ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

ሐምሌ 27 ቀን 1981 ዓ.ም. ነበር። በአደባባዩ የሰፈረው በመቶ ሺ የሚቆጠር ሕዝብ የተለያዩ መፈክሮችን ይዞ ”እምቢ አምባገነንነትን! እምቢ የአንድ ፓርቲ ሥርዓትን! እምቢ የሰብዓዊ መብት ረገጣን” እያለ ይጮሃል። ታንኮችንና መትረየሶች የተደቀኑባቸው የወታደር መኪናዎችን በማሰማራት፣ የአገሪቱ 27ኛው ክፍለ ጦር ህዝቡን ከቧል። ታንኩ እየቀረበ መጣ። አንድ ወጣት ከታንኩ ፊት ቆመ። ታንኩ ጨፍልቆት አለፈ። ድንገትም ተኩስ ተጀመረ። መሳሪያ በታጠቁ በአገራቸው ሰዎች በተተኮሰ ጥይት በሺሆች የሚቆጠሩ ወደቁ። የሰው ልጆች ደም እንደ ጎርፍ ፈሰሰ።

 

በሰው ልጆች ታሪክ ትልቅ ጠባሳን ጥሎ ያለፈው ይህ አሳዛኝ ክስተት የተፈጸመው ቤጂንግ ቻይና በሚገኘው የቼይናሜን አደባባይ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ ለዚህ አረመኔያዊ ወንጀል ተጠያቂ የሆነ አንድም የቻይና ኮሚኒስት ባለሥልጣን የለም።

 

የቼይናሜኑ አደባባይ እልቂት፣ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት የሚደረገውን ትግል ግን አላቋረጠም። ከዘመኑ የቻያና የዴሞክራሲ ታጋዮች መካከል፣ የቼይናሜን አደባባይ ጭፍጨፋ ተጠያቂ የሆኑት ለሕግ መቅረብ እንዳለባቸው በአደባባይና በድፍረት የሚከራከረው፣ የህጻን ሴት ልጅ አባት ሁ ጂያ ይገኝበታል።

 

ሁ ጂያ በርካታ ጊዜ በቻይና ኮሚኒስት አገዛዝ የታሰረ፣ ከፍተኛ ግፍና እንግልት የደረሰበት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ፣ ወንጀል ሳይፈጽም፣ ለሰብአዊ መብትና ለሕግ የበላይነት እንዲሁም ለዜጎች መብት መከበር ደፍሮ መናገሩ እንደ ጥፋት ተወስዶ በእሥር ላይ ይገኛል።

 

ሁ ጂያ ከሁለት ዓመታት በፊት በ2001 ዓ.ም.፣ የአውሮፓ ሕብረት የሚሰጠው፣ ከኖቤል የሰላም ሽልማት ቀጥሎ ትልቅ ቦታ ያለው፣ የሳካራቭ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።

 

የስድሳ ስምንት ዓመት አዛውንት ሴት ናቸው። ከቻይና በስተ ደቡብ ምዕራብ የምትገኝ አንዲት ትንሽ አገር ተወላጅ ዜጋ ናቸው። በነሐሴ 1980 ዓ.ም በአገሪቱ ወታደራዊ ጁንታ ስልጣን ጨበጠ። እኝህ ሴት በመስከረም 1981 የብሄራዊ ዴሞክራሲ ሊግ የተባለ፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለዴሞክራሲ የሚታገል ድርጅት መሰረቱ። በሐምሌ 1981 ዓ.ም. የቁም እሥረኛ ተደረጉ። ከአገር ለቀው የሚሄዱ ከሆነ እንደሚፈቱ ቢነገራቸውም ”በጭራሽ ሕዝቤን ትቼ አልሄድም” በሚል ከአገር ለቀው እንደማይሀዱ አሳወቁ።

 

በ1981 ዓ.ም ወታደራዊው ጂንታ ብሄራዊ ምርጫ ጠራ። እኝህ ሴት የቁም እሥረኛ ቢሆኑም የሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲ ከ492 የፓርላማ መቀመጫዎች 392ቱን አሸነፈ። በምርጫ ሽንፈት ቢያጋጠመውም ወታደራዊው ጁንታ ምርጫውን ሰረዘ። ስልጣን እንደማይለቅም አሳወቀ። እኝህ ሴት ከእሥር ተፈተው ጠቅላይ ሚኒቴር ይሆናሉ ተብሎ ሲጠበቅ በእሥር ቤት እንዲቆዩ ተደረገ። ይኸው እስከ አሁን ድረስ እኝህ ሴት በወይኒ ቤት ይገኛሉ።

 

እኝህ ሴት፣ ቀደም ሲል በርማ ተብላ በምትታወቀው በሚያማር የዴሞርካሲና የሰብዓዊ መብት ታጋይ የሆኑት አን ሳን ሱ ኪ ናቸው። እንደ ቻይናው ሁ ጂምያ፣ አን ሳን ሱኪም በ1982 የሳካሮቭ ሽልማት ሊሰጣቸው ችሏል።

 

ሌላም የሳካራቭ ተሸካሚ ከሆኑት መካከል፣ ለ27 ዓመት በእሥር የተንገላቱት፣ ታላቁ የአፍሪካ አባት ተብለው የሚታወቁት፣ ኔልሰን ማንዴላም ይገኙበታል።

 

በቅርቡ በአውሮፓ ሕብረት ሁለተኛ ትልቁ ብሎክ የሆነውና ጀርመናዊው ስሹን ማርቲን፣ ጣሊያናዊው ዲ ካስትሮስ ፓውሎ፣ እንግሊዛዊቷ ስትሊኸር ካትሪን፣ ፈረንሳዊው ኦንሪ ዌበር፣ ፖርቱጊዟ አና ጎሜዝ የመሳሰሉ 184 የፓርላማ አባላትን ያቀፈው፣ Progressive Alliance of Socialists and Democrats የተሰኘው ቡድን፣ እንደ አን ሳን ሱኪና ሁ ጂያም በአገራች ያለች አንዲት ታላቅ ኢትዮጵያዊትን የሳካራቭ ተሸላሚ እንድትሆን በኦፌሴል መስከረም 18 ቀን እንደሚጠቁማ በድህረ ገጹ አሳውቋል። ይች ሴት የዴሞክራሲ ጀግና የሆነችው የምንወዳትና የምናከብራት እህታችንና መሪያችን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ናት።

 

http://www.socialistgroup.org/gpes/public/detail.htm?id=134676§ion=NER&category=NEWS&startpos=0&topicid=-1&request_locale=EN

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለዚህ ለተከበረ የሳካሮቭ ሽልማት ከመቶ አምሳ በላይ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት መጠቆሟ ብቻ፣ በአገራችን ኢትዮጵያ የሚደረገው ሰላማዊ የዴሞክራሲ ትግል ትልቅ ድልን እንዳስመዘገበ ሊቆጠር ይችላል።

 

በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ እንዳየነው ሁሉ አሳሪዎቿ አንገታቸውን ሲደፉ፣ ምንም እንኳን ከቃሊቲ እንድትወጣ ባይደረግም፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን በአለም አሉ ከሚባሉ ታላላቅ ተቋማት አንዱ በሆነው በአውሮፓ ሕብረት፣ አጀንዳ ለመሆን በቅታለች። አቶ መለስ እርሷን አስረውና 99.7% የፓርላማ መቀመጫዎች ዘርፈው አሸነፍኩ እያሉ ቢሆንም ያሸነፈችው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መሆኑ ግን በገሃድ እየታየ ነው።

 

አቶ መለስ ዜናዊ በገንዘብና በጠመንጫ ኃይል ጥቂቶች ሰዎች ሊከተሏቸው ችለዋል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን ሰው ሳታስገድድ፣ አንዲት ሳንቲም ሳትወረውር በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በፍቃዳቸው የሚከተሏት ኢትዮጵያዊያያኖችን አፍርታለች።

 

አቶ መለስ ዜናዊ በሙስና የተዘፈቁ አምባገነን የአፍርካ መሪዎችን ክለብ በመወከል፣ ለልመና ሥራ፣ እንደ ጂ 7 በመሳሰሉ የአንዳንድ የአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ስማቸው ሲጠራ እንሰማለን። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን እውነት፣ ዴሞክራሲን፣ ሰላማዊ ቁርጠኝነንት፣ ኢትዮጵያዊነት በመወከሏ ስሟ እየተጠራ ነው።

 

አቶ መለስ ዜናዊ፣ በተለይም ከ547 መቀመጫዎች ውስጥ 545ቱን አሸነፍኩ በማለታቸውና፣ እንደነ አርከበ እቁባይ የመሳሰሉ በስራቸው ያስመሰከሩ ፣ እንደ አባይ ጸሐዬ ያሉ ትሁት ሰዎች እያሉ፣ ባለቤታቸውን ወ/ሮ አዜብ መስፍን የሕወሃት ፖሊት ቢሮ አድርገው በመሾም፣ ሕወሃትን ከድርጅትነት ወደ ቤተሰብ ጉባዔነት እንዲሸጋገር ማድረጋቸው፣ በእርጅናና በጤና ምክንያት ስልጣናቸውን ለወንድማቸው ለራውል ካስትሮ ካስተላለፉት ከፊደል ካስትሮ ከመሳሰሉ ጋር ለመደመር በቅተዋል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን፣ በዘመናችን ታላላቅ ሰዎች ከሚባሉት ከነ ኔልሰን ማንዴላና አንሳ ሱንኪ ጋር እየተመሳሰለች ነው። ለሳካሮቭ ሽልማት መጠቆሟም በግልጽ የሚያሳየው ይሄንኑ ነው።

 

በጠራ አይምሮ ነገሮችን ለሚመለከት ማንም ኢትዮጵያዊ አቶ መለስ ዜናዊ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በማሰራችው፣ አስረውም ደግሞ አልፈታም በማለታቸው፣ የበለጠ እየተዋረዱ፣ እየቀለሉና እየተጠሉ እንዲመጡ አደረጋቸው እንጂ ምንም የጠቀማቸው ነገር የለም።

 

እንደ ዳዊት መደጋገም አይሁንብኝ እንጂ፣ አሁንም አቶ መለስ ዜናዊ ይችን ዳግማዊት ጣይቱ ብጡል ብዬ የምጠራትን ታላቅ ኢትዮጵያዊት ሴት፣ ለራሳቸው ሲሉ እንዲፈቱ እጠይቃለሁ። አቶ መለስ ደጋግመው እንደሚዋሹት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሕሊና እሥረኛ እንጂ የፖለቲካ እሥረኛ አይደለችም።

ብርቱካን ሚደቅሳ አሁን ትፈታ!


ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

መስከረም 18 ቀን 2003 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ