ምርጫው የማይከበርለት ሕዝብ እንዴት “ምረጠኝ” ይባላል? (ሀብታሙ አሰፋ)
ሀብታሙ አሰፋ
የአቶ መለስ አስተዳደር ደጋግሞ እንደተናገረው የ97ቱ ምርጫ እንዳይደገም ቀዳዳዎችን ሁሉ ደፍኗል። እነዚህ ቀዳዳዎች የታወቁ ናቸው። ምርጫ እንዳይኖር የሚያደርጉ የአፈና እርምጃዎችን ነው። ይቃወሙኛል የሚላቸውን ሁሉ በሞትና በእድሜ ልክ እስራት የሚቀጣበት የፀረ-አሸባሪነት ሕግ አውጥቷል። ከዚህ አልፎም ሕጉ በነማን ላይ እንደሚሰራ እነ ጀነራል ተፈራ ማሞ በፈጠራ ወንጀል በዚሁ አዋጅ መሰረት ተፈረዶባቸዋል። በ97ቱ ምርጫ በገለልተኝነት የታዘቡ የሲቪል ማህበረሰቡን የሚወክሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ፀጥ የሚያደርግ አዋጅ ወጥቷል። የፕሬስ ነፃነት ተስፋ ጭምር እንዲጨልም የዘጋውን ዘግቷል። ያሰጉኛል የሚላቸውንም የቀሩትን ለይቶ ተራ በተራ ለመጨፍለቅ ዘመቻ ይዟል። ተቃዋሚዎችን ለመከፋፈል የጀመረው ዘመቻ ከቅንጅት ውህደት ተቃውሞ ተነስቶ አጋር ተቃዋሚዎች እስከማፍራት ሄዷል።
የመከላከያ ሰራዊቱን በአንድ ጎሳ የበላይነት አዋቅሮ ጨርሷል። ደህንነቱንም በተመሳሳይ የሚመራ ነው። የቀሩትም ዋና ዋና መንግስታዊ ተቋማት የክልል ይሁኑ የፌዴራል የዘረኛውን ስርዓት የስልጣን ባለቤትነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ተዋቅረዋል። የዚህ ሁሉ ድምር ወያኔና የወያኔን ይሁንታ ያገኘ ብቻ የአገዛዙን ትእዛዝ እየተቀበለ እንዲኖር ማድረግ ነው።ምርጫ ብሎ ይሕንን መዋቅር መለወጥ የለም ማለታቸው ነው።
ፍርድ ቤት ከመቼውም ጊዜ በላይ የአገዛዙ ሰዎች ይሉኝታ ባጣ ሁኔታ የሚጫወቱበት ተቋም ሆኗል። ህብረተሰቡ ይቅር ስርዓቱ ቀጥተኛ ፍላጎት ባለው እንደ ምርጫ ጉዳይ ይቅርና አንድ የስርዓቱ አገልጋይን በፍ/ቤት ተሟግቼ እረታለሁ ብሎ አያምንም። ፍትህ ሞቷል ። ዳኝነት የለም። ለዚህ ይመስላል አንዳንድ ካድሬ ዳኞችን "የፍርድ ቤቱ አጋዚ" ማለት የጀመረው።
ምርጫ ቦርድ በገዥው ቡድን ታማኝ ግለሰቦች ከላይ እስከታች የተዋቀረ ነው። በ97 ምርጫ ወቅት በምርጫ አስፈፃሚነት ኢህአዴግ መድቧቸው ድምጽ ቆጥረው ተቃዋሚዎች አሸነፉ ብለው ወረቀት ከሰጡ ብዙዎቹ ተለቅመው ተባረዋል። ሌላው ቀርቶ ወደ መደበኛ ስራቸው እንዳይመለሱ የተደረጉ መኖራቸው ጭምር የአደባባይ ሚስጥር ነው።አብረው ድምጽ የዘረፍ ተሹመዋል ተሸልመዋል። ዛሬ ቀርቶ በቀደመው ምርጫ እንኳ የህዝብ ታዛቢ የሚባሉት ኢህአዴግን የሚደግፉ አባላቱና ደጋፊዎች ነበሩ።
በኢትዮጵያ ባለው ተጨባኝ ሁኔታ ቅድሚያ መጠየቅ ያለበት ምርጫ ነው ወይስ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ስርአት የሚለው የግድ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው። ተቃዋሚዎች በነፃ መንቀሳቀስ አልቻሉም። ለምርጫ እጩነት ሊያቀርቡ ያዘጋጁዋቸውን ጨምሮ ሌሎች አባላቶቻቸውም በፈጠራ ወንጀል እየታሰሩ ነው። የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ዛሬም የአቶ መለስን ድምፅ ብቻ የሚያሰሙ የፕሮፓጋንዳ ማሽኖች መሆናቸውን ቀጥለዋል። የህዝብ ድምፅ ፈፅሞ የሚሰማበት እድል የለም። የፕሬስ ነፃነትን በመጋፋት በርካታ የነፃ ፕሬስ ጋዜጦችን በጉልበት አግደዋል። የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር በጉልበት ተዘግቷል። በየምሽቱ በሚደረገው ጸረ-የፕሬስ ነጻነት ፕሮፖጋንዳ በምርጫ 97 ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት ፕሬሶችን በተለመደ ፈጠራ ክስ በዘመቻ መወንጀል አልቆመም። ባለፉት ሁለት አመታት ፈራ ተባ እያሉ አማራጭ ሀሳብ ለመሰንዘር የሞከሩ ሳይቀሩ በአሸባሪነት ተወንጅለዋል። በተጽዕኖ ከተዘጉት አልተማሩም በተባሉት ላይም የማያዳግመው አብዮታዊ እርምጃ ይቀጥላል የሚል ማሸማቀቂያ አልቆመም።
ዛሬ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያስቡት ጭምር አስረግጠው እንደሚናገሩት ምርጫው ህዝቡ ሳይመርጥ የተጠናቀቀ ነው።የህዝቡ ድምጽ የማይከበርበት የምርጫ ሂደት መሆኑን እያወቁ ለምን ህዝቡን ድምጽ ስጠን ይሉታል? በተጭበረበረ ምርጫ የአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ተስፋ አይለመልምም። ያ ቢሆን ኖሮ ከ97 ታሪካዊ ምርጫ በኋላ ዛሬ የደረስንበት የበለጠ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ባልወደቅን ነበር። ያሁሉ የንጹሀን ደም ፈሶም ነጻ ተቋማት ስለሌሉ ገዳዮች ዳግም ምርጫ የሚያጭበረብሩበት ስርአት አለ።
ሀሳባቸውን ለመግለጽ የሞከሩት ዜጎች በፈጠራ ወንጀል እየተከሰሱ፣ በነፃ የሚዳኙበት ፍ/ቤት ተነፍጎ ሞትና እድሜ ልክ በሚፈረድባቸው አገር እንደምን ያለ ምርጫ ይደረጋል? ከዚህ መሰሉስ የምርጫ ሒደት ምን ውጤት ይገኛል? “ምርጫ ግቡ” የሚሉ ወገኖችን ጨምሮ “ምርጫ እንግባ” ሚሉትም ይሄን ለህዝብ በበቂ የማስረዳት ግዴታ አለባቸው።
ተቃዋሚነት እንጀራ ወይም የስራ መስክ መሆን የለበትም። የሚደግፈኝ ህዝብ ደገፈኝ አልደገፈኝ በአደባባይ የተስፋ ዳቦ እየመገብኩ በተቃዋሚነት እቀጥላለሁ ማለት በትልቁ ጥያቄ ያስነሳል። የአገሪቱን ሕዝብ የዴሞክራሲ ተስፋ የሚያጨልም ሕገ-መንግስት እየረገጠ ሕግ በሚያወጣ ፓርላማ አንድና ሁለት ተቃዋሚ ገብቶ የሚጮህበት ስርዓት ምርጫ አይባልም።
በ97 ታሪካዊ ምርጫ ሕዝቡ ድምጼ፡ ተዘርፎ ልጆቼ ተገድለው ፓርላማ እንዳትገቡ አለ። ብዙዎች ፓርላማ አንገባም ያሉትን ተራምደው ወደ ፓርላማ ገቡ። አንዳንዶች እየተደበደቡ ያለፍላጎታቸው ገብተው ተቀመጡ። ፓርላማው በአምስት ዓመት የስራ ቆይታው ምን ሰራ? እኛ ሳንሆን ራሳቸው ፓርላማ የገቡት ተቃዋሚዎች ሳይቀር ገብተን ያመጣነው ውጤት የለም ብለዋል።እነሱ ፓርላማ ስለገቡ የወጡትን የአፈና አዋጆች አላስቀሯቸውም። የሕዝብ ሕይወት የተገበረበት ምርጫ የስልጣን ጥም ባሰከረው የአቶ መለስ ቡድን ተይዞም ከአምስት ዓመት በኋላ የተለወጠ ነገር የለም።ዛሬም ምርጫው ለዚሁ ህገ ወጥ ቡድን ህጋዊ ሽፋን ከመስጠት ያለፈ ጥቅም ለአገሪቱም ሆነ ለህዝቡ የለውም።
ታዲያ ለምንድነው ተቃዋሚዎች አስቀድሞ ውጤቱ በታወቀ የይስሙላ ምርጫ እንዲገቡ የምንገፋቸው? ተቃዋሚ ሲባል በትክክል አማራጭ ሐሳብ አቅርበው ከገዥው ፓርቲ የሚለዩትን እንጅ ማለያቸውን ቀይረው ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በምርጫው እንወዳደራለን ያሉትን አይጨምርም። እነዚህን ወገኖች በተቃዋሚነት እንደማይመለከት ሕዝቡ በየአጋጣሚው ሃሳቡን ከገለፀ ቆይቷል።
አቶ መለስ ያሸነፉትን የምርጫ ቴአትር ከነልደቱ ጋር በማድረጋቸው ምእራባዊያን ምርጫ እንደተደረገ ስለሚቆጥሩ ቢያንስ የቀሩት ይሳተፉ ማለት በቂ መከራከሪያ አይደለም።ምራባውያን በጠራራ ጸሐይ የሕዝብ ድምጽም ሲሰረቅ አይተዋል። ከምስክርነት ያለፈ ሊያደርጉልን የቻሉት ነገር የለም።ቁልፉ ያለው በሕዝቡ እጅ ነው። የሚሳተፉትም እውነት ይሔ ምርጫ ወደተፈላጊው የለውጥ ጎዳና ይወስደናል ወይስ አይወስደንም ብለው በቂ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። የሕዝቡን የለውጥ ተስፋ የሚያዳፍን ምርጫ መሳተፍስ ጠቀሜታው ለማን ነው?
በ97ቱ ምርጫ እንደታየው አንዳንዶች ተገደው፡ አንዳንዶች ፓርቲያቸው ከሚጠፋ ሕዝቡ የሰጠው ድምፅ ተዘርፎ፡ የተገደለውም ሆነ ተመርጦ የሞተውም ሞቶ ፓርላማ ገብተዋል። የቀሩት ደግሞ አዲስ ሰልፍ አሳማሪ ሆነው የአብዮቱን ጎራ ተቀላቅለው የመረጣቸውን ሕዝብ ከገደለ ጋር ቆመው መርገም ይዘዋል።
በዚህ የ2002 ምርጫ ያለመሳተፍ ቀላል የማይባል ፈተና ነው። እነ መለስ መታጀብ ይፈልጋሉ። የማይፈልጉት የሕዝብ ድምጽ ተዘረፈ መባልን ነው። የጠሉት ነጻ ምርጫ አይደለም የሚሉትን ነው። ስለዚህ የእውነተኛ ተቃዋሚዎች በዚህ ቴያትር አለመሳተፍ የሚጎዳው እነመለስን ብቻ ነው። ተቃዋሚዎቹ ባይሳተፉ ቀጣይ ትግላቸው ትክክለኛ ምርጫ የሚደረግበት ስርዓት ይኑር ማለት እንጂ የተጭበረበረ ምርጫ ውጤት ተቀበሉ አትቀበሉ የሚል አታካራ አይደለም።
ዘንድሮ በምርጫው አይግባ ወይም ይግባ የሚባለው መድረክ አመራር የሕዝብ ድምፅ ተዘርፎ ፓርላማ አንገባም ብለው መከራ የተቀበሉትንም፣ ድርጅቴ ከሚዘጋ ወደ ፓርላማ እገባለሁ ያሉትንም፣ ፓለቲካ እንጀራዬ ስለሆነ የመረጠኝ ሕዝብ ሞተ አልሞተ በተቃዋሚነት እቀጥላለሁ ያሉትም፣ ምርጫውን በሩቅ የታዘቡትም እና በግል ጭምር የሚንቀሳቀሱትን ያቀፈ ነው።
መድረኩ የአቶ መለስ አስተዳደር የትኛውንም ተፅእኖ ቢያደርግ ምርጫ ከመግባት ይቀራል ብዬ ደፍሬ መናገር አልሞክርም። የመድረኩ ጥቂት ድርጅቶች በተናጠል እንግባ ወይም አንግባ ቢሉም ውጤቱ የተለመደውን መከፋፈል ያመጣል። ሁሉም ደግሞ ምርጫውን አንግባ ብለውም አይወስኑም። ወያኔ ጨዋታውን ቀጥሎ ገና ከመነሻው ከተቃዋሚዎቹ መሐከል እኔ የመረጥኩላችሁ ዕጯችሁ ካልሆነ አልመዘግብም እያለ ጭምር ነው። ነገሩ ሲገፋ ፓርቲዎቹ ምርጫውን አንሳተፍም ቢሉም ዕጩዎች ተገደው በአጃቢነት እንዲቀጥሉ ከማድረግ አይመለሱም። ፓርቲዎቹ እንግባ ሲሉ ደግሞ በእጩነት ካስመዘገቡዋቸው የተወሰኑት በግዴታ ራሳቸውን በአስሯአንደኛው ሰዓት ከተወዳዳሪነት እንዲያገሉ ይደረጋል። ይሔ በሁሉም የምርጫ ቴያትሮች የተለመደ ነው።
ሕዝቡ ምርጫ ቢኖረውና ድምፅ የሚከበርበት ስርአት ቢኖር መድረኩ የማይናቅ የህዝብ ድጋፍ ሊያገኝ ይችል ነበር። እነ አቶ መለስ ጡንቻቸውን አጠንክረው ገና ከአሁኑ አጥፍቶ ጠፊ እያሉ የአሸባሪነት ቀለም እየቀቡት ነው። ለአፈና ስርአቱ መድረኩ ምርጫ ገባ አልገባ ውጤት አያመጣም። ምርጫ ቆርጦ ከገባ የተጭበረበረውን የምርጫ ውጤት የመቀበል ግዴታ አለበት። ያንን ካላደረገ በእብሪት እንደሚሉት የፈንጅ ወረዳ ስላለፈ የተወሰኑት መሪዎች ወይ የኦነግ፣ ወይ የግንቦት ሰባት ወይ የአርበኞች ግንባር፡ የአገር ክህደት ወይ አመጽ አደራጅ የሚል ታርጋ ተለጥፎባቸው እስር ቤት ይገባሉ። ከመሀል የተወሰኑ አባሎቻቸው ድርጅታቸው ላይ እንዲዘምቱ ይደረጋል። በዚህ ሳይሸነፍ እስከመጨረሻ ሕዝቡ ለኔ ድምጼን ይስጠኝ፣ የሰጠው ድምጽም በአግባቡ አልተቆጠረም፣ ውጤቱ ተጭበርብሯል ያለ ሰለባ ይሆናል።
የአገሪቱን ሕዝብ የሚጠብቁ ነፃ ተቋማት መከላከያ፣ ፓሊስ፣ ደህንነት ፍ/ቤት፣ ሚዲያ፣ ምርጫ ቦርድ ፓርላማ በሌሉበት መቅደም ያለበት የቱ ነው? ብሎ ቆም ብሎ መጠየቅ የግድ የሚልበት ወቅት በሕዝቡ ከታመነበት ቆይቷል።
በምርጫ 2002 እነ አቶ መለስ ብቻቸውን ተመራጭም አስመራጭም ታዛቢም ሆነው በሂደቱ እንዲሳተፉ መፍቀድ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ከዚህ የሚገኘው ውጤት ያለ ነፃ ተቋማት በሚደረግ ምርጫ መሳተፍ በተዘዋዋሪ የአፈና ስርዓቱ በያዘው እርምጃ እንዲቀጥል መፍቀድ መሆኑን ማሳየት ነው።ድርድሩ የፖለቲካ ትግሉም አብይ ጥያቄ ተቋማቱ ይቅደሙ መሆን አለበት። ይሔ ሳይሆን መሳተፉ ከረጅም ግብ አኳያም የአገሪቱን የዴሞክራሲ ትግል አያግዝም። በ97 ምርጫና ተያያዥ ጉዳዮቹ ብቻ ሳይሆን ከአምስት አመት በኋላ አገሪቱ ያለችበት ዘረኛ የአፈና ሥርዓት ያረጋገጠው ሐቅም ይሔንኑ ነው።
ምርጫ ካልተገባ የአገሪቱ ሕዝብ ሀብትና በስሙ መጥቶ ምርጫ ቦርድ ኪስ የገባው የምርጫ ማካሔጃ ገንዘብ አይሰጥም። ከሕዝብ መብት ይልቅ የገንዘብ ክፍፍል ጉዳይ ላስቀደሙ ልደቱን መሳዮች በምርጫው ለመሳተፍ ዋስትናቸው ገንዘብ ማግኘት ብቻ ነው። በሐቅ ሕዝቡን ለዴሞክራሲ ጥያቄ ታግለን እናታግላለን ለሚሉት ግን ጥያቄው የሚመለስበትን የተዘጋ በር ለማስከፈት ትግልን መቀጠል ወይስ በሩ ይዘጋ ከበሩ ውጭ ትግላችንን እንቀጥላለን ማለት ነው? ከመሰረታዊ ጥያቄ ያፈነገጠ ትግል የጠቀመው ገዳዮችን ብቻ ነው።
ምርጫ 2002 ለሕዝቡ የሚታገሉ ተቃዋሚዎችን ፓለቲካ እንጀራዬ ነው ከሚሉት የሚለዩበት ነው። ውጤቱ አስቀድሞ ለታወቀው ምርጫ አጃቢ መሆን በየትኛውም መስፈርት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማምጣት የሚደረገውን ትግል አያግዝም።
የሕዝቡን ሐሳብ በሐቅ ያነገቡ ተቃዋሚዎች ምርጫ መሳተፍ እንፈልጋለን፡ የምንሳተፈው ግን ሕዝቡ መምረጥ የሚችልበት ነጻ ተቋማት ሲመሰረቱ ነው ማለት አለባቸው። ለፍርድ ቤት ነፃነት ሳይቆሙ ነፃ ላልሆነ ፍርድ ቤት ነገ ምርጫ ተጭበርብሯል ብለው ክስ ሊያቀርቡ ነው? ይሔ በዚህ ፍርድ ቤት በፈጠራ እንዲወነጀሉ ሌላ እድል ለወያኔ መስጠት ነው። ምርጫው የማይከበርለት ሕዝብስ ለምን ምረጠኝ ይባላል? ምርጫው የሚጠቅመው ዕውን ሕዝቡን ነው ወይስ አስቀድመው ራሳቸውን መርጠው ያስቀመጡትን ገዢዎች? መልሱ የታወቀ ነው። አስቀድሞ በተጭበረበረ የምርጫ ስርዓት የተጠቀመ ሕዝብ የለም። ተቃዋሚዎችም ከህዝቡ ጋር ታግለው ሊያስፈቷቸው የሚገቡ የፖለቲካ እስረኞችን ጉዳይ አብይ አጀንዳ ሳያደርጉ ራሳቸው የፖለቲካ እስረኛ መሆን የለባቸውም።በምርጫው በመሳተፍ በፈጠራ ተወንጅለው እንዲታሰሩም ሆነ የሚገደሉበትን ስርአት ከወዲሁ መፍቀድ የለባቸውም።



