የአንድነት እነ ፕሮፌሠር መስፍንን ከአባልነት ማባረር አባላትን አስቆጣ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም 2 ቀን 2002 ዓ.ም. September 12, 2009)፦ በቅርቡ ጠቅላላ ጉባዔ ሊጠራ ነው የሚባለው አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ነሐሴ 30 ቀን 2001 ዓ.ም. ባደረገው የም/ቤቱ ስብሰባ፤ እነ ፕሮፌሠር መስፍንን በድምፅ ብልጫ ከአባልነት ማባረሩ በአባላቶች ጥያቄ አስነሳ።
ፓርቲው በአመለካከትና በአቋም በመለየታቸው ከድርጅቱ አባልነት ተሰናብተዋል ያላቸው፤ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያምንና ዶክተር ሽመልስ ተክለፃዲቅን ጨምሮ 14 ሰዎች ሲሆኑ፤ አቶ አመኀ ዳኛውና አርቲስት ደበበ እሸቱም ይገኙበታል። ከወራት በፊት አቶ ታምራት ታረቀኝ የተባሉትን አባል አስቀድሞ ያሰናበተው አንድነት፤ ዋና ፀሐፊው አቶ አስራት ጣሴ “ኃላፊነቴን ልልቀቅ” ሲሉ ያቀረቡትን ጥያቄ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ጉባዔ ሳይቀበለው ቀርቷል። የፓርቲውን እንቅስቃሴና ዓላማ በመፃረር “የማወክ ተግባር ለመፈጸም ሞክረዋል” በሚል እንዲባረሩ ካደረጋቸው 14 አባላቱ በተጨማሪ በ8 አባላቱ ላይ የ3 ወር እገዳ ጥሏል።
እገዳውን በሚመለከትና ለግጭቱ መነሻ የሆነውን አንጻራዊ ምክንያት በውይይት መፍታት ይገባል የሚሉ ወጣት የፓርቲው አባላት፤ ድርጅቱም ሆነ የተባረሩት አካላት ሁኔታውን በሚገባ አጢነው መፍትሔ በአፋጣኝ እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርበዋል።
ወጣቶቹ ይህ ሁሉ የትግል እንቅስቃሴ ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ማስፈን እስከሆነ ድረስ አንድነትም ዲሞክራሲን በውስጡ መለማመድ ይገባዋል ሲሉ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸዋል። በተጨማሪም ፓርቲው ይህንን የመቻቻልና ግልፃማነትን ካላዳበረ በወጣቶችና በመጭው ትውልድ እንዲሁም በሀገሪቱ መጻዒ ዕጣ ፈንታ ላይ የሚጥሉትን ጥቁር ጠባሳ ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው በአጽንዖ ገልጸዋል።
የተባረሩት እነ ፕ/ር መስፍን “ፓርቲው የአምባገነንነት አሠራር ሰፍኖበታል፣ የሚመራውም በጡንቸኞችና ለነዚሁም ጡንቸኞች በሚያጨበጭቡ ሎሌዎች ሆኗል” ሲሉ ክስ አቅርበውበታል።
ኢንጂንየር ግዛቸው ሸፈራው ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች “ግልጽነትና ሚዛናዊነት ይጐድላችኋል …” በማለት ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ማንያዘዋል አሠፋ እና ወ/ሮ ፍቅርተ ዘሪሁን የተባሉ ሁለት የቀድሞ ቅንጅት ደጋፊዎች፤ “የአንድነት ሰዎች ትርምስ የኢትዮጵያን ህዝብ የትግል መንፈሥ የሚጐዳና የወይዘሪት ብርቱኳንን መስዋዕትነት የሚያረክስ ተግባር ነው” ብለውታል። ፕሮፌሠር መስፍን ግን “የኛ መጣላት ኢህአዲግን የሚያስፈነጥዘው ከሆነ ይፈንጥዝ፤ ከጠራን በኋላ ጥንካሬያችንን ያውቃል” እያሉ ናቸው።



