መክብብ ማሞ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ሳፓርሙራት ኒያዞቭ ይባላሉ። ቱርክሜኒስታንን ለሁለት ዓስርተ ዓመታት ያህል አስተዳድረዋል - ገዝተዋል ቢባል የሚቀል ይመስለኛል። አነሳሳቸው ከዝቅተኛ ቤተሰብ ነው። አባታቸው ናዚ ጀርመንን ሲዋጉ እንደሞቱ ይነገራል። ሌሎቹ ቤተሰቦቻቸው ደግሞ በመሬት መንቀጥቀጥ ስለሞቱ ወላጅ አልባ ነው ሆነው ያደጉት። ብዙም ሳይቆይ ግን አገራቸው የሶቪዬት አንድኛዋ ክልል በነበረችበት ወቅት የኮሙኒስት ፓርቲው አባል በመሆን የቱርክሜን ኮሙኒስት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ሆነው ለዓመታት ሠርተዋል። በሶቪዬት ኅብረት ኮሙኒስታዊ አገዛዝ መለኪያ እንኳን ፓርቲያቸው ፈጽሞ ተሃድሶን የማያውቅ አምባገነናዊ እንደነበር ይነገራል።

 

 

 

የሶቪዬት ኅብረት ወደተለያዩ ግዛቶች ስትፈረካከስ ከተፈጠሩት መካከል አንዷ ቱርክሜኒስታን ስትሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኒያዞቭም አገሪቷን ያለማቋረጥ ሲገዙ ቆይተዋል። በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ”ምርጫ” ተካሄደና ኒያዞቭ 99.5% ድምጽ በማግኘት ”ተመረጡ”። ከዚያ በኋላም ኒያዞቭ ”ቱርክሜንባሺ” (የቱርክሜኖች አባት) በማለት ለራሳቸው ማዕረግ ሰጡ። በዚህ ግን አላቆሙም - ፓርቲያቸው የቱርክሜኒስታንን የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ከነደፈ በኋላ እርሳቸው ዕቅዱን ለማስፈጸም ”ጥበብ የተካኑት ብልህ መሪ” ስለሆኑ በሥልጣን ይቆዩ ዘንድ በቀረበው ጥያቄ 99.9% የህዝብ ድጋፍ በማግኘታቸው በ1990ዎቹ ማብቂያ ላይ ”ፓርላማው” ተሰብስቦ የኒያዞቭን አመራር እስካሁን ”ስለአልጠገብን” እርሳቸው ”ከፊት ሆነው እየመሩ እኛም እየተከተልን” ”ብልህ አመራራቸው እንዲቀጥል” ለምን አናደርግም በማለት ”የዕድሜ ልክ ፕሬዝዳንት” እንዲሆኑ ውሳኔው አስተላለፈ።

 

የውሳኔው ዋና ዓላማም እንዲህ አይነት ”የሰከነ አእምሮ” ያላቸውና ”የእውነት ተምሳሌት” የሆኑ መሪ የትም ተፈልገው ስለማይገኙ ለምን ይህንን ”ልማታዊ” ሥራቸውን ለዘላለም አይቀጥሉም ከሚል ”በጎ” አስተሳሰብ የመነጨ ነበር። ሆኖም ፓርላማው ይህንን ውሳኔ ሲያጸድቅ የፕሬዚዳንቱ የዕውቀት ምንጭ ”ከአእምሮአቸው” ይሁን ”ከቅንድባቸው” ሳይገልጽ ቢያልፍም ”ሊቁ ሰው” ኒያዞቭ ግን የኮሌጅ ምሩቅ እንደሆኑና ዕውቀታቸውም ከምህንድስና ጀምሮ እስከ ስነግጥም ፣ ፍልስፍና ታሪክና ሙዚቃ ጠርዝ እንደሚደርስ ራሳቸው ብቻ ሳይሆኑ አድናቂዎቻቸው ይናገራሉ።

 

እንዲህ ዓይነት ”የሰከነ አእምሮ” ያላቸው ”የዕውቀት ተምሳሌት” መሪ ”ብልህ አመራራቸውን ላልጠገበው” ህዝባቸው ከፈጸሙት ተግባራት መካከል በዋንኛነት የሚጠቀሰው በጋዝ ክምችት የበለጸገችው አገራቸው ከሽያጩ የምታስገባውን ትርፍ በተለያዩ የምዕራብ አውሮፓ አገራት ባንኮች በስማቸው ማከማቸት ሲሆን በጀርመኑ የዶቼ ባንክ እስከ 3ቢሊዮን ዶላር እንዳላቸው ይገመታል። ታዲያ ከዚህ ትርፍ ለህዝባቸው የለገሱት ነገር ቢኖር ምስላቸው በየከተማዎች ሁሉ እንዲሰራና ሃውልት እንዲቆምላቸው ማድረግ ሲሆን በአገራቸው ሥራዓጥነት 60% እንዲደርስ እንዲሁም ህዝቡ በየጊዜው የውሃና የመብራት መቋረጥ ስለሚደርስበት ሁኔታዎችን አቻችሎ እንዲኖር የሚቻላቸውን ሁሉ አድገዋል። ”ብልህ አመራራቸው ባለም የታወቀው” እኚህ ታላቅ መሪ የምዕራባውያን ከፍተኛ ድጋፍ ያላቸው ሲሆን ብዙ ለውጦችንም ላገራቸው አምጥተዋል - የሳምንቱን ቀናት እንዲሁም የወራትን መጠሪያ በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም ቀይረዋል። ይህ የስም መቀየር ጉዳይ ተወርዋሪ ኮከብም (meteor) በስማቸው እስከማሰየም አድርሷቸዋል።

 

ኒያዞቭ ለረጅም ጊዜ የተጠናወታቸውን የሲጋራ ማጤስ ሱስ ከጤናቸው ጋር በተያያዘ ምክንያት ሲያቆሙ የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውም ሆነ ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ሲጋራ እንዲያቆም መመሪያ በመስጠት እርሳቸው ”ከፊት ሆነው በመምራት ሌሎች እንዲከተሏቸው” ተምሳሌት ለመሆን ጥረዋል። አሜሪካ የቱርክሜኒስታን ጎረቤት በሆነችው አፍጋኒስታን የጀመረችውን የጸረሽብርተኝነት ዘመቻ ኒያዞቭ ሙሉ በሙሉ የደገፉ ሲሆን እንዲያውም በአገራቸው የአየር ክልል የአሜሪካ አውሮፕላኖች እንዲበሩ በመፍቀድ ለምዕራባውያን ያላቸውን ታማኝነት በተደጋጋሚ በመግለጻቸው ከምዕራቡ ዓለም ያላቋረጠ ድጋፍ ለአገራቸው ”ህዝብ” እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።

 

ኒያዞቭ የአገራቸው ህዝብ በራሱ ቋንቋ እንዲማርና እንዲያነብ በማለት ለዘመናት አገራቸው ስትተቀምበት የቆየችውን የ”ሲሪሊክ” (Cyrillic) ፊደላትን በመቀየር በላቲን እንዲተካ አድርገዋል። ይህንንም በማድረግ በርካታ ዜጎች አገራቸውን ለቅቀው ለስደት እንዲዳረጉ በማድረግ ታላቅ ”ውለታ” ለአገራቸው ሰርተዋል። የወርቅ ጥርስ ማድረግን የከለከሉት እኒህ ”ሊቅ መሪ” ልጆች አጥንት መቆርጠም እንዲጀምሩና የጥርሳቸውንም ጥንካሬ እንዲጠብቁ ምክራቸውን የለገሱ ሲሆን ይህንንም ዕውቀት ያገኙት በልጅነታቸው ውሾች አጥንት ሲቆረጥሙ በማየት እንደሆነ ይናገራሉ። ሆኖም ግን በአንድ ጉዳይ ላይ ተቃውሞ እንዳላቸው ይናገራሉ። ይህም ምስላቸው በየቦታው መደረጉን በተመለከተ ሲሆን ተቃውሟቸውንም ሲገልጹ ”በመሠረቱ እኔ ፎቶግራፌ በየቦታው እንዲሆን አልፈልግም ሆኖም ግን ህዝቡ ፈልጎ ያደረገው ስለሆነ ምንም የምለው አይኖረኝም” ሲሉ ተደምጠዋል።

 

 

እነዚህን የመሳሰሉ ታላላቅ ነገሮችን ሲያከናውኑ የቆዩት ”ውበት ካይናቸው ሽፋን የፈለቀላቸው ሊቅ ሰው” ”ይቀጥል” ጨምሮ ጨማምሮ ”ይምራን” ተብለው እንዳልተወደሱ በጤና ይሁን ወይም ለሚወዷት አገራቸው ሌት ከቀን በመሥራት በደረሰባቸው ድካም በየትኛው ምክንያት እንደሆነ ሳይታወቅ በረሃማ በሆነችው አገራቸው የበረዶ ቤተመንግሥት ለመሥራት የነበራቸውን ሕልም ዕውን ሳያደርጉ ከዚህ ዓለምና ”ይቀጥል” ብሎ ”ልባዊ” ምኞቱ ከገለጸላቸው ተለይተው አፈር ገቡ። ያ ”ያማረ ቅንድብም” አፈር በላው። ወይ ነዶ!!

 


መክብብ ማሞ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ