የጭለማ ቤት ጓደኞቼ
ሲሳይ አጌና
ልክ የዛሬ አምስት ዓመት በጥቅምት 1999 ዓ.ም. ዓለም በቃኝ ጭለማ ቤት የነበሩት የጭለማ ቤት ጓደኞቼ ዛሬ ተመልሰው ጨለማ ቤት ከወደቁ አንድ ወር አስቆጠሩ፤ ለመብት እና ለነጻነት መቆም፣ ለእውነት እና ለፍትህ መሰለፍ፣ እኩልነት እና ዲሞክራሲ መጠየቅ በወንጀል ተመንዝሮ፣ በአሸባሪነት ተፈርጆ ወህኒ ወርደዋል። ክሱ የፈጠራ፣ ሁሉ ነገር የጨበጣ እንደሆነ ከመነሻው ግልጽ የሆነው የህወሓት መሪዎች ውሸታሞች መሆናቸው ስለሚታወቅ ብቻ አልነበረም፤ ...
ባለፉት ሃያ ዓመታት የፈጠራ ክስ በማቀነባበር፣ አሳፋሪ "ማስረጃ" በመፈብረክ ስለሚታወቁም ብቻ አይደለም፤ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ለመወንጀል እና ሕዝብንም ለማሸበር ራሳቸው ፈንጂ እያጠመዱ በሀገሪቱ የሽብር ድርጊት መፈጸማቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር (ጉዳይ ፈጻሚ) የነበሩት ቪኪ ሀድልስተን ስላረጋገጡ እንዲሁም የህወሓት የሽብር ታሪክ በግሎባል ቴረሪዝም ዳታ ቤዝ ላይ ጭምር ስለተመዘገበ ነው። (ቪኪ ሀድልስተን እ/ኤ/አ አርብ ኦክቶበር 6/2006 ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የላኩትንና ሀሙስ ሴፕቴምበር 1/2011 ዊክሊክስ ይፋ ያደረገውን መሉ መልዕክት በዚሕ ጽሑፍ መጨረሻ ገጽ ላይ ሰፍሯል፤ ከምንጩ ለማየት ከፈለጉ ደግሞ በዚህ እዚህ በመጫን ያገኙታል። የህወሓትን የቀደመ የሽብር ታሪክ ደግሞ በዚህ እዚህ በመጫን ያገኙታል።
የህወሓት ደህንነቶች የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ወንጅለው ለማሰር ሲሉ ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚሉ ንጹሃንን ፈንጂ አጥምደው መግደላቸው ነው በዊክሊክስ ሰነድ የተጋለጠው። በምርጫ 1997 በተመሳሳይ ተቃዋሚዎችን ለመወንጀል ፖሊሶችን ጭምር በቦምብ እና በጥይት መግደላቸውን የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ አቶ ፍሬሕይወት ሳሙኤል አጋልጠዋል። በኃይል እና በጠለፋ የሪፖርቱን መደምደሚያ ከልሰው ለፓርላማ ባቀረቡት በእነ ዶ/ር መኮንን ዲሳሳ ሪፖርትም ላይ ሰልፈኞቹ የጦር መሳሪያ አለመያዛቸው ተሰምሮበት በፓርላማው ጸድቋል። ፖሊሶቹ ደግሞ የተገደሉት በጦር መሳሪያ መሆኑ በዚያው ሪፖርት ላይ ተረጋግጧል። "ተራራውን ያንቀጠቀጠው" እንዲሁም ባለፉት 20 ዓመታት ሕዝቡን በረሃብ እና በሽብር የቀጠቀጠው ህወሓት ማለት ይህ ነው።
አንሰበርም ብለው ለሕዝብ መብት እና ነጻነት የቆሙ ወገኖችን ለመወንጀል ሆቴል እና ታክሲ ላይ ፈንጂ እያጠመዱ ንጹሃንን የሚፈጁ ጨካኞች እያንዳንዱን ሰው ለማሰር አንድ ታክሲ ሙሉ ንጹሃንን ከሚያቃጥሉ የፀረ ሽብር ሕጉ እንኳን ሥራ ላይ ዋለ የምለው ከውስጥ በመነጨ ስሜት ነው። ይህ ሕግ ባይኖር ኖሮ አቶ በቀለ ገለታን እና ወጣቱን ፖለቲከኛ ኦልባና ሌሊሳን አሸባሪ ብሎ ለማሰር ቢያንስ አንድ ታክሲ በፈንጂ ማጋየታቸው የሚጠበቅ ነበር። ጋሽ ደቤን (አንጋፋውን አርቲስት ደበበ እሸቱን) ለማሰር አንድ ሆቴል ወይንም ሌላ ታክሲ፣ እስክንድር እና አንዱዓለምን ለመክሰስ እንዲሁ ተጨማሪ አውሬያዊ ድርጊት ሊፈጽሙ ይችሉ እንደነበር ከጀርባ ታሪካቸው በመነሳት መደምደም ይቻላል። ... ወደ ጨለማ ቤት ጓደኞቼ ልመለስ ...
ከአምስት ዓመት በፊት ሐምሌ 20 ቀን 1998 ዓ.ም. አንዱዓለም አራጌ እና እስክንድር ነጋ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ነበሩ። በዚህ ዕለት ከሰዓት ከቀኑ አስር ሰዓት ገደማ እስክንድር ዞን 5 ከሚባለው ስፍራ ተወሰደ። አንዱዓለምም ዞን አንድ ከተባለው የእስር ግቢ እቃህን ጠቅልለህ ውጣ የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ደረሰው። እስክንድር እና አንዱዓለም በፖሊስ መኪና ተጭነው ወደ ቀድሞው ከርቸሌ እስር ቤት ከተወሰዱ በኋላ ዓለም በቃኝ ጨለማ ቤት ተቆለፈባቸው። አስቀድሞ ወደ ጨለማ ቤት ተወስዶ የነበረው ሙሉነህ ኢዩኤልም እንደገና ወደ ጨለማው ተመለሰ።
ትንሽ ሲቆዩ እኔም ደበርኩዋቸውና ነኀሴ 12 ቀን 1998 ከቃሊቲ ወስደው የጨለማው ቤት ማኅበርተኛ አደረጉኝ። ጓደኞቼ በሞቀ ወሬ ተቀበሉኝ። እያወራን እኩለ ሌሊትን ተሻገርን፣ ሊነጋ ሲል በእንቅልፍ ተሸነፍኩኝ። ከእንቅልፌ ነቅቼ ዙሪያውን ሳማትር ግድግዳው በጽሑፍ ተሞልቷል። "ከዚህ ሕይወት አንድ ገመድ አይሻልም ወይ?" የሚለው ሳይደበዝዝ በደማቁ ይታያል። በብቸኝነት የስቃይ ሕይወት ተማሮ ገመድ የተመኘውና ገመድም አጥቶ ምኞቱን እዚያ ጭለማ ቤት ትቶ ተራውን ለኛ የለቀቀው ማን እንደሆነ አላወቅንም። ዘግይቶ በደረሰን መረጃ እዚያ ክፍል ውስጥ የነበሩት ሻለቃ ፀሐዬ ወልደሥላሴ ነበሩ። ሻለቃ ፀሐዬ ወልደሥላሴ ህወሓትን በአፍላው ዘመን በ1968 ተቀላቀሉ፣ እስከ ግንቦት 4 ቀን 1994 ከህወሓት ጋር ቀጠሉ። (መከላካያ ሠራዊቱ ከፖለቲካ ነጻ የሚሆነው ወረቀት ላይ ብቻ መሆኑ ይታወቃል)
ሻለቃ ፀሐዬ በየካቲት ወር 1993 ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለሁለት መሰንጠቁን ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ላይ የስብሰባውን መሪና የደህንነት ሚኒስትሩን አቶ ከንፈ ገ/መድህንን በጥይት ገድለዋል በሚል ታሰሩ። ሻለቃ ፀሐዬ በቅድሚያ በማዕከላዊ ምርመራ፣ በኋላም በዓለም በቃኝ፣ በመጨረሻም በቃሊቲ ከ6 ዓመታት በላይ ጨለማ ቤት አሳልፈዋል። እኚህ ሰው ከግንቦት 4 ቀን 1993 ዓ.ም. እስከተገደሉበት ቀን ድረስ 6 ዓመት ከ2 ወር ከ26 ቀን የታሰሩት ለብቻቸው ነበር። ... ሐምሌ 29 ቀን 1999 ሌሊት የቃሊቲ እስር ቤት ኃላፊዎች ሻለቃ ፀሐዬ መኖሪያ ቤት ድረስ በመሄድ "ሻለቃ ፀሐዬ ስለታመመ መጥተሽ እዪው" በማለት ባለቤታቸውን ይዘዋቸው ይሄዳሉ። ሴትየዋ ዛሬ ወደማያስታውሱት አንድ ግቢ አስገብተው ወደ አንድ ክፍል እያመላከቱ "እዚያ ክፍል ተኝቷል፤ ግቢና አነጋግሪው" ብለው ይመርዋቸዋል። ባለቤታቸውን ሻለቃ ፀሐዬን ሊያነጋግሩ የገቡት ወይዘሮ የጠበቃቸው በደም የጨቀየ የባለቤታቸው አስክሬን ነበር። ህወሓት እንዲህም ነው።
ስለጨለማ ቤት ጉዋደኞቼ ሳነሳ የጨለማ ቤቱ ግድግዳ ፊቴ ላይ ተደቅኖ ብዙ ርቀት ወሰደኝ። በዘረኝነት እያበዱ ከነቁሻሻው ህወሓትን የሚደግፉ፣ ሺህ ዘመን እሱ ይግዛን በማለት ለአቶ መለስ ውዳሴ የሚያቀርቡ (በቨርጂኒያ አርሊንግተን የነበረውን ውዳሴ እና ጭፈራ ልብ ይሏል)። [ቪዲዮውን ለመመልከት ከታች ያለውን የማጫቻ ቁልፉን ይጫኑ!] ህወሓት እና አቶ መለስ ከዘረኝነታቸው ባሻገር ጭካኔያቸው በርሃ ወርደው በመከራ ውስጥ ባለፉት ላይ ጭምር መሆኑ የሚከሰትላቸው መቼ ይሆን? ወይንስ ሻለቃ ፀሐዬ ዘራቸው ሲቆጠር ሌላ ሆኖ ተገኘ? በሻለቃ ፀሐዬ የተገደሉት የአቶ ክንፈ ገብረመድህን ደም ደመ ከልብ ይሁን እያልኩ አይደለም። አቶ ክንፈን የገደለ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ከገደለ ወንጀለኛ በተለየ ለምን ሰቆቃ ይፈጸምበታል? ነው ጥያቄው። ገዳይም፣ ሟችም የታገሉለት ሥርዓት በኢትዮጵያ ምድር ጥላቻ እና ሰቆቃ ያነገሰ፣ ዕኩልነትን የገሰሰ መሆኑ ፀሐይ በወጉ ያገኘው ዕውነታ ቢሆንም፤ ሰብዓዊና ሕጋዊ መብታቸው መከበር እንዳለበት አምናለሁ።
በኢህአዴግ የ20 ዓመታት አገዛዝ የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው አስረኞች በተረጋገጠ መረጃ ሁለት ብቻ ሲሆኑ፤ እነርሱም ጄኔራል ኃየሎም አርኣያን የገደለው አቶ ጀሚል ያሲን እና አቶ ክንፈን የገደሉት ሻለቃ ፀሐዬ ወልደሥላሴ ናቸው። ሌሎች ሁለት እና ሦስት ሰው ገድለው ሞት የተፈረደባቸው በርካታ ሰዎች በወህኒ ቤት ውሰጥ ሲኖሩ፣ አንዳንዶቹ ሞት ፍርዱ ከጸናባቸው 17 ዓመታት አልፏቸዋል። ሁሉም ሰዎች እኩል ቢሆኑም ህወሓቶች የበለጠ እኩል ናቸው እና የሆነው ሁሉ መሆን የሚገባው ነበር። በነገራችን ላይ በሌሎቹ ላይ ለምን ሞቱ ተፈጻሚ አልሆነም እያልኩ ሳይሆን፤ የህወሓት መዝገበ ቃላት ”ሰው” የሚለውን ቃል ”ህወሓት” በሚል የሚፈታው መሆኑን ለማሳየት ብቻ ነው።
እርግጥ ነው ሻለቃ ፀሐዬ ለ6 ዓመታት ከሰው ሳይገናኙ የውስጣቸውን በውስጣቸው እንደያዙ መገደላቸው ከግድያው ጀርባ ማን አለ? የሚለውን ጥያቄ በብርቱ ያስነሳል። አቶ ክንፈ የተገደሉበትን ስብሰባ ሊመሩ ከመነሻው ፕሮግራም የተያዘላቸው አቶ መለስ ዜናዊ አቶ ክንፈን ልከው ርሳቸው መቅረታቸው የአጋጣሚ ተብሎ እንዳይታለፍ ሻለቃ ፀሐዬ ከሰው ሳይገናኙ 6 ዓመታት በጨለማ ማሳለፋቸው እንዲሁም፤ የሚሊኒየሙ ይቅርታ በታወጀበት፣ የቅንጅት መሪዎች በተፈቱ በ17 ኛው ቀን መገደላቸው አብዝተን እንድንጠረጥር፣ ጠልቀን እንድንመረምር የሚያደርግ ነው። ለህወሓት ቅርብ የሆኑ ሰዎች ”ሴራ አለ” የሚለውን ቢያጣጥሉም። ...
አልፎ አልፎ የምጽፋቸውን ጽሑፎች የተመለከተ አንድ ታዛቢ፤ ”የተለያዩ ርዕሶችን አንድ ላይ አትደርት፤ ለየብቻቸው ጻፋቸው” ያለኝ ትዝ ስላለኝ ርዕሴ ህወሓት እና ሻለቃ ፀሐዬ ከመሆኑ በፊት ልመለስ። ... አዎን! ሻለቃ ፀሐዬ የነበሩበትን ጨለማ ቤት ዛሬ ተመልሰው ጨለማ ከተጣሉት እስክንድር እና አንዱዓለም እንዲሁም ዛሬ በውጭ ከሚኖረው ሙሉነህ ኢዩኤል ጋር በ1998 ክረምት ተረከብን። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በ17 የማጭበርበር ወንጀል ተከሶ ከወህኒ ቤት ያመለጠ ወርቁ የተባለ ሰው ሲያዝ ጨለማውን ለሱ ለቀን ለእኛ ቆርቆሮ ቤት ተቀለሰልን። አንድ የኮንፈረንስ ጠረጴዛ የምታህል ግቢም ታጠረልን። ዓለም በቃኝ ወህኒ ቤት ያረፈበት ስፍራ ለአፍሪካ ሕብረት አስቀድሞ በመሰጠቱ ሕብረቱ ግንባታውን ሲጀምር በህዳር ወር 1999 ከጠባቡ ወህኒ ቤት ወደቃሊቲ ተጭነን ከሌሎች አባሪዎቻችን ጋር ተቀላቀልን። ከወራት በኋላ ሁላችንም ወደ ሰፊው እስር ቤት ተለቀቅን። በተፈታን በአምስተኛው ዓመት እስክንድር እና አንዱአለም አሸባሪ የሚል ስም ወጥቶላቸው እንደገና ወደ ጨለማ ቤት ተመለሱ። ከነርሱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ታዋቂው የቲያትር ባለሙያ እና ፖለቲከኛ አርቲስት ደበበ እሸቱ በ70 ዓመቱ በአሸባሪነት ታሰረ።
ጋሽ ደበበ እንዲሁም በህዳር 1999 በአፍሪካ ሕብረት ሳቢያ ከጠባቡዋ እስር ቤት የወጡት አንዱዓለም እና እስክንድር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወደ ሚኖርበት የቁም እስር የተሸጋገሩት ወይንም ከቃሊቲ የወጡት ሽምግልና እና ይቅርታ የሚል ኮተት ቢንጠለጠልለትም እውነታው እና በዊክሊክስ ሰነድ በዲፕሎማሲያዊ ቃና እንደተረጋገጠውም በአሜሪካ መንግሥት ግፊት ነበር። እንዲያውም እስክንድር ከሁለት ወራት ቀደም ብሎ በነጻ የተለቀቀ ቢሆንም፤ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን በተያዘ ዕለት ምሽት በይቅርታ ነው የወጣው በማለት ዘግበዋል። ሁሉ ነገረ በደመነፍስ ስለሆነ የእስክንድር እና አንዱዓለምን እንዲሁም የጋሽ ደበበን፣ የአቶ በቀለ ገለታን፣ የአቶ ኦልባና ሌሊሳን፣ የነክንፈሚካል ደበበን፣ ... ወዘተ አሸባሪነት የሚያስረዳ በቶን የሚቆጠር መረጃ እንዳላቸው ሰሞኑን አቶ መለስ የዓመቱን ዕቅድ ለፓርላማ ሲያቀርቡ እንሰማለን። ለመዋዕላ ሕጻናት የማይመጥን የመከነው ሽብር ወይንም ሌላ ስም የሚሰጡት ቲያትር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እናያለን። ... አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ አንዱዓለም እና እስክንድር ከግንቦት 7 የተቀበሉት መመሪያ እና ለአሜሪካ ወይንም ለእንግሊዝ መንግሥት፣ ምናልባትም ለኤርትራ የስለላ ተግባር ሲያከናውኑ እንደነበር የሚያስረዳ በጌታቸው አሰፋ ወይንም በኢሳይያስ ወልደጊዮርጊስ የተደረሰ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች የሚተረክ ፎርጀሪ እና ቀሽም ዶክመንተሪ በነጻ ያሳዩናል፤ ለተመልካቹ ሳይከፍሉ ለማለት ነው።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን አዘውትሮ ማየት አይኪው ዝቅ ያደርጋል ይል ነበር እስክንድር። በርግጥም ሆድ በርሃብ እየጮኸ፣ ሕሊና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እየተራቆተ ደስታ እንደራቀን ስቃዩ የሚቀጥለው እስከመቼ ይሆን? በርግጥ ደልቷቸው የሚስቁ፣ ባርነት ተመችቷቸው የሚገለፍጡም አልታጡም። መቼም በባርነት ስር ሆኖ የሚደሰት አዕምሮው ማፍሰስ የጀመረ እንጂ ሙሉ ጤነኛ ተብሎ ሊወሰድ አይችልም። ሳቅ ሲነሳ ከዓመት በፊት የነበረው የእስክንድር የሳቅ ምኞት ታወሰኝ። ቦሌ መንገድ ዓለም ሕንጻ ከሚገኘው ላፓሬዚያን ካፌ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን ማኪያቶ እንጠጣለን። ያው እንደ ሁሌው ፖለቲካውን ስንሰልቅ ከአጠገባችን ያሉት ጎረምሶች በሳቅ ያውካካሉ። አንዳንዶቹ ከምር በሳቅ እየፈረሱ ነበር። ጨዋታቸው የደራ ነውና ትኩረታችንን ስበዋል። "እኛ መቼ ነው የምንስቀው?" በሚል እስክንድር ለወረወረው ሃሳብ በወቅቱ ምላሽ አልነበረኝም፤ ግን አንዳንዴ ሳስበው የሚታኘክ በሌለበት፣ ደስታ በጠፋበት ጥርስ ራሱ በኢትዮጵያ ምን ያደርጋል? ...
ሳቅ እየናፈቀው ጨለማ ቤት የሚንከራተተው እስክንድር ነጋ የወርቅ ማንኪያ ጎርሰው ከተወለዱ የሀብታም ልጆች አንዱ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የጀመረው ዛሬ የአቶ መለስ ልጆች በሚማሩበት እንግሊዝ ስኩል ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ እና ከፍተኛ ትምህርቱን የተከታተለው በዩ.ኤስ. አሜሪካ ነው። በዚህ ሂደት ያለፉ ሰዎች (ያ ትውልድን አይጨምርም) በአብዛኛው ከሀገራቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት የላላ እንደሆነ በስፋት ሲታመን፣ እንደ ኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ መግባት በእነሱ ዓይን የጤንነት ምልክት ተደርጎ የሚታይ አይደለም። የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲፈነዳ የቦሌ ልጆች "እኛ ምን አገባን የጨርቆስ፣ የፈረንሳይ እና የሽሮሜዳ ልጆች ይቸገሩበት" አሉ ተብሎ እንደተቀለደው ወደ እስር ቤት መወርወር እና መከራ መቀበል እንደኛ የኔታ ጋር ፊደል ቆጥረው አምሃ ደስታ እና መሰል የመንግሥት ት/ቤት ለተማሩ እንጂ በርግጥም በእንግሊዝ ስኩል ላለፉ ከባድ ቢሆንም፣ እስክንድር በአቶ መለስ የ20 ዓመታት አገዛዝ ለ8ኛ ግዜ እስር ቤት ገብቷል። ጨለማ ቤትም ተጥሏል።
በጥቅምት 1985 የፕሬስ ነጻነት መታወጁን ተከትሎ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ”ኢትዮጲስ” ጋዜጣን በማቋቋም ከሟቹ ታዋቂ ጋዜጠኛ ተፈራ አስማረ ጋር በነጻ ፕሬስ ውስጥ የሚታይ ደማቅ አሻራ አሳርፏል። በመቀጠል ”ሐበሻ” የእንግሊዘኛ ጋዜጣ፣ በኋላም ምኒሊክን ጨምሮ ሦስት ጋዜጦችን በማቋቋም እስከ ጥቅምት 1998 ሲሰራ ቆይቷል። ምርጫ 97ትን ተከትሎ በህዳር 1998 ለ7ኛ ግዜ ወደ እስር ቤት ተወሰደ። አሁን ለ8ኛ ግዜ። በዚህ ሂደት በተለይም በ1988ቱ እስራት ወቅት ባዶ ክፍል ቀዝቃዛ ወለል ላይ እንዲተኛ በማድረግ እንዲሁም በተፈጸመበት ድብደባ በእጁ ላይ ውልቃት ደርሶበታል። አሁንም የችግሩ ሰለባ እንደሆነ ቀጥሏል። በ1998 እስክንድርን ለማሰር ስሙ በጋዜጣ አዘጋጅነት ስላልሰፈረ እንዲሁም በባለቤትነትም እንዳይጠይቁት ምንም ቀዳዳ ሲያጡ ጨርሶ አባል ባልሆነበት የቅንጅት አመራር በማለት ከሰሱት። አንድ ዓመት ከ6 ወር ታስሮ በነጻ ተለቀቀ። በጋዜጣ ሥራም እንዳይሰማራ በፖለቲካ ውሳኔ ታገደ።
የህወሓት መሪዎች ያኔም ዛሬም እስክንድር ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ግንኙነት እንደሌለው ያውቃሉ። አሁን በግንቦት 7 ፈርጀውት በአሸባሪነት ሲከሱትም ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አለው ብለው በማመን ሳይሆን፤ በኢንተርኔት እና በሀገር ቤት አንዳንድ ጋዜጦች ላይ የሚጽፈው ዕውነት ስላንገሸገሻቸው፣ ትንተናው ስላባነናቸው ብቻ ነው። የአሁኑ እስራት የቅንጅት መሪዎች በተፈቱበት ወቅት አቶ መለስ ለህወሓት ሰዎች ተናገሩ የተባለውን ያስታውሰናል። በምዕራባውያኑ የተደረገውን ግፊት ተከትሎ የቅንጅት መሪዎችን ለመፍታት እና በፖለቲካው ሂደት እንዲቀጥሉ የህወሓት አመራር ሲወስን፣ የፖለቲካው አካሄድ የማይገባቸው የህወሓት ጄኔራሎችና ሌሎች ህወሓቶች አኩርፈው ነበር አሉ። አቶ መለስ ለነርሱ የሰጡት ማጽናኛ "አታስቡ እግር እስኪያወጡ እንጠብቃቸዋለን፤ ሊራመዱ ሲሉ እግራቸውን እንቆርጠዋለን" የሚል ነበር። ከህወሓት ውጭ ያለውን አንድም በአሽከርነት፤ አሊያም አዋርደው ለመግዛት የተነሱት የህወሓት መሪዎች ሁሉንም ለመስበር ቀና ያለውን መቀንጠስ ያስፈልጋል በሚል የወሰዱት ርምጃ ነው።
የማርቲን ሉተር ኪንግ አድናቂ፣ ሠላማዊ ትግል ላይ የቆረበውንና ባለፉት 12 ዓመታት በዚሁ የትግል መስመር ላይ ጸንቶ የቆመውን አንዱዓለም አራጌን በአሸባሪነት መክሰስ፣ ከሳሾቹ ደግሞ በዓለማቀፍ ደረጃ በአሸባሪነት የተመዘገበው የህወሓት መሪዎች መሆናቸው ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም የሚለውን ብሂል የሚያስታውስ ነው። አስገራሚው ነገር መንግሥት ሆነውም በዚሁ የሽብር ድርጊታቸው መቀጠላቸውን የአሜሪካ ኤምባሲ ሰነዶች ባረጋገጡበት እነ አንዱዓለምን በሽብር መክሰስ የህወሓት የደመነፍስ ጉዞ አሁንም እየተወለካከፈ መቀጠሉን ከማሳየት ውጭ የሚጨምረው ነገር የለም። ዛሬ የህወሓትን ውንጀላ የሚያምኑ በዘር ጥብቆ ውስጥ ገብተው ጉድጓድ ውስጥ እንዳለችው እንቁራሪት ሰማዩ የጠበበባቸው የህወሓት ሰዎች ብቻ ናቸው።
አንዱዓለም በ1990ዎቹ መጀመሪያ በአዲስ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ካውንስል አመራር ነበር። የፖለቲካ ተሳትፎውንም ከ1992 ጀምሮ በፓርቲ በመታቀፍ ቀጥሏል። በኢዴፓ ምክትል ፀሐፊነት፣ በቅንጅት ላዕላይ ምክር ቤት አባልነት አገልግሏል። በምርጫ 2002 የፓርቲዎች ክርክር የምርጫውን ሙቀት በመጨመር ብዘዎች ያስታውሱታል። በዚያ የፓርቲዎች ክርክር የተናገረው የተቆረጠበት ብቸኛ ተከራካሪም እርሱ ነበር። አሁን የኢህአዴግ አጋር ፓርቲ አመራር በመሆን በተገቢው ቦታ ላይ የሚገኘው የኢዴፓው ልደቱ አያሌውን በተመለከተ የተናገረው እንዲሁም ሬድዋን ሁሴን የተባለ ኢህአዴግን በወዶገብነት የተቀላቀለ ግለሰብ ከተቃዋሚነት ወደ ኢህአዴግ ያደረገውን ሽግግር የተቸበት ክፍል ተቆርጦ ወጥቷል።
ቃሊቲ እስር ቤትን ከደቡብ አፍሪካው ሮቢን አይላንድ ጋር በማነጻጸር የቃሊቲን ሲኦልነት የገለጸበትም እንዳይተላለፍ ታግዷል። ምርጫ 1997ትን ተከትሎ በተወሰደው የእስራት ርምጃ አንዱዓለም እስር ቤት ብቻ ሳይሆን ጨለማ ቤት ተጥሏል። ከጨለማ በተጨማሪ አደገኛ ቦዘኔ ዞን በተባለው የእስር ስፍራ ተወስዶ የታሰረ ብቸኛው የቅንጅት እስረኛ ነበር። የቅንጅት መሪዎች የፈረሙበትን የይቅርታ ወረቀት አንፈርምም ብለው ካንገራገሩትም አንዱ አንዱዓለም ነው። ... ያለፈው እንግልት አልበቃ ብሎ ከሁለት ሕጻናት ልጆቹ ሩሕ እና ዕፁብ ነጥለው መልሰው ጨለማ ውስጥ ጥለውታል። እስክንድርንም እስር ቤት ከተወለደው የ5 ዓመት ሕጻን ልጁ ናፍቆት ነጥለው ነበር በሰንሰለት አስረው የወሰዱት።
ሽብር ሲነሳ ዓለም አልቃይዳን እና ቢን ላደንን በዋናነት ያስታውሳል። ህወሓት ደግሞ ኦነግ እና ኦብነግን ይጠቅሳል። አሁን ደግሞ ግንቦት 7 ተጨምሮበታል። ዕድሜ ለዊክሊክስ እና ለግሎባል ቴረሪዝም ዳታቤዝ በሽፍትነቱም፣ በመንግሥትነቱም አሸባሪው ህወሓት መሆኑን አጋልጠዋል። የዊክሊክስ ምስጢራዊ ሰነዶች የህወሐትን መንግሥታዊ አሸባሪነት ከማጋለጥ ባሻገር ብዙዎች በአሜሪካ መንግሥት ላይ የነበራቸውን ቅሬታም የገፈፈ ሆኖ አልፏል። አዲስ አበባ ላይ የተፈራረቁት የአሜሪካ አምባሳደሮች ህወሓት ደጋፊ የሆኑት ቪኪ ሀድልስተንን ጨምሮ ስለ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የጠራ እና የተብራራ ሪፖርት ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ዕድሜ ለዊክሊክስ ተረድተናል። የአንድ ዘር አገዛዝ በሀገሪቱ መስፈኑን፣ የሌሎች ሚና የአጫዋችነት መሆኑን በዝርዝር ደጋግመው ጽፈዋል። የህወሓት መሪዎች ሰዎችን በሀሰት ወንጅለው እንደሚያስሩ ሌላው ቀርቶ ሰዎችን ለማሰር ሲሉ ፍንዳታ እንደሚያቀነባብሩ ዕድሜ ለዊክሊክስ ሁሉም ተገለጠ።
እዚህ ላይ ሌላው በደማቁ የሚሰመርበት ነጥብ በህወሓት ሰዎችና አደግዳጊዎቻቸው አቶ መለስ ከፍተኛ የማሳመን ችሎታ አላቸው በሚል ሲለቀቅ የነበረው ነጠላ ዜማ ወደ ተረትነት መቀየሩ ነው። ዲፕሎማቶቹ በአቶ መለስ ንግግር ያመኑ መስለው በአደባባይ እየለፈፉ፣ እየተየቡ የሚልኩት ሌላ መሆኑ በቂ ብርሃን አግኝቷል። የአቶ መለስ የንግግር ችሎታ የማይካድ ቢሆንም፣ ብዙ ግዜ የማሳመኛ ነጥባቸው ወይንም መከራከሪያቸው የይሉኝታ ገደብን ያለፈ፣ በስድብ የታጀበ እንደሆነም በግልጽ ይታወቃል። በጄኔቭ የአሜሪካ አምባሳደር ዳግላስ ግሪፍዝስ በኢትዮጵያ የአንድ ዘር የበላይነት ስለመግነኑ በማንሳት፣ ይህም ችግር ያስከትላል በማለት በሰብዓዊ መበት ኮሚሽን ጉባዔ ላይ የዛሬ 3 ዓመት ስጋታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል። ይህንን በተመለከተ በታህሳስ 2001 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የተጠየቁት አቶ መለስ ዜናዊ ዕውነታውን ከመካድ ባሻገር አሜሪካዊውን ዲፕሎማት ደደብ ማለታቸው በአደባባይ የተነገረ ነውና ብዙዎች ያስታውሱታል። ገሃዱን ዕውነታ በስድብ ለማስተባበል መፍጨርጨር፣ ይህ ግፍና ውርደት ከዚህ በላይ ለማስቀጠል መታበይ አጸፋው የውርደት ውርደት እንደሚሆን ቀኑን አንወቀው እንጂ ሳይታለም የተፈታ ነው። መውደቃችሁን የሚጠራጠር እርሱ ሕሊናው የዘረኝነት ሞራ የለበሰ፣ እንዲሁም በጥቅም አብዶ አዕምሮው ያፈሰሰ ብቻ ነው። ሌላው እንዳትወድቁበት ይጠነቀቃል እንጂ ሩቅ በማይባል ግዜ መውደቃችሁን አይጠራጠርም። የአፍሪካ ንጉሠ ነገሥትነትን ሲያልሙ ሲርቲ ጉድጓድ የወደቁትን ጋዳፊን ያየ በሥልጣን ይጫወታልን? ለመሆኑ የአቶ መለስ ሲርቲ የት ይሆን? አድዋ ወይንስ ቻይና?
ሲሳይ አጌና
እነሆ አድራሻዬ፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ጥቅምት 6 ቀን 2004 ዓ.ም.



