ኩችዬ - ሐምሌ 24 ቀን 2001 ዓ.ም July 31, 2009 www.kuchiye.blogspot.com  

በአንድነት ፓርቲ ዙሪያ የሚናፈሰው ውዝግብ ወርደ-ሰፊ ትምህርት ያዘለ ነው። ትምህርቱ ለፓርቲው ኃላፊዎችና ደጋፊዎች ብቻ ባድራሻ የተላከ ሳይሆን፤ ባገራቸው ፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ሁነኛ ለውጥ እናመጣለን ብለው ለሚባዝኑ ሌሎች ፓርቲዎች ጭምር የሚተርፍ መልካም ትምህርት ነው። ከዲስኩር ላድናችሁ ብዬ ነው እንጂ በዚህ ዙሪያ ብዙ የምለው ነበረኝ።

 

አንድነት ውስጥ አሁን ለተፈጠረው ውዝግብ መነሻ የሆነው “መድረክ ውስጥ እንግባ አንግባ?፣ የምንገባስ ቢሆን ምን ዳር-ድንበር አስቀምጠን ቢሆን ይሻላል?” የሚለው ነው። ሌሎች በበራሪ ወረቀት የሚበተኑ ክሶችና ሐሜቶች በተረፈ-ፖለቲካና በማድቤት ወሬነት የሚመደቡ ናቸው።

 

መድረክ በመሠረቱ፤

ማንም ይጀምረው ማን መድረክ ያለፈው 18 ዓመት የተዛባ የፖለቲካ ጉዞ የፈጠረው ህዋስ ነው። ዘረ-መል (ጄኔቲክ) ምንጩ የተለየ ነውና ቀደም ባለው ዘመን ከተፈጠሩ ስብስቦች ጋር በመሳ ሊታይ የሚገባው አይደለም።

 

መድረክ ከሚነቀፍባቸው ምክንያቶች፤

መድረክ ላይ ከሚሰነዘሩት ነቀፋዎች መሃከል ሁለቱንና ዋናዎቹን ላንሳ። (ሀ) መድረክን የመሠረቱት የብሔር ድርጅቶች ናቸው፤ (ለ) መድረክ ውስጥ ህዝባዊና ድርጅታዊ መሠረት የሌላቸው ግለሰቦች ተሰንገዋልና እነሱን ከድርጅት ጋር መሳ ማየትና መወጣጫ እርካብ ማቀበል ጅልነት ነው የሚሉት ናቸው።

 

የብሔር ድርጅቶች የሆኑ እንደሆንስ?

ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ድርጅቶችና የብሔር ስሜት የለም ብሎ ራሱን የሚያታልል ካለ በዚህኛው ክፍለ ዘመን የሚኖር አይደለም። የቱን ያህል ዘግናኝ ቢሆንም ያገራችን የፖለቲካ እውነታ የብሔር ቅኝት አለው። የቅኝቱ ቁስል መንግሥት ባለፉት አሥራ ስምንት ዓመታት ባካሄደው የተሳሳተ ዘመቻ ይበልጥ እንደሰፋ መዘንጋትም ስህተት ላይ ይጥላል። አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር በቅርቡ የገጠመውን ግራ መጋባት ላጫውታችሁ። መምህሩ በእንግሊዝኛ አነበነበና ተማሪዎቹ ገብቷቸውና አልገባቸው እንደሆነ ጠየቀ። ጭንቅላቶች ግራና ቀኝ ተወዛወዙ። ችግሩ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ መሆን አለበት አለና ትምህርቱን በብሔራዊ ቋንቋው በአማርኛ ደገመውና ተከትለውት እንደሁ ጠየቀ። ጥቂት የማይባለው ክፍል አሁንም እንዳልተከተለው ተረዳ።

 

የመምህሩን ልምድ ከብዙ አኳያ ልንተነትነው የምንችል ቢሆንም ከጽሑፌ ዓላማ አንፃር ዓይኑን ያፈጠጠብኝ ነገር አለ። የብሔርን ጉዳይ የምንፈታው አግልለነው ሳይሆን ወደጉያችን ጠጋ አድርገን መሆኑን ነው። ባዲስ አመለካከትና በብልህ ስሌት መልክ ካላስያዝነው ሀገራችን የምታመራበት አቅጣጫ እጅጉን አያምርም። ለዚህ ነው መድረክ ውስጥ ገብቶ መሥራትም ሆነ በተወሰነ ደረጃ ተሻርኮ መንቀሳቀስ ትክክለኛ የፖለቲካ አማራጭ መስሎ የሚታየኝ።

 

ሌላም ልንስተው የማይገባን የፖለቲካ ቁምነገር አለ። መድረክ ውስጥ ያሉት ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች ይህን ያህል በብሔርተኝነት ልክፍት የተጠመዱ አይመስሉኝም - ያለፈው አሥራ ስምንት ዓመት የፖለቲካ ተመክሯቸው ብሔርተኝነት ለእነርሱም፣ ለክልሎቻቸውም፣ ለኢትዮጵያም ጠቀሜታ እንደሌለው አስገንዝቧቸዋል የሚል ታሳቢ ማድረግ ይቻላልና። ከዚህም በተጨማሪ የምንኖርበት ዓለም ወደ ግሎባላይዜሽን መጣደፉ ትምህርት ሳይሰጣቸው ያልፋል ማለት ብልህነታቸው ላይ መሳለቅ ይሆናልና አልሞክረውም።

 

“ታዲያ ይህ ከሆነ ድርጅቶቻቸውን ለምን ሕብረብሔራዊ አያደርጉም?” የሚል ጥያቄ ቢነሳ አግባብነት አለው። ወገኖቼ! ሁሉም ፖለቲካ መንደራዊ ነው የሚለውን ብሂል መዘንጋት የለብንም። ፌደራላዊው የፖለቲካ አወቃቀርና የባጀቱ አፈሳስስ አጉራ-ተኮር እንደመሆኑ መጠን እነዚህ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸውን የሚደርሱት በዚሁ መስመር በመጓዝ ይመስለኛል። በፈረንጁ ሀገር እንደምናየው “ፌደራል መንግሥቱ ጋር ተሟግቼ መንገድ አሠራሁልህ፣ … ወዘተ” ማለት የማይችል ፓርቲና ፖለቲከኛ ዳግም ላይመረጥ ነውና አንዳንድ ፖለቲከኞች ይህን መንገድ ቢከተሉና መራጮቻቸውን ለመቅረብ መንገዳችን ይህ ነው ቢሉ ልንደነቅም ልንነቅፋቸውም አይገባም። ለነገሩ ብንደነቅና ብንነቅፍ ምን ለውጥ እናመጣለን?

 

ትንሽ ላክልበት። ፓርቲዎች የብሔር ቅኝት ስላላቸው ብቻ ሁሉም የአንቅጽ 39 አሽቃባጭ ናቸው ማለት አይደለም። ሁሉም ክልላዊ አወቃቀርን ይደግፋሉ ማለትም አይደለም። እንዲህ ዓይነት ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ መሥራት ብሔራዊ አንድነትን ሊያስገኝ የሚችል አጀንዳ በመቅረጽ ረገድ በር ይከፍታል። ካልተነጋገሩና አልፎ አልፎም “የቢራ ዲፕሎማሲ” ካላካሄዱ መተማመን አይገኝም፤ ስውር ጥላቻንና ጥርጣሬን ማስወገድ አይቻልም። ዲሞክራሲያዊ ባህልን ለማዳበርም ሆነ ከውዝግብ ነፃ የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር አይቻልም። ያችን የምታውቋትን ጥቅስ አሁንም ልድገማትና “የፖለቲካ መነሻውም መድረሻውም ንግግር ነው”።

 

የታዋቂ ግለሰቦች ጉዳይ!

በመድረኩ ውስጥ በግለሰብ ደረጃ ከተሰባሰቡት መሀከል የአቶ ስዬ አብርሃና የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስም ጎልቶ ይነሳል። አቶ ገብሩ አሥራት በዓረና ትግራይ ጃንጥላ ሥር ይሁኑ እንጅ ስማቸው በእጅጉ ሲነሳ እሰማለሁ። ቀልዱን እናቁምና ሁሉም ሰው እኩል አቅም፣ እኩል ተደማጭነት፣ እኩል ዕውቅት፣ እኩል ልምድ፣ እኩል ዝናና ግርማ-ሞገሥ የለውም። ባንድ በኩል “ሴሌብሪቲ” የምንላቸው አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ “እኛ” አለን። ምን ማድረግ ይቻላል? ጨካኝ ዓለም ናት!

 

ሁሉም እኩል ቢሆንማ ኖሮ እኔና ኃይሌ ገብረሥላሴ እኩል ልንደመጥ ነው፤ አንኳኩተን እኩል በር ሊከፈትልን ነው፤ በምርጫ ተወዳድረን ኃይሌን የማሸንፍ ዕድል አለህ ልትሉኝ ነው። ህልም!

 

እነስዬ መድረክ ውስጥም ሆኑ ከመድረክ ውጭም ሆኑ የሴሌብሪቲ ደረጃቸው የሚያስገኝላቸው የፖለቲካ እሴት አለ። የሚያመጡት ዕውቀት ልምድና ተከታይ አለ። ያሳለፉት ሕይወትም ሆነ በቅርቡ ዘመን የደረሰባቸው ጉስቁልና ስለራሳቸውም ስላገራቸውም ብዙ ያስተማራቸው አለ። ስለሌሎቹ አላውቅም እንጅ፤ ስዬ አብርሃ በቪ.ኦ.ኤ. ደህና ነገር ሲናገሩ ትዝ ይለኛል። ሙሉ በሙሉ አንጀቴን ባያርሰውም አቶ ገብሩ አሥራት ዋሽንግተን መጥቶ በተናገሩት ላይ ማለፊያ ጅምር አይቸባቸው ነበር። ሰዎችን የምናቀርበውና የምናርቀው በትናንት ተግባራቸው ብቻ እየመዝንን ከሆነ በማናውቀው ንግድ ውስጥ ተሰማርተናል ማለት ነው። በጨዋ ቤት ፖለቲካ የወደፊት ጥቅም ማስከበሪያና የወዳጅ ክበብ ማስፊያ መሣሪያ ነው። ባለጌ ቤት ደግሞ የቂም በቀል መወጫና የዜሮ ድምር ሙግት መንኮራኩር ይሆናል። ምድባችን ከባለጌዎቹ ጎራ እንዳይሆን አምላክን መማለድ ተገቢ ነው።

 

ከመዝጋቴ በፊት የምመኛቸውን ጥቂት ነገሮች ላካፍላችሁ። በትናንቱ ላይ የማላዘንና የቁርሾ አባዜያችን እንዲለቀን እመኛለሁ። ከዲሞክራሲያዊ ውይይት በኋላ በተደረጉ ውሳኔዎች ተገዥ መሆንን እንድንማር ልቦናችንን ይከፍትልን ዘንድ እመኛለሁ። ግለሰቦችም፣ ድርጅቶችም፣ መንግሥታትም የሚያመሩት ወደ ዝቅተኛው የውጤታማነት ዕድሜያቸው መሆኑን ይቀበሉ ዘንድ እመኛለሁ።


 

ኩችዬ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ሐምሌ 24 ቀን 2001 ዓ.ም July 31, 2009

 

ማሳሰቢያ አስፈላጊ ባይሆንም ከመድረክም ከተጠቀሱት ግለሰቦችም ጋር እውቅና እንደሌለኝ እገልጻለሁ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ