እንሆ የእርቅ ሃሳብ (ግርማ ካሣ)
የምርጫው ውዝግብ ቀጠሏል - የሚያዳምጥ ካለ እንሆ የእርቅ ሃሳብ
ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) ግንቦት 18 ቀን 2002 ዓ.ም.
ምርጫ 2002 ከተደረገ አራት ቀናት ሆኑት። ገዢው ፓርቲ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ አሸናፊ ነኝ ብሎ አወጀ። የአውሮፓ ሕብረት ታዛቢ ቡድን ምርጫው የአለም አቀፍ መስፈርትን ያሟላ እንዳልሆነ ይፋ አደረገ። የአሜሪካ መንግስት ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዳልሆነ የሚገልጽ መግለጫ አወጣ። ቢቢሲ፣ አሶስየትድ ፕሬሥ፣ ሮየርትስ፣ ቪኦዔ፣ አጃንስ ፍራንስ ፕሬሥ፣ ዋሺንግተን ፖስት …ምርጫውን እንደተጭበረበረ በሰፊው እያተቱ ነው።
አቶ መለስ ዜናዊ በመስቀል አደባባይ ድርጅታቸው ማሸነፉን አስመልክቶ በተናገሩት ንግግር፣ ተቃዋሚዎች የምርጫውን ውጤት እንዲቀበሉ ጥሪ አደረጉ። ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ድርጅታቸው እንዳሸነፈ፣ ምርጫውም እንዳልተጭበረበረ ተናገሩ።
የአቶ መለስ ዜናዊን የመስቀል አደባባይ ንግግር ተከትሎ፣ በነጋታው መድረክና መኢአድ ኦፍፊሴላዊ መግለጫ አወጡ። ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዳልሆነ፣ እንደተጭበረበረ ገልጸው ምርጫው እንዲደገም ጠየቁ። በምንም አይነት ሁኔታ ምርጫውን እንደማይቀበሉ አረጋገጡ።
ስለምርጫው ሂደትና ውጤት ብዙ ብዙ መጻፍ እንችላለን። ብዙ የታዘብነው፣ ብዙ ያየነው ፣ ብዙ የሰማነው ኔግር አለ። ነገር ግን 99% የሚለው ቁጥር በራሱ፣ ስለ ምርጫው ሁኔታ፣ ድምጽ አውጥቶ የሚናገር በመሆኑ ብዙ ወደ ዝርዝር አልሄድም።
ኢሕአዴግ ድምጽ ሰርቆ በስልጣን ላይ መቆየት ከነበረው አላማው አንጻር፣ ቢያንስ 30% የሚሆነውን ለተቃዋሚዎች ቢተውላቸው ኖሮ፣ ምናልባት አውሮፓና አሜሪካ ተቃውሟቸውን ላያሰሙ ይችሉ ነበር። ምናልባት ይሄን ጊዜም ተቃዋሚዎች ላይ፣ ምርጫውን እንዲቀበሉ ከዲፕሎማቶች ግፊት ይመጣ ነበር።(በምርጫ ዘጠና ሰባት እንዳደረጉት) እንደ ማስበው፣ ኢሕአደግ 99% አሸነፍኩ ማለቱ ለተቃዋሚዎች ትልቅ ገጸ በረከት ነው የሰጣቸው።
ያ ብቻ አይደለም። የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ ሲፈረም ኢሕአዴግ በመድረክ እና በመኢአድ መካከል ትልቅ ልዩነት እንዲፈጠር ማድረግ ችሎ ነበር። ሰሞኑን እንደተከታተልነው፣ በምርጫው ቀን የመኢአድና መድረክ ታዛቢዎች በትብብር ሲንቀሳቀሱ ታዝበናል። እኩል ትደብድበዋል፤ እኩል ተባረዋል። የምርጫውን ሁኔታም ተከትሎ ሁለቱም ምርጫውን አውግዘውታል። ሁለቱም ምርጫው እንደገና እንዲደረግ ጠይቀዋል። ምናልባትም መኢአድ መድረኩን ሊቀላቀል ይችል ይሆናል የሚል ግምት በአንዳንዶች ሲንጸባረቅ እየተሰማ ነው።
ሌላው የሥነ ምግባር ደንቡን የፈረመው ቡድን፣ በአቶ ልደቱ አያሌው የሚመራው ኤዴፓ ነው። የኤደፓ አቋም ምን እንደሆነ ገና አይታወቅም። ኤዴፓ ሶስተኛ አምራጭ በሚል ከመድረክ ጋር ከመሥራት ከኢሕአዴግ ጋር መሥራት ይሻላል የሚል አቋም ይዞ እየተንቀሳቀስ የነበረ ድርጅት ነው። የኤዴፓ ፖለቲካ፣ በተቻለ መጠን በፍርሃትና አቶ መለስ ዜናዊን ባለማስቀየም ላይ ያተኮረ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። ለዚህም ነው የኤዴፓው አቶ ለደቱ፣ አቶ መለስን የሚያስቆጣና የሚያናድድ በመሆኑ፣ አንድም ጊዜ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንድትፈታ ሲከራከርም ሆነ መግለጫ ሲያወጣ ያልተሰማው። ይህ የኢዴፓ አቋም ነው እንግዲህ ከመኢአድና ከመድረክን ጋር በመስማማት ምርጫው እንደገና እንዲደረግ ጥሪ ያቀርባል የሚል ግምት ብዙዎች የሌላቸው።
ኢሕአዴግ ምርጫው እንደገና እንደማያደረግ እየተናገረ ነው። እንደጋና ምርጫ ተደረገ ማለት ለኢሕአዴግ እንደ ሽንፈት ነው የሚቆጠረው። በመሆኑም አቶ መለስ ለዳግም ምርጫ ይስማማሉ የሚል ግምት የለኝም።
ተቃዋሚዎቹም ደግሞ በበኩላቸው ምርጫውን ለመቀበል ይከብዳቸዋል። ምርጫውን ሊቀበሉ መክበድ ብቻ ሳይሆን አይችሉም። ደጋፊዎቻቸውን ማሳመን አይችሉም። ምርጫውን ተቀብለው የነበራቸውን ተቀባይነት ይዘው መቀጠሉ ከባድ ነው የሚሆነው።
እንግዲህ በዚሁ ውዝግብ ውስጥ ነው ያለነው። ይህ መፍትሄ ካላገኝ አገራችንን ወደ ማይፈለግ አቅጣጫ ልንወስዳት እንችላለን።
ከምርጫው በፊት ሰላም እንዲኖር በመመኘት ለሕዝብ ንግግር ሲያደርጉ የነበሩ የኃይማኖት መሪዎች እዚህ ላይ እንግዲህ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ። ገዢው ፓርቲ ሲፈልጋቸው ብቻ በቴለቭዥን ብቅ በማለት ገዢው ፓርቲ መስማት የሚፈልገውን ብቻ መናገር ሳይሆን፣ እንደ እግዚአብሄር አገልጋይ በድፈረት ሁሉንም በመገሰጽ፣ በመቆጣትና በመምከር የተራራቁትን ወደ መሃል የማምጣት ሃላፊነት አለባቸው እላለሁ።
የሃይማኖት መሪዎች ሊያደርጉት የሚገባ አስተዋጾ እንደተጠበቀ ፣ በአገራችን ሊኖር የሚገባውን የእርቅ ሂደት ያግዝ ዘንድ እኔም እንደ አንድ ተራ ዜጋ አንዳንድ የእርቅ ሃሳቦችን እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ፡
- የአገሪቷ ሕገ መንግስት፣ አንቀጽ 59 ንኡስ አንቀጽ 1 ፣ የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስተር ፓርላማውን የመበተን መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። አንቀጽ 59 ንኡስ አንቀጽ 4 ደግሞ፣ ፓርላማው በተበተነ በስድስት ወራት ውስጥ እንደገና አዲስ ምርጫ እንደሚደረግ ይገልጻል። በመሆኑም የአሁኑ ምርጫ ውጤት እንዳለ ሆኖ፣ ከሁለት አመት በኋላ በአንቀጽ 59 መሰረት፣ ሕጉ እንደሚፈቀደው፣ አዲስ ምርጫ እንዲጠራ ስምምነት ቢደርስ ጥሩ ሊሆን ይችላል።
- አቶ መለስ ዜናው ከሃላፊነታቸው ለመነሳት ፍላጎት እንደነበራቸው በተደጋጋሚ ገልጸው እንደነበረ ይታወቃል። እንደርሳቸው ፍላጎት ቢሆን ኖሮ (እንደነገሩን) በዚህ ምርጫ አይወዳደሩም ነበር። በቅርቡም እንደሰማሁት፣ በርግጠኝነትም ከአምስት አመት በኋላ እንደሚለቁ አሳውቀዋል። ስለዚህ ከሁለት አመት በኋላ በሚደረገው ምርጫ፣ ድሮም የሚፈልጉት በመሆኑ፣ አቶ መለስ ዜናዊ ከውድድሩ ወጥተው እንደ ገለልተኛ ነጻና ዴሞርካሲያዊ ፍክክር የሚኖርበትን ሁኔታ ቢያመቻቹ ጥቅም ይኖረዋል።
- የአውሮፓ ሕብረት ታዛቢዎችም ሆነ የአለም አቀፉ ሜዲያ ምርጫው ፍትሃዊ አይደለም ካስባላቸው በርካታ ምክንያቶ አንዱ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ነው። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ቀድሞውኑ መታሰር አልነበረባትም። በአስቸኳይ ተፈታ የፖለቲካ እንቅስቃሴዋን እንድትቀጠል መደረግ ይኖርበታል። ወ/ት ብርቱካን አሁን ያለችበት የጤንነት ሁኔታ ለብዙዎች ግልጽ ያልሆነና አሳሳቢ በመሆኑ ከእሥር እንደተፈታች አስፈላጊው ሕክምና እንዲደረግላት መመቻቸት አለበት።
- የመድረክና የመኢአድ አመራር አባላት አሁን ያለውን የምርጫ ውጤት፣ ለአገር ሰላምና እርቅ ሲሉ ተቀብለው ከሁለት አመት በኋላ ለሚደረገው ምርጫ ቢዘገጁ ጥሩ ይሆናል። ምርጫውን መቀበል አስቸጋሪ እንደሆነ ይገባኛል፤ ግን መድረክንና መኢአድን የመረጠው ሰላም ወዳዱ ወገናችንን፣ በርጋታ ለምን እንደሆነ ከተነገረው ውሳኔያቸውን የሚቀበል ይመስለኛል።
- ከሁለት አመት በኋላ የሚደረገው ምርጫ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያው እንዲሆን፣ በዚህ ምርጫ የተሰራው ስህተት እንዳይደገም፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲዋቀሩ ማድርግ፤ ለዚህም የሚረዳ አንድ ገለልተኛ ኮሚሽን ማቋቋም ያስፈልጋል።
- ለሚቀጥሉት ሁለት አመታት አቶ መለስ ዜናዊ ለጋዜጠኖች በገለጹት መሰረት አንገብጋቢ የአገር ጉዳይ ላይ(የአባይን ውሃ የመጠቀም ጉዳይና የመሳሰሉ ጉዳዮች) ከመድረኩና ከመኢአድ አመራር አባላት ጋር የሚመክሩበት መድረክ ማመቻቸቱ ጥቅም ይኖረዋል።
ውድ የአገሬ ልጆች!
መለስ ብለን ወደ ኋላ ብንመለከት ብዙ ብዙ ነገሮችን ልንነጋገር እንችላለን። ይህንን የእርቅ ሃሳብ ሳቀርብ አማራጩ እጅግ በጣም የከፋ እንደሚሆን ስላሰብኩኝ ነው። ኢሕአዴግ 99% አሸነፍኩ ብሎ በምንም አይነት መልኩ በሰላም ሊገዛ አይችልም። የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ይሄን የሚያወቁት ይመስለኛል። መገንባት፣ ማልማት ቀላል ነው፤ ማፈረስና ማውደም ግን በጣም ቀላል ነው። ህዝብን በማስፈራራት፣ ተቃዋሚዎችን በማስፈራራት፣ ደጋፊዎችን በገንዘብ በመግዛት ብዙ መሄድ አይቻለም። መፍትሄው አሁንም እራስን ትሁት አደርጎ፤ ለእርቅን ለሰላም፤ መዘጋጀት ነው። መፍትሄው ሰጥቶ በመቀበል መርህ ለአገር የሚበጅ ጉዳይ ላይ ማተኮር ነው።
ግርማ ካሣ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ግንቦት 18 ቀን 2002 ዓ.ም.



