታለል አዋጭ ነው ብለው የሚያስቡ ግለሰቦችና ባንዳዎች መኖራቸውን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁንም ባንዳዎች አሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያ ልትወረርና አደጋ ሊያጋጥማት ባለበት በዚህ ጊዜ ውስጥ፤ ከጠላት ጋር የሚደራደር ባንዳ የፖለቲካ ድርጅት ስለመኖሩ በመጥቀስ፤ ይህንን ኃይል ማመን ያስቸግራል ብለዋል። “ከባንዳ ተልዕኮ መውጣት፣ ከጠላት ጋር ያለመደራደር በኢትዮጵያ ኢንተረስት (ጥቅም) ላይ የሚመሳሰል አቋም መያዝ ከሁላችንም ይጠበቃል” ብለዋል። “ይህንን ሳታሟሉና ከተመካከርን በኋላ ደብል ስታንዳርድ የምታራምዱ ከኾነ፤ ቅንነትና ውይይትን ያበላሻል። ወደፊትም ጥምር መንግሥት የምንፈጥር ከኾነም፤ መጠራጠር ካለ አብረን መንግሥት መኾን አንችልም። እንደዚህ ዐይነት መድረኮች እየተማመንን ለመሔድ የሚያግዙ መኾናቸውን በደንብ መገንዘብ ያስፈልጋል” በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል። ያልተፈታ ነገር ካለ ግን አሁንም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚቀርቡ ጥያቄዎችንም እናያለን በማለት ገልጸዋል። (ኢዛ)
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋም
በዕለቱ ከተሰነዘሩ ሐሳቦች አንዱ አሁን ባለው ሁኔታ የሽግግር መንግሥት ይመሥረት የሚለው ነው። በዚያ አዳራሽ ብቻ ሳይሆን፤ ቀደም ብሎም የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም አቋም የያዙ ፓርቲዎች አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ግን ይህ የማይኾን ሐሳብ መኾኑን አስረግጠው ተናግረዋል።
በምርጫ ዙሪያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና ተወካዮች ጋር የመከሩት የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ “የሽግግር መንግሥት ይቋቋም” በሚል ለሚቀርቡ ጥያቄዎች፤ “የሽግግር ሳይሆን የብጥብጥ መንግሥት ነው የምለው” በማለት የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚለውን ሐሳብ ኮንነዋል። “እንኳን በጋራ መንግሥት ለመኾን፤ በጋራ ምክር ቤት ተወያይቶ አጀንዳ መወሰን ያልቻለ ስብስብ፤ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ውስጥ እንደዚህ ዐይነት ቀልድ መቀለድ አያስፈልግም” በማለትም በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አቋም በግልጽ ተናግረዋል።
“ከዚህ ከወጣን ከአንድ ሰዓት በኋላ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ምን እንደሚያጋጥም ምንም እውቀት የለንም፤ ዝም ብሎ ዘሎ ሥልጣን መያዝ የሚቻልበትን መንገድ ከምንከተል፤ በተቻለ መጠን ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ፣ ነፃ እና ብዙ ተዋናዮች ያሉበት ማድረግ፤ እንደ ተዋናዮቹ ቁጥር በመንግሥትም በሌሎች ጉዳዮችም በጋራ የምንወስንበትን መንገድ መፍጠር ይበጃል” በማለት የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ጥያቄው ቦታ የሌለው መኾኑን ገልጸዋል። (ኢዛ)
ባንዳነት
በዕለቱ ማብራሪያቸው በተለያዩ የንግግራቸው ክፍል “ባንዳ” የሚለውን ቃል የተጠቀሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያውም በዚህ ወቅት በባንዳነት ከጠላት ጋር እስከመኾን መድረሳቸውን የጠቆመ መረጃ የሰጡበት ነው። በተለይ የሕወሓቱ ተወካይ (ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማ) ጥያቄን በመለሱበት ክፍል፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ አጋጥሟት የማያውቅ ችግር እንደገጠማት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወቅታዊ ችግርን መጠቀሚያ የማድረግ ነገር መታየቱንም ጠቅሰዋል።
“ከምርጫችን ጋር መያያዙና የባንዳ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎችም ፖለቲከኛ ነን ስለሚሉ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጠላት ጋር ለማወክ እድል የሚሰጥ ኾነ። ከፍተኛ ፈተና ነው ያለው፤ ነገር ግን ባሉት ፈተናዎች በእርግጠኝነት እንፈተናለን ጉዳዩ መሥዋዕትነትን የሚጠይቀን ይኾናል። ያሉትን ፈተናዎች ኢትዮጵያ አሸንፋ ትሻገራለች። በተቻለ መጠንም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም ይገነባል” የሚልም ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። (ኢዛ)
ምርጫውና የመንግሥት አቋም
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት የምርጫን ጉዳይ ብቻዬን ነው የምወስነው የሚል መንግሥት ያለመኾኑን በማብራራት፤ ምርጫው መካሔድ እንዳለበት ብልጽግና በፓርቲዎች ምክር ቤት አቋሙን ሲገልጽ መቆየቱንም አስረድተዋል። ምርጫው አይደረግ የሚል እምነትም ፍላጎትም እንዳልነበረው ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንንም በተለያዩ መስኮች ሲገልጹ እንደነበረም በመናገር፤ ብልጽግና ምርጫው እንዳይካሔድ ፍላጎት የለውም የሚለውን አስተያየት አንጠልጥለዋል።
አሁን የመጣው ፈታኝ ሁኔታ ግን ያንን ለማድረግ የሚያስችል ባለመኾኑ ብልጽግና አዲስ ይዞት የመጣው ነገር ቢኖር፤ የሁሉም ድምፅ እንዳሰማና አገር የሚገነባው በመመካከር እንጂ ግማሹን አስረን ግማሹን እንዲሰደድ አድርገን ዴሞክራሲ ልንገነባ አንችልም የሚል ግልጽ አቋም መኾኑን የጠቀሱበት ነበር። በተለይ ከሕወሓት ተወካይ ለተነሳው አስተያየትና ጥያቄ ከፌደራልና ከብልጽግና ፓርቲ ጋር መነጋገር፣ መወያየት፣ መፈታት አለበት፤ ትክክል አይደለም የምትሉት ነገር ካለ ብልጽግና ለመወያየት ዝግጁ መኾኑን ነበር የገለጹት። አክለውም ውይይቱን በግልጽም በስውርም ማድረግ ይቻላል በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
አስከትለው ግን ሕወሓት በሚያስተዳድረው ክልል አለ ያሉትን ግድፈት በሞከሩበት ገለጻቸው፤ “በዚሁ አጋጣሚ ድርጅትዎን አደራ ማለት የምፈልገው እናንተ በምትመሩት ክልል የሚፎካከሩ ፓርቲዎች ወጥተው መግባት ባለመቻል በተደጋጋሚ ክስ ያቀርባሉ። ዴሞክራሲን እዚያው ተለማምዳችሁ እዚያው አድርጋችሁ፤ እኛም ከእናንተ ትምህርት እንድንወስድ ብታደርጉ መልካም ነው” በማለት ለዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ ምላሽ ሰጥተዋል።
አሁን ባለው ልምምድ ውስጥ አምሳ ዓመት ሙሉ (ሴራና አሻጥር) አምሳ ዓመት ሙሉ ማታለል አዋጭ ነው ብለው የሚያስቡ ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ፤ ባንዳዎች አሉ። ኢትዮጵያ ልትወረር አደጋ ሊያጋጥማት ባለበት በዚህ ጊዜ ውስጥ፤ ከጠላት ጋር የሚደራደርና የሚሿከት ባንዳም አለ፤ ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ይሄንን ኃይል ማመን ያስቸግራል። ከባንዳ ተልዕኮ መውጣትና ከጠላት ጋር አለመደራደር በኢትዮጵያ ፍላጎት ላይ የሚመሳሰል አቋም መያዝ ከሁሉም የሚጠበቅ ስለመኾኑ ተናግረዋል። (ኢዛ)
ልደቱና ጃዋር
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከሰሞኑ የመንግሥትና የፖለቲካ ድርጅቶች ውይይት በኋላ አቶ ልደቱ አያሌው እና አቶ ጃዋር መሐመድ በኤልቲቪ ላይ ቀርበው የራሳቸውንና የፓርቲዎቻቸውን አቋም አሳውቀዋል። ቀድመውም ቢኾን የሽግግር መንግሥት መመሥረት አለበት ብለው የሚያምኑት አቶ ልደቱ አያሌው፤ ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትሩና በተፎካካሪ ፓርቲዎች ያደረጉትን ውይይት የታይታ መኾኑን አመልክተዋል። አሁንም ሁሉም ፓርቲዎች ያሉበት መስማማት ያስፈልጋልም በማለት ሞግተዋል።
አሁን ያለው መንግሥት ከደረጃ በታች አቅም ያለው መኾኑንም ጠቅሰዋል። ምርጫውን በተመለከተ ግን ሁሉንም ያግባባ አሠራር መፈጠር አለበት። ከመስከረም 30 በኋላ ይህ መንግሥት ያበቃል፤ ስለዚህ ሁሉም ፓርቲ እኩል መኾኑንም መታወቅ አለበት ብለዋል።
“በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ኾና፤ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት፤ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ግን የሥልጣን ዘመኑን በሕገ-ወጥ መንገድ ለማራዘም” እየሞከረ መኾኑን የገለጹት አቶ ጃዋርም፤ ከመስከረም 30 በኋላ ሥልጣን እንደሌለው አውቆ ብልጽግና ፓርቲ ከወዲሁ ሁሉንም የሚያስማማበትን ማድረግ አለበት ብሏል። (ኢዛ)
ምርጫ ቦርድ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ እና የምክር ቤቱ ውሳኔ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ምርጫን በተመለከተ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ በአብላጫ ድምፅ ያጸደቀው በዚህ ሳምንት ነው። የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርብ ለሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከመምራቱም በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የጠቅላላ ምርጫን የተመለከተ ምክረ ሐሳብ ማብራሪያ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
በቦርዱ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ የመራጮች ምዝገባ የሚጀምረው ከሚያዝያ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ቢሆንም፤ በአገሪቱ ውስጥ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በርካታ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች የተገደቡ በመኾኑ የምርጫ ሒደቱን በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ማካሔድ አልተቻለም ብለዋል። ይሄን ተከትሎም የውሳኔ ሐሳቡን ለምክር ቤቱ እንዲያቀርቡ ኾኗል።
ወረርሽኙ በዓለምና በአገራችን መከሰቱን ተከትሎ መንግሥት ቅድሚያ ለሕዝብና ለአገር በሚል በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ቦርዱም በዚህ ጊዜ ምርጫ ማካሔድ እንደማይቻል መግለጹ ተገቢ እንደኾነ ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው፣ ወረርሽኙ በዓለምና በአገራችን በመከሰቱ መንግሥት ቅድሚያ ለሕዝብና ለአገር በሚል በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፤ ስለኾነም ቦርዱም ከዚህ ጊዜ ምርጫ ማካሔድ እንደማይቻል ማመልከቱ ተገቢ መኾን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ምርጫን በተመለከተ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በአንድ ተቃውሞ፣ በ18 ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምፅ በማፅደቅ፤ ምርጫውን በተመለከተ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርብ ለሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሦስት ተቃውሞ፣ በሰባት ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምፅ መርቷል። (ኢዛ)
የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውሳኔ
ከሳምንቱ ዐበይት ጉዳዮች ውስጥ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ጫና ለመቀነስ ያስችላሉ ያላቸውን የተለያዩ የፖሊሲ ውሳኔዎች ማሳለፉን ማሳወቁ ነው።
ውሳኔዎቹ ከውዝፍ የግብር ዕዳ ጋር የተገናኙ የዜጎችን ኑሮ መታደግ ላይ ያተኮሩ መኾናቸውን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ ያሳወቁ ሲሆን፤ ወረርሽኙ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በማሰብ የተወሰነ ስለመኾኑም የሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ ያመለክታል።
መንግሥት ከዚህ ቀደም ከወሰዳቸው እርምጃዎች በተጨማሪ በዚህ ሳምንት የወሰደው የፖሊሲ ውሳኔ ግብር ከፍለው የኦዲት ግኝት የተገኘባቸው ተቋማትም ውዝፍ የኦዲት ግኝታቸውን ውሳኔው ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ ፍሬ ግብሩን በሚቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ከፍለው እንዲጨርሱ መወሰኑ አንዱ ነው። የፍሬ ግብራቸውን 25 በመቶ በመጀመሪያ በመክፈል ቀሪውን በተሰጣቸው ጊዜ ለሚከፍሉ ተቋማት የግብር ቅጣትና ወለድ እንደሚነሳላቸው ነው።
ሙሉ የፍሬ ግብሩን በአንድ ጊዜ የሚከፍሉ ተቋማትም የአስር በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግላቸው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ውሳኔውን ለማስፈጸም ገንዘብ ሚኒስቴርና የገቢዎች ሚኒስቴር ዝርዝር መመሪያ እያዘጋጁ መኾኑን ጠቁመዋል።
“ከኦዲት ግኝትና ከውዝፍ ጋር ተያይዞ በፍርድ ሒደት ላይ ያሉ ተቋማትም ፍሬ ግብራቸውን ከፍለው ከክርክር መውጣት እንደሚችሉና ይህ ግን በግብር ከፋዮቹ ፈቃደኝነት የሚወሰን ነው” ብለዋል።
በሌላ በኩል ወረርሽኙን ምክንያት በማድረግ ለተከራዮቻቸው የቤት ኪራይ እፎይታ ለሰጡ ግለሰቦችና ተቋማት የኪራይ ገቢ ግብር ስረዛ አድርጓል። “ይህ ውሳኔ ተቋማቱን ማመስገንና ሌሎችን ለማበረታታት ነው” ብለዋል።
በገቢ መቀዛቀዝ ምክንያት ለሠራተኞቻቸው ደምወዝ መክፈል ያልቻሉ ተቋማትን ለማገዝም፤ ተቋማቱ ለሠራተኞች የሚከፍሉትን የአራት ወር የደምወዝ ግብር አስቀርተው ለሠራተኞች ደምወዝ ክፍያ እንዲያውሉት ውሳኔ ተላልፏል።
የፖሊሲ ውሳኔው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ጤና ተቋማት የተለያዩ ቢዝነስ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን ያጠቃልላል። መንግሥት ይህን ውሳኔ የወሰነው በወረርሽኙ ምክንያት የተፈጠረውን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ለማነቃቃት ተቋማቱ ሠራተኞቻቸውን ሳይበትኑ ሥራቸውን መሥራት እንዲችሉ ለማገዝ እንደኾነ ዶክተር ኢዮብ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ብድር መስጠት የሚያስችለውን አስቸኳይ የብድር መስኮት እንዲከፍትም ተወስኗል። ለአምራች ሕብረት ሥራ ማኅበራት 1.5 ቢሊዮን ብር ብድር እንደሚዘጋጅ ይኸው በዚህ ሳምንት በመንግሥት የተወሰነው ውሳኔ ያመለክታል።
የዜጎችን የወጪ ጫና መጋራት በሚልም፤ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ በጎ አድራጊ ግለሰቦች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ያጋጠማቸውን የኢኮኖሚ ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል። በዚህ ረገድ በመደረግ ላይ ካለው ድጋፍ አንዱ የቤት አከራዮች ተከራዮች ለተወሰነ ጊዜ ከኪራይ ክፍያ ነፃ እንዲኾኑ የሚያደርጉት ድጋፍ መኾኑን ገልጾ ከዚህ አንፃርም የተወሰነውን ውሳኔ አሳውቋል።
በመኾኑም በተመሳሳይ መንግሥት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ከሥራ እንዳይፈናቀሉ፤ እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ለመክፈል ተቸግረው ከጎዳና ላይ እንዳይወድቁ የበኩሉን እገዛ ማድረግ እንደሚኖርበት ታምኖ፤ በዚህም መሠረት የድጋፍ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በቀረበው ሐሳብ መሠረት፤ ለመኖሪያ፣ ለትምህርት፣ እንዲሁም ለአነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች አገልግሎት ከሚውሉ ቤቶች ኪራይ በሚገኝ ገቢ ላይ የሚከፈለውን ግብር ማንሳት የሚለው ታምኖበት፤ በአሁኑ ጊዜ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጫና ኾኖ የሚታየው የቤት ኪራይ ወጪ በመኾኑ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ውሳኔ ላይ መደረሱ ተነግሯል። በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በአገሪቱ የተፈጠረው የዋጋ ንረት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የቤት ኪራይ በመክፈል ረገድ የነበራቸውን አቅም በማዳከሙ፤ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ በመረዳት፤ ወጪውን መጋራት ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ የቤት አከራዮች ከቤት ኪራይ ከሚያገኙት ገቢ ላይ ሊከፍሉ የሚገባውን በአማካኝ 30% የገቢ ግብር ማስቀረት ተግባራዊ ይደረጋል። በገቢ ግብር አዋጅ እንደተደነገገው ከቤት ኪራይ ከሚገኝ ገቢ ውስጥ 50% ወጪ እንደሚኾን ተቆጥሮ አከራይ በቀሪው 50% ላይ 30% ግብር ሊከፍል ይገባል። በመኾኑም መንግሥት የሁለት ወራትን የኪራይ ወጪ እንዲሸፍን ለማድረግ ከተፈለገ አከራዮች በአንድ የግብር ዓመት ውስጥ ሊከፍሉ የሚገባውን ግብር ቀሪ ማድረግ እንደሚኖርበት ታምኖ ውሳኔ ተወስኗል። (ኢዛ)
የደምወዝ ገቢ ግብር ማንሳት
ከሰሞኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ውስጥ አንዱ ያለሥራ ደምወዝ የሚከፈላቸው ሠራተኞች የሚጠየቀውን የደምወዝ ገቢ ግብር ማንሳት የሚለውም ጉዳይ ታይቷል። አንዳንድ ድርጅቶች ባጋጠማቸው የሥራ መዳከም፤ እንዲሁም የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት ለመከላከል ሲባል ሠራተኞቻቸው በየቤታቸው እንዲቆዩ በመደረጋቸው፤ እነዚህ ድርጅቶች በሚኖርባቸው የወጪ ጫና ምክንያት ደምወዝ በመክፈል ሠራተኞችን ይዘው መቀጠል ስለማይችሉ፤ ሠራተኛ የመቀነስ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደዱ ግልጽ በመኾኑ፤ ሠራተኛ መቀነስ የሚያስከትለውን ማኅበራዊና ሰብዓዊ ችግር ለመከላከል፤ መንግሥት አንዳንድ ድጋፎችን ማድረግ እንደሚኖርበትም፤ አሠሪው ለሠራተኛ ደምወዝ የሚያወጣውን ወጪ መጋራት በገቢ ግብር አዋጅ በተደነገገው መሠረት፤ አሠሪ ለሠራተኛ ከሚከፍለው ደምወዝ ላይ ገቢው በመጨመሩ ቁጥሩ እያደገ የሚሔድ እስከ 35 በመቶ የደምወዝ ገቢ ግብር ለመንግሥት ገቢ ማድረግ አለበት።
አሠሪው በዚህ ረገድ የሚኖርበት ወጪ ባይኖር ሠራተኛውን ለተወሰነ ጊዜ ለማቆየት ሊበረታታ ስለሚችል፤ አሠሪው ለሁለት ወራት ያህል ያለሥራ ለተቀመጡ ሠራተኞች ከሚከፍለው ደምወዝ ላይ 50 በመቶ ያህል መንግሥት እንዲጋራ ለማድረግ መንግሥት በአራት ወራት ደምወዝ ላይ ሊከፈል የሚገባውን ግብር አሠሪው እንዲጠቀምበት እንዲፈቀድም ማሻሻያ ተደርጓል። (ኢዛ)
እርዳታ ከግብር ተቀናሽ እንዲኾን መፍቀድ
በተለያዩ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል። ይህ ድጋፍ በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል ለማድረግ መንግሥት እነዚህን በጎ አድራጊዎች ማበረታታት ስለሚኖርበት፤ እንደተሰሚዎች የሚሰጡት እርዳታ ከግብር ቅናሽ እንዲኾን በቀረበው ሐሳብ ላይ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በገቢ ግብር አዋጅ ለበጎ አድራጐት ዓላማ የሚደረጉ ስጦታዎች ግብር ከሚከፈልበት የግብር ዓመቱ ገቢ አሥር በመቶ ባልበለጠ መጠን ለግብር ተቀናሽ እንዲደረግ ይፈቅዳል። ይህ መጠን ከፍ እንዲል ቢደረግ፤ በጎ አድራጊዎች ኮሮና ቫይረስን ለመዋጋት ለሚደረገው ጥረት የበለጠ ድጋፍ ለማድረግ ይበረታታሉ።
በመኾኑም ኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በጎ አድራጊዎች ለመንግሥት የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ ግብር ከሚከፈልበት የ2012 ዓ.ም. ሃያ በመቶ ባልበለጠ መጠን ለግብር ክፍያ ተቀናሽ እንዲኾን እንዲፈቀድ ሐሳብ ቀርቧል። ቀጥተኛ ተጎጂ ያደረጋቸው የንግድ ተቋማት በየወሩ ይከፍሉት የነበረው የተጨማሪ እሴትና የተርን ኦቨር ታክስን አጠራቅመው ሰኔ ላይ እንዲከፍሉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አሳልፏል። (ኢዛ)



