አይ ሽብሬ!!! (ወለላዬ)
አይ ሽብሬ!!!
ከወለላዬ (ለሽብሬ ደሳለኝ እና በግፍ ለተገደሉት ሦስተኛ ዓመት መታሰቢያ ይሁን)
እፍ ብለው ካጨለሙሽ
በጥይት ዶፍ ከበሳሱሽ
ሦስተኛ ዓመት ይሄው ሞላሽ
አንቺ ምድር አንቺ ሀገሬ
አዋሀድኩሽ ከሽብሬ
በናትነት ባገርነት
ልትቆሚልን ባጋርነት
ልትደብቂን እንደጫካ
ልጠልይን እንደዋርካ
እርግቢቷ እንደመላክ
ልታነሽን በመንበርከክ
እሪ ብለሽ እንደቀረብሽ
በጥይት ዶፍ ከበሳሱሽ
ሦስተኛ ዓመት ይሄው ሞላሽ
አይ አውሬነት አይ ጭካኔ
እረስተውት ነገን በኔ
የሥልጣን ዛር ልክፍታቸው
ሰው መሳዮች አውሬ አርጎአቸው
ገድለው በልተው ላይጠረቁ
ላያለቅሱ ወይ ላይስቁ
ወይ ላይከብሩ ላይደኸዩ
ስንቱን ከሰው ካገር ለዩ
ስንቱን አጭደው በደም ነክረው
በጭዳነት ጣሉት ሰክረው
አቤት እግዚዎ የግፍ ሥራ
አንገት ቀልተው መዘው ካራ
እንደጀግና በመፎከር
አረከሷት ያችን ሀገር
አይ ሽብሬ አይ ሀገሬ
ሰለቀጠሽ በላሽ አውሬ
አይ ሀገሬ አይ እናቴ
ሆኖ ታየኝ ሞትሽ ሞቴ
እታበባ እቴ እሜቴ
ሀገር ክብሬ ነፃነቴ
አዋረዱሽ አዋረዱኝ
አገር እናት እት አሳጡኝ
ሳያምርብሽ ሳያምርብኝ
እንደከፋሽ እንደከፋኝ
ሳንተያይ ሳንገኛኝ
መንገድ ደፉሽ ገደሉብኝ
እንዴት አልጮህ አላነባ
ማነው ከልካይ ወንድን እንባ
ለምን አልጮህ አላለቅስ
የህቴ አናት ሲፈረከስ
እንዴት አልሆን አመፀኛ
ተሳዳቢ ነገረኛ
እንዴት አልሆን ቁጡ አኩራፊ
ሆነውብኝ አገር አጥፊ
አወይ ክብሬ ነፃነቴ
ወይ ሽብሬ ወየው እቴ
እፍ ብለው ካጨለሙሽ
በጥይት ዶፍ ከበሳሱሽ
ሦስተኛ ዓመት ይሄው ሞላሽ
እንዴት ነበር ያንቺ ሕይወት
አስተዳደግ የሩቅ ምኞት
ምን ነበረ እቴ ዓላማሽ
ለወገንሽ ለሀገርሽ
ለወደፊት ምን ልትሰሪ
እንደነበር ተናገሪ
መቃብሩን ፈንቅይና
ሞትን ትንሽ ተራ አርጊና
ቀና በይ ነይ ሽብሬ
አሳፍሪው ይሄን አውሬ
መሸነፉን ሞት እራሱ
አሳውቂ ነይ ለነሱ
አንቺን ገድሎ አገር ቀብሮ
አንዱን አስሮ ሌላ አባሮ
የምጣት ቀን መዳረሻ
የዲያቢሎስ መቀደሻ
አርጎ ሀገርን አረካክሶ
እንደገና ከሱ ብሶ
”በመንግሥታችን የተነሱ ...
”ሕግጋትን ያፈረሱ ...
”አመጽ ሽብር ያነሳሱ ...
”ጥፋተኞች አጉራ ዘለል ...
”ናቸው! ...” ብሎ ሲወነጅል
እነአጋዚ ምን ይባሉ
ሰው እያየ ሰው ሲበሉ
ምን ይባሉ አዛዦቹ
በአደባባይ ገዳዮቹ
ወዲያ ተውኝ አታናግሩኝ
ክፉ ቁስሌን አታሰታውሱኝ
ለነፃነት ላንቀላፉት
ለእኩልነት ለወደቁት
ሐቅን ይዘው ለታጨዱት
ለዛ ወጣት ወንድም ክብሬ
ለኢትዮጵያ ውድ ሀገሬ
ኀዘን ላይ ነኝ ለሽብሬ
አወይ ክብሬ ነፃነቴ
ወዮ ሀገሬ አወይ እቴ
እፍ ብለው ካጨለሙሽ
በጥይት ዶፍ ከበሳሱሽ
ሦስተኛ ዓመት ይሄው ሞላሽ
ከወለላዬ (ለሽብሬ ደሳለኝ እና በግፍ ለተገደሉት ሦስተኛ ዓመት መታሰቢያ ይሁን!)