አቤ ገላው ዘርአይ ድረስ! (ሉሉ ከበደ)
አቤ ገላው ዘርአይ ድረስ!
(ሉሉ ከበደ)
ሰው ሁሉ በፈራበት፤
እንደ ኤሊ ድንጋይ ለብሶ በተኛበት፤
በቁም በሞተበት፤
ብቅ አለ ዘርዓይ ድረስ አዲስ ስጋ ለብሶ፤
አበበ ገላው ተብሎ፡ ጥይት አንደበት ጎርሶ።
ተኮሰበት! ያንን ፈሪ የባንዳ ልጅ፤
ሲመለስ ሲቀለስ አግኝቶት ጌቶቹ ደጅ፤
አንገቱን ሰበረው፤አንዘፈዘፈው!!!
በጌቶቹ ፊት አርበተበተው::
ያ..ንን.. የ..ባንዳ ልጅ.. ያ..ንን..ፈሪ፤
የጣሊያን ጻእረ መንፈስ መሰሪ።
ለካንስ እርቃኑን ቆሞ ላገኘው፤
ከጥንቸል የባሰ ብርግግ ነው።
በሺህ ጦር፤ በሺህ መድፍ ታጥሮ፤
ከቤተመንግስት ቱቦ ሲያቅራራ፤
በከብቶቹ ምክር ቤት ሲያጓራ፤
ሰው ይመስል ነበር የማይፈራ።
ለካንስ አውላላ ሜዳ ላይ ላገኘው፤
ነፍሱ በፍርሀት የቀጠነች ድውይ ነው።
ምነዋ.. ምነዋ.. ሳይለመስ በቀረ፤
በፍርሀቱ እዚያው ሞቶ በተቀበረ፤
ኢትዮጵያም እፎይ ብላ ነበረ።
አቤ ተኩሷል!…በል እንገፍእንገፍ፤
ያባትህ ጋሻ ትኳኑ ይርገፍ፤
የኢትዮጵያ ጀግና ተነስ ተሰለፍ፤
ዛሬን አትለፍ!.. ዛሬን አትለፍ!
አቤን ተከተል ይጣራል ቃሉ፤
እያለ.. ዘራፍ!..
ነጻነት በሉ!..ነጻነት በሉ! ነጻነት በሉ!
በቁጣ በንዴት እየተንበለበለ፤
ፍሪደም!..ፍሪደም!.ፍሪደም!..ፍሪደም!..እያለ!!
አቤን ተከተል፤
ክተት ሰራዊት፤ ምታ ነጋሪት!



