የኔ ሽበት (Read on PDF)

ከወለላዬ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

 

በቁርጥራጭ ሦስት መንግሥት

ስንገላታ ስንከራተት

ቱግ ብሎ በባዶ ቤት

ያስቀኛል የኔ ሽበት

ድሮ ፀጉሩ ነጥቶ እማውቀው

ቦርጭ ቢጤ ሆድ ነበረው

ድሮ የማውቀው ባለሽበት

ነበረ ቢያንስ የአምስት አባት

ይሆን ነበር ወይም ዶክተር

የድሮ ነጭ ባለፀጉር

መሪ ነበር ወይ የእድሩ

ያኔ እማወቀው ነጥቶ ፀጉሩ

እንደኔ እንዲህ የወረረው

ቢያንስ ሥልጣን ቤት ነበረው

ወይ ደጃዘማች ፊት አውራሪ

ወይ ዳሪክተር አስተማሪ

ይሆን ነበር የጦር መሪ

ወይ ቀኝ አዝማች ባላምባራስ

ይሆን ነበር ወይም አጃንስ

ቢጠፋ እንኳን ሌላው ቢቀር

የእቁብ ዳኛ ይሆን ነበር

ወይም ቅቤ ማር ነጋዴ

ብር ማግኛ ያለው ዘዴ

የታወቀ ባለ ሆቴል

ባለ ጋራዥ ባለ ኦፔል

ይሆን ነበር ባለ ወፍጮ

ብዙ ሰጪ ለመዋጮ

ብዬ ሳስብ የኔ ሽበት

መንጨፍረሩ በባዶ ቤት

ያስቀኛል እንደዘበት

 

ወይ ተምሬ ጫፍ አልደረስኩ

ወይ ዘምቼ አልተመለስኩ

በኔው ሽበት እኔው አፈርኩ

መሿለኪያ ወይ ካሳንችስ

ገዳም ሰፈር ሀብተጊዮርጊስ

ደጃች ውቤ ስልከሰከስ

እዛ ስጭር እዛ ሳምስ

ቀን በጠላ ባዶ ግሳት

ማታ በጠጅ ከንቱ ኩራት

በትንባሆ በጫት ሃዚም

ተተብትቤ ስስለመለም

በየቦታው ስርመጠመጥ

የሰው ወሬ ሳገላብጥ

በኑሮዬ ሳልለወጥ

እንደገና ጊዜው ከፍቶ

አመጽ ሽብር ተበራክቶ

የወንድሜ ማህል አናት

ተበርግዶ ጥይት ከፍቶት

የእህቴ የፊት ፀዳል

ተጨማልቆ በደም መግል

ያን አይቼ በፍርሃት

ካንዱ ዘመድ ወዳንዱ ቤት

እህል ሳልቀመስ በባዶ እግሬ

ከልደታ እስከ አቧሬ

ከቡራዩ እስከ ጊዮርጊስ

ከላም በረት እስከ ሳሪስ

ከመርካቶ እጉለሌ

ከቃሊቲ እግንፍሌ

ከረምኩና ስንከራተት

ጨምሬበት ዳግም ስደት

እኔ ሆንኩኝ የዛ ውጤት

የታባቱ የኔ ሽበት

አዋረደኝ በባዶ ቤት

 

ለነገሩ በውጪ ሀገር

ጭራሽ የለም ጥቁር ፀጉር

መላጣውን ጌታ ወዶት

ገላገለው ከዚህ ሽበት

የሱ ደግሞ መጥፎ ችግር

ሲሸብት ነው ዳርና ዳር

ነፃ ወጥቷል ከዚህ ሴቱ

አለው ዘዴ በያይነቱ

 

አታርጉብኝ ብቻ ፍርጃ

ይወለዳል ነጭም ጥጃ

የማዝነው ግን የኔን ሽበት

ቢያደርግለኝ በሀገር ቤት

በማስታረቅ ባልና ሚስት

በበላሁኝ ስንት ሙክት

ሆኖ ቀረ እዚህ ከንቱ

የኔ ሽበት የታባቱ

እችል ነበር ልከልለው

እንዴት ከኔ ልሰውረው

እስከዛሬ ያልነጣችሁ

ካጉል ሽበት ያድናችሁ

ወይ ውለዱ ወይ ተማሩ

ነግዳችሁ ወይ ክበሩ

ላገራችሁ ወይም ሥሩ

ነጣጥታችሁ እንዳትቀሩ

ሽበት መጣ ደረሰብኝ

ምን ይሻላል እንዳትሉኝ

 

በቁርጥራጭ ሦስት መንግሥት

ስንገላታ ስንከራተት

ቱግ ብሎ በባዶ ቤት

ያስቀኛል የኔ ሽበት።

 

ከወለላዬ ሰኔ 26 ቀን 2000 ዓ.ም. ስዊድን

July 3, 2008 Sweden

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ