የነፃነት እልህ

ወለላዬ ከስዊድን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

(በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ) 

ነፃነትህ ጠፍቶ መብትህ ሲሸረሸር፣

ተስፋህን ሲያጠፉት እንዳትኖር በሀገር፣

ያለ የሌለውን እየቦጠበጡ፣

በደምህ ሲከብሩ በላብህ ሲያጌጡ፣

ጠረፍ ላይ ያለውን ያጥንትህን ችካል፣

ጠላት አስገብተው ነቃቅለው በመጣል፣

ሊኖሩ ካሰቡ ሥልጣን ላይ ባንተ ደም፣

ደንቆሮ ካረጉህ ያልገባው መኃይም፣

ዝም ብለህ አትይ ከህዝብ ጋር አብር

መሆንክን ተረዳ የሀገር ወታደር

 

እናቴ ኢትዮጵያ ሀገሬ ሀገሬ፣

የሚልን አሳደው አድነው እንዳውሬ፣

ሲያስሩ ሲያንገላቱ አይተህ አትደበቅ፣

ሁልህም ተነሳ ነፃነትን ጠይቅ።

 

እንዳለው ነዋሪ በምስራቅ በምዕራብ፣

የሚለይህ ሳይኖር አንተም የትግራይ ህዝብ፣

ከድህነት ወጥመድ ሳትወጣ ሳትርቅ፣

ሊያሞኙህ አስበው ቢሉህም አንተን ወርቅ

ተንኮላቸው ይግባህ በዝምታ አትኑር፣

ላገር መቆምህን በተቃውሞ አስመስክር

ሀገር ናት መኖርያህ ተራፊ ያንተ ቅርስ

በዘረኞች ወጥመድ ገብተህ አትታመስ

 

ግፈኛ ሥልጣኑን በህዝብ ሲነጠቅ

ለትግሉ ምን ሠራሁ ብለህ ከመሳቀቅ

ላገር መቆምህን አሁኑኑ አሳውቅ

አለማንም ግፊት ጥሪና ና ውጣ፣

በስምህ ሲነገድ ይጫርብህ ቁጣ።

 

የሰው ልጅ ሲነጠቅ ነፃነቱን ሲያጣ፣

‘እንብየው!’ ካላለ ነፍሱ ካልተቆጣ፣

ጥርጥር ይከታል እንዳለው እስትንፋስ፣

መውጣቱ መውረዱ ደሙ አናቱ ድረስ።

አንተን መሳይ ፍጡር ሆዱን ስላሰፋ፣

ነፃነት ሲነፍግህ እያየህ በይፋ፣

ውርደት አትቀበል አንገትክን አትድፋ።

 

የነሱ ልጅ ደልቶት ተንደላቆ እንዲማር፣

ሜዳ አዳሪ እንዲሆን የኛ አበሳ እንዲቆጥር፣

እኛ ስንጨነቅ አጥተን ሙሉ ጤና፣

እነሱ እንዲያገኙ የሞላ ሕክምና፣

እኛ ስንራቆት እነሱ እንዲያጌጡ፣

ሽሮ አሮብን ሳለ ጮማ እንዲያማርጡ፣

በተንጣለለ ቤት ውስጡ በተሟላ፣

ህዝብ እያራቆቱ እንዲኖሩ ቪላ፣

በምንም ሁኔታ በፈለገው መንገድ፣

ዓይናችን እያየ የለብንም መፍቀድ።

 

ሕግና ዳኝነት ዲሞክራሲን ገፈው፣

ሰብዓዊ መብትን ከህዝብ ላይ ነጥቀው፣

ያገርን በረከት የተፈጥሮን ሲሳይ፣

እነማን ሆነው ነው? የሆኑብን ከልካይ።

ማን ስለሆኑ ነው? ባገር ላይ እነሱ፣

እንደፈለጋቸው ‘ሚገድሉ ‘ሚከሱ?

በነፃነታችን ይብቃቸው ማላገጥ፣

በእሺታ አንኑር እንቢታን እንምረጥ።

 

ከዳኝነት ማጣት ከፍትህ ሰቀቀን፣

ከችግር ከስቃይ ከረሃብ ለመዳን፣

በአንድነት ተነስተን መታገል አለብን።

‘ይሁን እስቲ!’ እያለ አንገቱን የደፋ፣

ነፃነቱን ሊያገኝ አይኖረውም ተስፋ።

እንዳን እንውጣ ከጎመን በጤና፣

ይታየን መብራቱ የነፃነት ፋና።

የተነጠቅነውን የነፃነት ሲሳይ፣

ማስመለስ አለብን መንጭቀን ከበዳይ።

 

ነፃነትን ናፍቀን ከያዝነው ትንቅንቅ፣

ብንቆስል ብንደማም እሜዳ ብንወድቅ፣

ከትግሉ ጎዳና የለብንም መራቅ።

አዝኖና ተክዞ እቤት ከተገባ፣

ሲንፏቀቅ ይከርማል ትግሉ ሆኖ ሽባ።

ስለዚህ ትግላችን እንዲታይ በጉልህ፣

በልባችን ይጫር የነፃነት እልህ።


 

ወለላዬ ከስዊድን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

ሰኔ 16 ቀን 2001 / June 23, 2009

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ