ሀብታሙ አሰፋ

በምርጫ 97 የህዝብ ድምፅ ከተሰረቀ በኋላ ሥርዓቱ ያሰጉኛል ያላቸውን ሁሉ እያሳደደ ያጠቃ ነበር። ዳንኤል በቀለ “አክሽን ኤድ” የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከኃላፊዎቹ አንዱ ነው። በሙያው የሕግ ባለሙያም ጭምር ነው። ምርጫውን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች ከሚሰጡ ምሁራን አንዱ ነበር። ሃሳብን መግለፅ ወንጀል በመሆኑ የእነ አቶ መለስ ደህንነቶች ከሚያሳድዷቸው ዜጎች አንዱ ይሆናል።

 

ዳንኤል አንድ ምሽት የሴት ጓደኛውን አዲሱ ገበያ አካባቢ በመኪናው ሸኝቶ ሲመለስ መሣሪያ የታጠቁት የአቶ መለስ ማጅራት መቺዎች ያስቆሙና “አንተነህ እንዴ ኢህአዴግን የምትቃወመው?” እያሉ በሽጉጥ ሰደፍ ይደበድቡት ገቡ። አሸብረነዋል ብለው ሲወስኑ ጥለውት ይሄዳሉ። ማምሻውን ጨለማ ለብሰው የፈፀሙትን ከነ ንግግራቸው ዳንኤል ይፋ ያደርጋል።

 

ዜናው ከሀገር ውስጥ አልፎ በዓለም ተሰራጨ። በወቅቱ የኢህአዴግ የምርጫ ኃላፊ የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን ምክትል ታደሰ ካሣ (ጥንቅሹ) አደባባይ ይወጣና “ዳንኤልን ለምን እንመታዋለን፤ እሱማ ተቃዋሚዎች ፓርላማ ይግቡ የሚል ስለሆነ የመቱት ቅንጅቶች ናቸው” አለ። የኛ ደጋፊ ነው ሃሳቡ ይስማማናል ማለቱ ነበር። ይሄው አስተያየት የደህንነቱ ልሳን በነበረው በቀድሞዋ የቪኦኤ ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ በሚታተመው ኢፍቲን ጋዜጣ ታትሞ ወጣ።

 

ዳንኤልን ስለ ጉዳዩ ቃለመጠይቅ አድርጌለት በሰጠኝ አስተያየት “እንዲህ አይነቱ የውንብድና ተግባር ሊቆም ይገባል” ብሎ ነበር። የተመኘው ሳይሆን ቀርቶ ዳንኤልም የቅንጅት መሪዎች፣ የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች እና የመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ሲታሰሩ ታሰረ። ሲፈታ ዘግይቶ ከነፃነት ደምሴ ጋር ተፈታ። እነ አቶ በረከት ያኔም ማጅራት እየመቱ አንዴ አባላችን ነው፤ ሌላ ጊዜ ደጋፊያችን ነው ማለታቸውን ቀጥለው፤ የገደሏቸውን ንጹኀን ቤተሰቦች ሳይቀር ቅንጅት ነው የገደለው ብላችሁ ፈርሙ ለመሣሪያ ክፈሉስ ብለው አልነበር።

 

ያ በሆነ በጥቂት ቀናት ልዩነት ሌላ ተፈላጊ ሰው ማጅራቱን ተመታ። ዳንኤልን ሲመቱት “አንተነህ ወይ ኢህአዲግን የምትቃወመው?” ማለታቸውን አስተካክለው የቪኦኤ ጋዜጠኛ የሆነውን መለስካቸው አምሃን ከታክሲ ከወረደ ጀምሮ ከጀርባው ሲከተሉ ቆይተው ቤቱ ሊገባ ጥቂት ሲቀረው አፍነው በድንጋይ ጭንቅላቱን ደጋግመው ፈነከቱት። ይህን ሁሉ ሲያደርጉ አንድ ቃል አልተነፈሱም።

 

መለስካቸው ጭንቅላቱን ክፉኛ ተጎድቶ ስለነበር ሆስፒታል ሔደ። በወቅቱ እንዳየሁት ጭንቅላቱ ሙሉ ለሙሉ በፋሻ ተጠቅልሎ ነበር። በዚህ አልበቃቸው ብሎ በማግስቱ ፌደራል ፖሊሶች ቤቱ ይሄዱና ይዘውት ጣቢያ ይሄዳሉ። እዚያ ማን እንደመታው ይጠይቁታል። ገና ለገና መቱኝ እንዳይል ማስፈራሪያ ነበር። የመቱትን መፈለጉ የፖሊስ ሥራ መሆኑ ቀረና ለምርመራ ታስሮ ተጠያቂው ተበዳይ ሆነ። ዜናው ባልታወቁ ሰዎች ተመታ ተብሎ ተሰራጨ። ዛሬም ድረስ ማጅራት መምታታቸውን አላቆሙም። የፖሊስ ኃይሉም እንደ ፓርላማው፣ መገናኛ ብዙኀን፣ ፍርድ ቤት፣ መከላከያ፣ ምርጫ ቦርድ፣ ደህንነት ገለልተኛ ስላልሆነ ማጅራት እየመታና ለማጅራት መቺዎች ከለላ እየሰጠ የዜጎችን መብት ይረግጣል።

 

በያንሳ ዳባ የተቃዋሚ ድርጅት አባልና የምርጫ ቀስቃሽ በመሆኑ በሥርዓቱ ሚሊሻዎች በመሣሪያ ተደብድቦ በጽኑ ቆስሎ ሲታከም ቆይቶ ሕይወቱ አለፈ። ትግራይ ውስጥ በግፍ በጩቤ ተወግተው ከተገደሉት የመድረኩ/ዓረና የምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪ አቶ አረጋዊ ገብረዮሐንስ ጋር ሁለተኛው በነ አቶ መለስ ማጅራት መቺዎች የተገደለ መሆኑ ነው። ጅማ ላይ በጩቤ የተወጋው ሌላው የመድረኩ አባል እና በየቦታው እየተደበደቡ ያሉት ጉዳይ መጨረሻው አልታወቀም። ማጅራት መምታቱም ሆነ ግድያው ግን የሕግ የበላይነት እስካልተረጋገጠ ድረስ አንዴ በጥይት፣ ሌላ ጊዜ በጩቤ በጥይት ብቻ በተፈለገው መልኩ አፋኞቹ እስካሉ ቀጣይ መሆኑን ያሳያል።

 

እነ በረከት የአቶ አረጋዊን ሞት የመጠጥ ቤት ግጭት ሲሉ ከርመው የበያንሳን ሞት ደግሞ ወባና ተስቦ፤ አባልነቱንም የኢህአዴግ ነው ብለዋል። የሥርዓቱን አፀያፊ ወንጀልና መሰል ማጅራት መቺነት ለሚያውቁት ሰዎች ነገሩ አዲስ አይደለም። የተለመደ ቅጥፈት ነው።

 

በኢትዮጵያ የእነ አቶ መለስ ዘረኛና አምባገነናዊ ሥርዓት ፈቅዶ የሚደረግ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ የለም። ለነፃ ምርጫ የሚያበቁ ነፃ ዲሞክራሲያዊ ተቋማትም የሉም።

 

ከወራት በፊት “ምርጫው የማይከበርለት ህዝብ እንዴት ምረጠኝ ይባላል?” በሚል ርዕስ በፃፍኩት አንድ ጽሑፍ ምርጫውን ተከትሎ እነ አቶ መለስ ስለወሰዱትና ሊወስዱት ስለሚችሉት የአፈና እርምጃ የተወሰኑ ሃሳቦች ሰንዝሬ ነበር። ያንን አልደግመውም። በዚያ ጽሑፍ ማጠቃላያ ግን ስለ ምርጫ መግባትና አለመግባት አንድ ሃሳብ አንስቼ ነበር።

 

“በዚህ የ2002 ዓ.ም. ምርጫ ያለመሳተፍ ቀላል የማይባል ፈተና ነው። እነ መለስ መታጀብ ይፈልጋሉ። የማይፈልጉት የህዝብ ድምፅ ተዘረፈ መባልን ነው። የጠሉት ነፃ ምርጫ አይደለም የሚሉትን ነው። ስለዚህ የእውነተኛ ተቃዋሚዎች በዚህ ቴአትር አለመሳተፍ የሚጎዳው እነ መለስን ብቻ ነው። ተቃዋሚዎቹ ባይሳተፉ ቀጣይ ትግላቸው ትክክለኛ ምርጫ የሚደረግበት ሥርዓት ይኑር ማለት እንጂ የተጭበረበረ ምርጫ ውጤት ተቀበሉ አትቀበሉ የሚል አተካራ አይደለም። …”

 

“ህዝቡ ምርጫ ቢኖረውና ድምፁ የሚከበርበት ሥርዓት ቢኖር መድረኩ የማይናቅ የህዝብ ድጋፍ ሊያገኝ ይችል ነበር። እነ አቶ መለስ ጡንቻቸውን አጠንክረው ገና ከአሁኑ አጥፍቶ ጠፊ እያሉ የአሸባሪነት ቀለም እየቀቡት ነው። ለአፈና ሥርዓቱ መድረኩ ምርጫ ገባ አልገባ ውጤት አያመጣም። ምርጫ ቆርጦ ከገባ የተጭበረበረውን የምርጫ ውጤት የመቀበል ግዴታ አለበት። ያንን ካላደረገ በእብሪት እንደሚሉት የፈንጅ ወረዳ ስላለፈ የተወሰኑት መሪዎች ወይ የኦነግ፣ ወይ የግንቦት ሰባት፣ ወይ የአርበኞች ግንባር፣ የሀገር ክህደት፣ ወይ አመፅ አደራጅ የሚል ታርጋ ተለጥፎባቸው እስር ቤት ይገባሉ። ከመሃል የተወሰኑ አባሎቻቸው ድርጅታቸው ላይ እንዲዘምቱ ይደረጋል። በዚህ ሳይሸነፍ እስከመጨረሻ ህዝቡ ለኔ ድምፁን ይስጠኝ፣ የሰጠው ድምፅም በአግባቡ አልተቆጠረም ውጤቱ ተጭበርብሯል ያለ ሰለባ ይሆናል። …”

 

በዚያ ጽሑፍ አበክሬ ለመጥቀስ የሞከርኩት የዘንድሮ ምርጫን አስመልክቶ ራሳቸው ተቃዋሚዎች የሚጠቅሷቸውን ችግሮች ነበር። ሥርዓቱ ምርጫውን ለማፈን የወሰዳቸውን የተለያዩ የአፈና እርምጃዎች ጠቅሻለሁ።

 

ዛሬ እነ አቶ መለስ ብቻቸውን በሚሮጡበት ምርጫ አጭበርብረው ማለፋቸውን እርግጠኛ ናቸው። በዚህ ምርጫ ላይ ተሳትፌ የህዝብ ድምፅ አስከብራለሁ የሚል እውነተኛ ተቃዋሚና በhገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መምጣት አለበት ብሎ የሚደግፍ አላጋጠመኝም።

 

በምርጫው ዋዜማ እንደምናየው እነ አቶ መለስ ማጅራት መምታቱን አጠናክረው ይዘውታል። በሀገር ውስጥ አንድም ገለልተኛ የምርጫ ታዛቢ አለመኖሩን በአፈና አዋጃቸው አረጋግጠዋል። ነፃ መገናኛ ብዙኀን የለም።

 

የደረሰባቸውን ሙከራ የተናገሩትም ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው። በሥርዓቱ ማጅራት መቺዎች ሳቢያ ሕይወታቸው ያለፈውን የሁለቱንም ንፁኀን ጉዳይ አቶ መለስ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ አይፈቅዱም። ምርጫ ቦርድ ያጣራ ብለዋል። ምርጫው ከምርጫው ቀን በፊት ጀምሮ ማጅራቱን የተመታው ምርጫ ተጭበርብሯል ሲባል የሚጣራው በዚሁ መንገድ ነው። ገለልተኛ ያልሆነውን ቦርድ ውሳኔ አለመቀበል ፍትሃዊ ቢሆንም ይህን ማለት መንግሥት መገልበጥ ነው።

 

እውነተኛ ተቃዋሚዎች ምርጫውን ላለመሳተፍ አለመወሰናቸውን ብቻ ሳይሆን ጨርሶም እንሳተፍ ወይስ አንሳተፍ ብለው አልተወያዩበትም። የእነ አቶ አረጋዊ ግድያ በገለልተኛ አካል ይጣራ የሚል ተቃዋሚ ነገ ምርጫው ተጭበርብሮ ምርጫ ቦርድ ላጣራ ቢል ምላሹ ተመሳሳይ ነው የሚሆነው።

 

የይስሙላ ምርጫውን ለማጅራት መቺዎቹ ብቻ መልቀቅ ግን ዲሞክራሲያዊ ትግሉን ያግዛል። በአንድ በኩል በተጭበረበረ ምርጫ በመሳተፍ ለሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ቅንጣት አስተዋፅዖ ማድረግ እንደማይቻል በምርጫ 97 ብቻ ሳይሆን በእስካሁኑም ሂደት የታየው ግልፅ አድርጓል።

 

በሠላማዊ ትግል ማመንና ሠላማዊ ትግልን መከተል ማለት የግድ አስቀድሞ በግልፅ በተጭበረበረ የምርጫ ሂደት መሳተፍን አይጠይቅም። ትግሉ የሀገሪቱን ዲሞክራሲያዊ ሂደት ለማጎልበትና ህዝቡን አታግሎ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት ሥርዓት ለመገንባት ከሆነ በዚህ ምርጫ መሳተፍ ከዚህ ግብ አያደርስም።

 

ለሕግ የበላይነት የቆሙ፣ በከንቱ ደማቸው የፈሰሰውን ንፁኀን ጉዳይ የሚያሳስባቸውና ለህዝቡ ጥቅም ለቆሙ ወገኖች በሙሉ ሂደቱን አጢነው ፈጣን ውሳኔ መስጠት አለባቸው። ምርጫውን ረግጦ አለመውጣትና በዚህ አስቀድሞ ውጤቱ በታወቀ ከሂደቱ ጀምሮ የተጭበተረበረ ምርጫ መሳተፍ ለእነ አቶ መለስ ድል ነው። እነሱ እስካሉ ድረስ የገደሉትን እየገደሉ ምርጫ እያጭበረበሩ ለራሳቸው ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የሚያደርጉትን ሩጫ በተዘዋዋሪ መንገድ ማገዝ ነው። የጥቂት ተቃዋሚዎች (አዲሶቹን የአቶ መለስ አጋሮች አይመለከትም) የስም ፓርላማ መግባት የሚለውጠው ነገር የለም።

 

ሕጋዊና ሠላማዊ ትግል ማለት ሕገ ወጥ ምርጫን ውጤት መቀበልን አይጠይቅም። አስቀድሞ በተጭበረበረ ምርጫ መሳተፍም ማለት ሊሆን አይችልም። የብዙ የተጭበረበሩ ምርጫዎች ድምር አንድ ቀን ለሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አያመጣም።

 

መጭበርበሩ አስቀድሞ እርግጠኛ በሆነ ምርጫ ተሳትፎ ኋላ የምርጫው ውጤት ይከበርልን ማለት ለኔ ትርጉም የለውም። ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ይኑር ብሎ መታገል ግን የፈሰሰውን የንፁኀን ደም ለመፋረድ መቁረጥ ነው። ወ/ት ብርቱካን መስዋዕትነት እየከፈለችለት ያለውን የሕግ የበላይነት መርኅ ከልብ መደገፍ እና ለዚህ መርኅ መከበር በፅናት መቆም ነው።

 

ምርጫውን አስቀድመው ማጅራት የመቱት እነ አቶ መለስ ከምርጫው ራሴን አገላለሁ በሚሉት እንጂ በነሱ የተጭበረበረ ምርጫ በሚሳተፉት ሊጋለጡ አይችሉም። ተቃዋሚዎች ይህን ምርጫ ረግጠው በመውጣት ምርጫውን አስቀድመው ያጭበረበሩትን ሴራ ሊያከሽፉባቸው ይገባል።


ሀብታሙ አሰፋ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ