ብሔራዊ ተጠያቂነት ያልከበደው የአንድነት አታካራ (ስሜነህ)
“… የእኛን መለያየት ልዩ የሚያደርገው በሃሳብ ከእኛ የተለየን የራሳችንን ወገን ከምድረ ገጽ ድራሹን ካላጠፋንና ሞራሉን አንኮታኩተን እርኩሳዊ እርካታን ካላገኘን እንቅልፍ ያለመተኛታችን አባዜ ነው። ወይ እኛ አንተኛ ወይ ሰው አናስተኛ። ግራ የገባን፣ ቀናነት የጎደለን፣ … ህዝቦች። የተለያዩ ልምዶችም ሆኑ የ2 ሺህ ዓመት ሚሊኒየም ምንም ያላስተማሩን። …” የሚሉት በስዊድን የቀድሞ ቅንጅት በኋላም የአንድነት የድጋፍ ሰጪ ማኅበር ዋና ፀሐፊ የነበሩት አቶ ስሜነህ ታምራት ናቸው። አቶ ስሜነህ በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ የሰጡትን ጠንከር ያለ አስተያየት ታነቡ ዘንድ እንጋብዛለን። መልካም ንባብ!
ብሔራዊ ተጠያቂነት ያልከበደው የአንድነት አታካራ
ስሜነህ - ከስዊድን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ከዛሬ 33 ዓመት በፊት የተነገረ የፖለቲካ ትንበያ
“ስጋ በአህያ ጀርባ ተጭኖ
ውሻ እንዲመራ ጅብ እንዲነዳ ተወስኖ
በእርግጥ ይደርሳል ወይ? እንደነበር ሆኖ።”
የየካቲት ህዝባዊ እንቅስቃሴ አቅጣጫ እየሳተ መምጣቱን ገና በጠዋት የተረዱ የፖለቲካ ታዛቢዎች ጥርጣሬአቸውንና ስጋታቸውን የገለፁበት የግጥም ቋጠሮ ነበር። ዛሬ ከሰላሣ ሦስት ዓመት በኋላስ? “እውን አንድነት ለዲሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ በዚህ የቅራኔ አያያዝና የፓርቲ አስተዳደር የቅንጅት ዓላማ ወራሽነቱን በተግባር ይወጣ ይሆን?" ብዙዎቹ ጥርጣሬአቸውንና ስጋታቸውን እንደመጀመሪያዎቹ በግጥም ለመግለጽ ባይፈልጉም ይህ ብሔራዊ ጉዳይ በእጅጉ አሳስቧቸው እየተወያዩበት ይገኛሉ። እኔም እንደግለሰብ በዚህ ፖለቲካዊ ጉዳይ የሚሰማኝን እንድተነፍስ ለቅንጅት መንፈሥ የተሰዉት ወገኖች፣ በሀገር ቤት ከሞቱት በላይ - ካሉት በታች ሆነው ለህዝብ ሲሉ መስዋዕት እየከፈሉ የሚገኙ ዲሞክራቶች ጩኸት አነሳሳኝ።
1. በሆነ ባልሆነ ልዩነት መፍጠርን እንደአዋቂነት የመመልከት አባዜ
ሀገራችን ኢትዮጵያ ቆየት ባለው የታሪክ ዘመን የጥንታዊት አፍሪካ ሥልጣኔና የመንግሥት አስተዳደር ቀዳማዊ ሞዴል እንደነበረች ይነገራል። ዛሬ ዛሬ ደግሞ ከረሃብና ቸነፈር መታወቂያነት ባሻገር ፀጉር ሰንጥቆ በሆነ ባልሆነው መለያየት ልዩ ምልክቷ ሆኗል። በመሠረቱ በሃሳብ መለያየትና ያመኑበትን መከተል የሰው ልጅ አንድ የነፃነቱ አካል ነው። የእኛ የመለያየት ምክንያቶችን ስናጤናቸው ግን አስገራሚም አስቂኝም ናቸው። አንዳንዴ ገና ከመነሻው አንግባባም። ተስማምተን ትንሽ ብንሄድም ባንድነት አንዘልቅም። ፍፃሜው ላይ ሲደረስ መቅረብ ባለበት ጉዳይ በመጀመሪያ እንለያይበታለን። እናም የመለያያ ምክንያታችን እንቆቅልሽም ይመስላል። የምንነጋገረው ስለአንድ ሀገር እድገትና ስለሀገሬው ህዝብ የተሻለ ኑሮ፣ የምንደሰኩረው ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለነፃነትና ለሕግ የበላይነት፣ …። ግን ለምን እንደማንስማማ አይገባኝም። የሁሉም ሀገር ህዝብ በተለያዩ ብሔራዊ ጉዳዮች የተለያየ አመለካከት አለው እናም ይለያያል።
የእኛን መለያየት ልዩ የሚያደርገው በሃሳብ ከእኛ የተለየን የራሳችንን ወገን ከምድረ ገጽ ድራሹን ካላጠፋንና ሞራሉን አንኮታኩተን እርኩሳዊ እርካታን ካላገኘን እንቅልፍ ያለመተኛታችን አባዜ ነው። ወይ እኛ አንተኛ ወይ ሰው አናስተኛ። ግራ የገባን፣ ቀናነት የጎደለን፣ … ህዝቦች። የተለያዩ ልምዶችም ሆኑ የ2 ሺህ ዓመት ሚሊኒየም ምንም ያላስተማሩን።
በብዙ ሀገር ህዝቦች መካከል እንዳለው ሁሉ በእኛም ሀገር በግለሰቦችም ሆነ በቡድኖች መካከል ግልጽ ያለ ልዩነት መኖር ይጠበቃል። የልዩነቱን ምንነት አጢኖ ቢቻል ልዩነቱን አጥፍቶ አንድ መሆን። ካልተቻለም ልዩነቱን ለማቀራረብ የተወሰነ ርቀት መቅረብ። ይህ ካልሆነ ደግሞ እርስ በእርስ ተከባብሮ በየመረጡት መንገድ መጓዝ። ለሀገርና ለወገን ጥቅም ሲባል ከሚስማሙት ጋር ብቻ ሳይሆን ከማይስማሙትም ጋራ አብሮ ለመሥራት ራስን ማዘጋጀት የዲሞክራሲ ባህል የግድ ይለናል። ይህን አብሮና ተቻችሎ በመሥራት የሀገርን ብሔራዊ እድገት ለማፋጠን በጎ ተግባር ሳንሰንቅ ለሀገርና ለወገን ቆሜአለሁ ማለት ሚዛን የጎደለው ፖለቲከኛነት ይሆናል።
ይህን ልዩነትን እንደፋሽን ወይም እንደአዋቂነት የመመልከት ጎጅ ባህል ብዙዎቻችን እናወግዘዋለን። እራሴን ጨምሮ የመፍትሔው አመንጪዎች መሆን ግን ተስኖናል። እኔስ እውቀቱም አቅሙም ስላነሰኝ ነው። እባካችሁ የምትችሉ ወገኖች በጥናት ላይ ተመስርታችሁ ይህን በሆነ ባልሆነ የመለያየት አባዜ የምናስወግድበትን መላ ፈልጉልን። የእኛ የኢትዮጵያዊያንን በሆነ ባልሆነ የመለያየትን እርስ በእርስ የመናቆር ጉዳይ አስመልክቶ የሚሰማኝን ቁጭት ይበልጥ የሚያባብሰው ደግሞ ለመለያየቱና ለአታካራው መነሻና ጦስ እየሆነ የሚቀርበው ተውኔት የተማረው ወገናችን መሆኑ ነው። የተማረው ሰው ለሚናገረውና ለሚሠራው ሁሉ ምክንያታዊ ይመስለኝ ነበር። አንዳንዶቹማ የእኛ መንገድ የእየሱስ ጎዳና ነው ሊሉን ምንም አይቀራቸው። እኛን ሳይሆን እሱን ፈርተው እንጂ።
እስኪትንሽ ወደኋላ ዞር ብለን በልዩነት የተፈጠሩ ብሔራዊ ችግሮችን እንመልከት፤
ሀ) ኢህአፓና መኢሶን በተባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የመንገድ ምርጫና እኔ በመረጥኩት ካልሆነ በሚል የፖለቲካ ሽኩቻ ስንት ወጣት እንዳለቀ ለታሪክ እንተወው።
ለ) በርካታ የወያኔ ተቃዋሚ የሆኑ ድርጅቶች በሰሜን አሜሪካ የፈጠሩት ሕብረትም፤ “ሕ” ብቻ ቀርቶ ብረትነቱ ከጠፋ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ሐ) የግንቦት 97 ምርጫ ድል አድራጊ ተቃዋሚዎች ትክክለኛ የተግባር ቅደም ተከተል መተለም ተስኗቸው በተፈጠረ ትርምስ ያለቀውን ወገን እናስታውሳለን። ቅንጅት ያገኘውን የፖለቲካ መድረክ ተጠቅሞ ለበለጠ ድል አለመዘጋጀቱ ብዙ ብዙ የተባለለት ድክመት መሆኑን አሁንም ለታሪክ ትተን፤ ሥልጣኑ ቢቀር እንኳን አንድነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል በማይችልበት ሁኔታ ተሸራፍሮና ተሰነጣጥቆ ከግዙፍ ተቃዋሚነት ወደ ኢዴአፓ፣ መኢአድ፣ አንድነት፣ ግንቦት 7፣ … መቦጫጨቁ አሁንም በተማረ ወገን የተፈፀመ አፍራሽ ተግባር መሆኑ ቁጭቱ እንዳይረሳን ያደርገናል።
በዚህ ሳቢያ የተሰበረውን የኢትዮጵያን ህዝብ የትግል ሞራልና የሥነልቦና ጭንቀት ምን አይነት የፖለቲካ ሥራ ተሠርቶ እንደሚመልሰው እሱ (ፈጣሪ) ይወቀው። ለነገሩ የባርነት አስተዳድር እስካለ ድረስ የነፃነት ትግል መቼም ይሁን በማን አይቀሬ ነውና በዚህስ ተስፋ አንቆርጥም። የኢትዮጵያ ምሁራን እባካችሁ በኢትዮጵያ ጉዳይ አንድ ሁኑና ልዩነታችሁን የምታቻችሉበትን ኤክስፐርሜንት ሥሩ በማለት በትንሿ እውቀቴ ብሔራዊ መልዕክቴን አሰማለሁ።
2. የአንድነት መፈጠር የዓላማ ወይስ የምን ወራሽ ለመሆን?
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ “የቅንጅት ዓላማ ወራሽ እንጂ የድክመቶቹ ወራሽ አይሆንም” የሚለው ገዥ ሃሳብ በርካታ ተስፋ ያጡ የህዝብ ወገኖችን ተስፋ ሰጪ ሆኖ አሰባስቧቸዋል። በሥልጣን ላይ ያለውን የገዥ ፓርቲ ሁለንተና ተፅዕኖ (universal domination) ተቋቁሞ የተበታተነውን የቅንጅት ምክር ቤት አባልና ደጋፊ በገጠርና በከተማ አሰባስቦ አንድነት ፓርቲን ለመመስረት በተደረገው ሠላማዊ ግብግብ ሁሉም የአመራር አባላት የወልና የግል ድርሻቸውን ተወጥተዋል። በቅንጅት መፈራረስ የተመታውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሞራልና ሥነልቦና እንደገና ለማነሳሳት ሁሉም በወኔና በቁጭት ተረባርበዋል። በውስጥና በውጪ ያለው ዲሞክራሲያዊ ሠራዊትም አስፈላጊውን የሞራልና የፋይናንስ ድጋፍ ለግሷል። በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያዋ የሴት የፖለቲካ መሪ የሆነችው ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ (ብርቱዋ) በዚህ ክንዋኔ የከፈለችው የማደራጀትና የማሰባሰብ አኩሪ ብሔራዊ ተግባር ከአንድነት ታሪክ ጋር ተቆራኝቶ ይኖራል የሚል እምነት አለኝ።
ይሁን እንጂ የብርቱካን ህዝባዊ መሠረትና የአንድነት እንደገና ህዝብን ለቀጣይ ትግል የማነሳሳት አስፈሪ አዝማሚያ ወያኔን እንቅልፍ አሳጣው። እናም እንደተለመደው ተለጣፊ ወንጀል ተዘጋጅቶ ፍትህ ሰጭዋና ነፃ አውጭዋ ዳኛ ብርቱካን ፍትህ ተርባ ለዳግማዊ እስር ተዳረገች። የወያኔ ቀመር “ብርቱካንን ማሰር የአንድነት እንቅስቃሴን ማቆም ነው” የሚል ነው። በእርግጥም እሷ ከታሰረችበት ጊዜ ጀምሮ በፓርቲው ይታይ የነበረው መረጋጋትና የእርምጃውን አደገኛነት በቸልታ መመልከት የወያኔ ቀመር ትክክል መሆኑ ተንፀባርቆበታል።
ግድ ሆኖባቸው እንጂ በእንስት ፆታ ለመመራት ህሊናቸው ያልተቀበላቸው ኦሪታውያን ግለሰቦችም የመታሰሯን ጉዳይ አስመልክተው፤ “ይህ የእርስዋ የግል ጉዳይ ነው” እስከማለት ቃጥቷቸው እንደነበር አይዘነጋም። በሊቀመንበሯ መታሰር ዙሪያ ከኮሚቴ ማቋቋም የዘለለና የሚመዘን የሕግ አገልግሎትም ሆነ የ“ትፈታ!” ግፊት በጉልህ ታይቷል ማለት ይከብዳል። የብርቱካን አቋም የእኛም የፓርቲውም አቋም ነው ብሎ አፋጣኝ መግለጫ ለማውጣትም በራሱ ችግሮች ገጥሞት እንደነበር የመግለጫው መዘግየት ይናገራል።
አንዳንድ የፓርቲው መሪዎች በፓርቲው አመራር የመቆየትና አለመቆየታቸው በአጠራጣሪ ሁኔታ ላይ መታየቱ በራሱ የማይናቅ አፍራሽ ተፅዕኖ አሳድሯል። ፓርቲው በዓላማ ፅናታቸው በተፈተኑ ሰዎች ካልተመራ ደግሞ አንድ ምዕራፍ ላይ ቀጥ ብሎ ይቆምና ያልተጠበቀ የአመራር እጥረት ሊያጋጥመው ይችላል። ለዚህ መድኃኒቱ ተተኪ ወጣት ካድሬዎችን ከታች ወደላይ እያወጡ መድረክ በመስጠት አመራር ማለማመድ ይገባ ነበር። ነገር ግን ይህ ሲደረግ አልታየም። እንደውም አንዳንድ የአመራር አባላት ከወጣቱ እንቅስቃሴ ጋር ባለመጣጣማቸው መጠነኛም ቢሆን ችግር ተከስቶ እንደነበር በይፋ ተገልጿል።
እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ማለት ይገባ ይመስለኛል። የፓርቲውን አስተዳደራዊ ሥራ የሚያከናውነው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከማናቸውም አባልና ከማናቸውም አካል የበለጠ ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዳለበት ነው። ምክንያቱም ይህ የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ አካል፤
የፓርቲውን ዕለት ተዕለት ሥራ አከናዋኝ ማለትም ዓላማና ግቡን ጠብቆ የተነደፉ የሥራ እንቅስቃሴዎችን የሚቆጣጠር፣ የፓርቲውን የሰው ኃይልና የበጀት አጠቃቀም በአግባቡ የሚመራ፣ በአመራሩና በአባላቱ፣ በአባላቱና በህዝቡ፣ በህዝቡና በገዥው ፓርቲ መካከል ያሉትን ግንኙነቶችና መስተጋብሮች የሚከታተል፣ ከመሰል ፓርቲዎችና ድርጅቶች ጋር የሚፈጠረውን ግንኙነት በርቀት አይቶ በአንድነት ስትራቴጅያዊ ግቦች ላይ የሚያሳድረውን በጎና አፍራሽ ተፅዕኖ ፈጥኖ የሚመለከት፣ በጥቅሉ የፓርቲውን የውስጥና የውጪ ግንኙነት በሁለንተና መልኩ የሚወስን፣ ፓርቲውን ወክሎ በርካታ ጉዳዮችን የመፈፀም ከፍተኛ ኃላፊነት ያለው የሥልጣን እርካብ ነው።
ቁምነገሩ ያለው ኃላፊነቱን መዘርዘሩ ላይ ሳይሆን እነኝህን ተግባራት ተወጥቷቸዋል ወይ? ካልተወጣቸውስ ችግሩ ያለው የት ላይ ነው? እንዴትስ ይፈታል? የሚለውን አንስቶ ብዙ ማለት ይቻላል። ፓርቲው አሁን ያለበትን አጣብቂኝና ውስብስብ ሁኔታም እንደ አንድ ምክንያት ልናደርገው እንችላለን። በምንም መስፈርት ለአጠቃላዩ የፓርቲው ችግሮች ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ብቻ ተጠያቂ አድርጎ ማቅረብ ግን ሚዛን የጎደለው አስተያየት ከመሆኑም ባሻገር የፓርቲውን የስህተት ቦታ አውቆ እንደመደበቅም ይቆጠራል። ይህን ማድረግ ደግሞ የቅንጅት ድክመትን በመድገም የደካማ ጎኑ ወራሽ እንጂ የዓላማው ወራሽ አያደርግም።
አንዳንድ ጥያቄዎችን አንስቼ ግላዊ አስተያየቴን ለመስጠትና ለዚህ ጽሑፍም መነሻ ምክንያት የሆነኝ በቅርቡ በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ውስጥ በሁለት ክፍሎች የተነሳው ነፋስ ነው። በእርግጥ ነፋሱ ከጠነከረና ጉዳዩ ከሚገባው በላይ ከተወጠረ የአንድነት ቤት እንዳይፈርስ እሰጋለሁ። ይህ ከሆነ ደግሞ አንድነት በዓላማ ሳይሆን በተግባር ቅንጅት ሆነ ማለት ነው። ችግሩ ላልቶ በውይይት ከተፈታም “ጉድ አንድ ሰሞን ነው” ተብሎ ይቀራል። የብዙዎችንም ምኞት ቅራኔው በውይይት ተፈትቶ የፓርቲውን ሕይወት ማቆየትና በእርግጥም አንድነት የተጣለበትን ብሔራዊ አደራ በብቃት ሊወጣ ይችላል የምንልበት እምነት እንዲፈጥርልን ነው።
3. ፓርቲው በተሳሳተ የብዙኀን ውሳኔ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የሚደረግ የቅድሚያ ጥንቃቄ
እንደ የቅንጅት ዓላማ ወራሽነት የአንድነት ፓርቲ የግለሰብና የቡድን/ድርጅት ነፃነትን እንዲያከብር ይጠበቅበታል። ስለዚህ ማንም ግለሰብ በግልም ሆነ በቡድን የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ አስተያየቱን ቢሰጥ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ተገቢ አይሆንም። ታዲያ ለምንድን ነው በወያኔ ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ፀረ-ወያኔ ወረቀቶችን የምናሰራጨው? ሕገመንግሥታዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብታችንን በመጣሱ አይደለምን? በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ከተሰባሰቡት መካከል ጥቂቶቹ፤ “ሥራ አስፈፃሚ የሚሠራው ተግባር ከፓርቲያችን ደንብና ሕግ አኳያ ትክክል አይደለም” ቢሉ ችግሩ የት ላይ ነው? እነኝህ ተሰባስበው ውሳኔ ማሳለፍ ያልቻሉ ተቃዋሚዎች ቅሬታቸውን በበራሪ ጽሑፍ መግለፃቸው ቢቻል ቢቻል መለመድ የሚኖርበት አዲስ ባህል እንዲሆን ዛሬ ያለንበት ሁኔታ የግድ ይላል። አንዱ የዲሞክራሲ መገለጫ ዘዴም የተቀበሉትን ብቻ ሳይሆን የተቃወሙትንም በመጥፎ ተምሳሌት ያለመፈረጅ ነው።
በእርግጥ አሁን ፓርቲው ባለበት ሁኔታ፣ ደጋፊው ከፓርቲው ከሚጠብቀው ብሔራዊ ተግባራት አንፃር፣ ይህ ተቃውሞ- ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በዚህ መንገድ ብቻ መቅረብ ነበረበት ወይ? የሚለው ሌላ አነጋጋሪና በተከታይም የምዳስሰው ይሆናል።
በርዕዮተ ዓለም ብስለቱና በድርጅታዊ ብቃቱ ሰፊ ልምድ ያዳበረ ፓርቲ ቢሆንም እንኳን ብዙ ሁኔታዎች ሳይታዩና ሳይመዛዘኑ በጥድፊያ የሚወሰን ውሳኔ ሲውል ሲያድር ፓርቲውን እየጎዳ እንደሚመጣ አርቆ ማየት ብሔራዊ ኃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት ያስችላል። ከዚህ አኳያ አንድነት ገና የአንድ ዓመት ፓርቲ፤ ለዛውም መሪ ሊቀመንበሩን ያጣ፤ በችግር የተሳሰረ ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል። የዚህ አይነት ልምድ ያላካበተ ፓርቲ አንድ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት አይደለም አንዴና ሁለቴ ከዚያም በላይ ሂዶ ውሳኔው ሊያስከትል የሚችለውን አጠቃላይ ሁኔታ መመርመርና አፍራሽ ጎኑን አሻግሮ በማየት ፓርቲው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የማድረግ ግንባር ቀደም ኃላፊነት የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ነው።
የአካሄድ ፎርማሊቲ (procedure) ለመጠበቅ ተብሎ በውል ያልተብላላ ጉዳይ ብዙኀን እንዲወስኑት ቢደረግ በፓርቲው ላይ አሁንም አጠቃላይ ውድቀትን (General Crisis) እንዳያስከትል ሃሳብን ማንሸራሸር ጠቃሚና ጎጅ ገፅታውን ማንጨልጨል ከአስወሳኙ አካል ይጠበቃል። የፓርቲውን አጠቃላይ ውድቀት እስካስከተለ ድረስ አይደለም ብዙኀኑ ሁሉም ያለልዩነት ውሳኔ ቢያሳልፉም እንኳን፤ ሁሉም ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ መታወቅ አለበት። ዳሩ ግን ዓላማ ከከሸፈ፣ ትኩስ ትግል ከቀዘቀዘ፣ ደጋፊ ተስፋ ከቆረጠ፣ በፓርቲው ውስጥ አንድ መሆን ከጠፋ በኋላ፣ … የሚደረግ መወቃቀስ ምን ይፈይዳል? “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ …” እንደተባለው ይሆናል። የአንድነት ፓርቲ ከህዝብ መካከል የተገኘ ፓርቲ እንደመሆኑ የህዝብ እሴት ነው። ስለዚህም ፓርቲውን ለአንድ ወቅት የሚመራ የሥራ አስፈፃሚ የግል ንብረት አይደለም። የግል ባልሆነ ንብረት ላይ ደግሞ በግል መወሰንና ማስወሰን፣ ብሎም የሌላውን ስሜት መንካት ዘለቄታዊ መፍትሔን አያመጣም።
4. የብዙኀን ውሳኔ ፍፁም አይደለም
አንድ በውል መጤን ያለበት ጉዳይ ብዙኀን የወሰኑት ሃሳብ ገዥ ሃሳብ ቢሆንም፤ ውሳኔው በማናቸውም መልኩ ፍፁም ነው ማለት አይደለም።
ተቀራራቢ እውቀትና ተቀራራቢ ልምድ የሌላቸው የፓርቲው ውሳኔ ሰጪ ብዙኀን፣ ብዙውን ጊዜ ውሳኔ የሚያሳልፉት ጥቂት ሰዎች በሠሩት የሎቢንግ ተግባር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ከዚህ አኳያ ለአንድ ጉዳይ ማብራሪያ ሲቀርብ፤ “ምን ይደረግ ብዙኀን የወሰኑት ነው” ማለት ብቻውን የተሟላ መፍትሔ አመልካች አይደለም። ከዚህ ጭብጥ የምንገነዘበው እውነታ ብዙኀን የወሰኑት ውሳኔ ምንግዜም ቢሆን ትክክል ነው ማለት አስቸጋሪ መሆኑንም ነው። ብዙኀኑ የወሰኑት እውነትና ትክክል ከሆነማ የወያኔው አቶ መለስ ዜናዊ ባቃዣቸው ቁጥር የተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ሁሉ በትክክለኛነት ለመቀበል ልንገደድ ነው ማለት ነው።
በአንድ ፓርቲ ውስጥ ጥቂቶች እውነተኛውን መንገድ ይዘው፤ ነገር ግን በልዩ ልዩ አስገዳጅ ሁኔታዎችና ፓርቲው በውስጡ ባለው የዲሞክራሲ መታፈግና ሃሳብን የማንሸራሸር ጠባብ መድረክ የተነሳ ብዙኀኑ በተሳሳተ መልኩ አንድ ውሳኔ ሊያሳልፉ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በሳል አባላት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱትም እንዲህ አይነት የተሳሳተ ውሳኔ እንዳይተላለፍ ብዙኀኑን ለማሳመን ያለመታከት ግንባር ለግንባር የሚሠሩት ፖለቲካዊ ተግባር ነው። ጠንካራ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴም እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር የጥንካሬውን ብቃት ማሳየት ይጠበቅበታል።
5. የፓርቲ አባላትን ማባረር በራስ አለመተማመን ወይስ …?
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በተመሠረተ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መጀመሪያ የፓርቲውን የጥናትና ምርምር ኃላፊ አቶ አምሃ ዳኘውን ከኃላፊነት ማገዱን አስታውሳለሁ። በመቀጠልም አቶ ታምራት ታረቀኝን አግዷል። አሁን በቅርቡም የሥራ አስፈፃሚው ሥልጣን የፈቀደለትን ጥቂት የማይባሉ (21) አባላትን እንዳገደ ይነገራል። ነገር ግን ፓርቲው ምንም የእገዳ እርምጃ አልተወሰደም ይላል። ቅንጅት ውስጥ ውስጡን በልዩነት ሻግቶ፣ ቆስሎና ተበሳስቶ፤ ልዩነቱም በገሃድ እየታየ አንዳንድ ግብዞች “ቅንጅት አሁንም አንድ ነው! አትረበሹ!” ሲሉን ቆይተው፤ የተፈጠረውን ሁኔታ በኀዘን እናስታውሳለን። እና ዛሬም እውነተኛውን ለማወቅ እንዴት ይቻላል?
አንድ የፓርቲ አባል ለቆመለት ህዝባዊ ዓላማ ዕውቀቱን፣ ልምዱን፣ ጊዜውንና ሀብቱን መስዋዕት በማድረግ ለፓርቲው ዓላማ መሳካት የሚከፍለው ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ብቻ ሳይሆን ክቡርም ነው። ስለዚህ በአባላት ፓለቲካዊ ሕይወት ላይ የሚወሰድ ውሳኔ አሁንም ከአጠቃላይ የፓርቲው ቅራኔ አያያዝና አፈታት መርኅ፣ ፓርቲው ካለበት ተጨባጭ ሁኔታ፣ የትግል ፍላጎትና ልምድ ያላቸውን ኃይሎች ማጣት ከሚያስከትለው ችግር አኳያ፣ የሃሳብ ነፃነትን በውል ከመተግበር አንፃር እና ከሌሎችም ተያያዥ ውስጣዊና ውጫዊ ጉዳዮች ጋር ሊፈተሽ ይገባል እላለሁ።
“ቅንጅት የማንኛውም የኢትዮጵያዊ ግለሰብ የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ሙሉ በሙሉ የሚከበርበት ኅብረብሔራዊ ኅብረተሰብ እንዲያብብ ይታገላል። እጅግ ውድ የሆነው የሰው ልጅ እሴት ነፃነት እንደመሆኑ በሁሉም መስክ የግለሰብ ነፃነት ቀዳሚ ስፍራ ይይዛል።” (የቅንጅት ማኒፌስቶ)
አንድነት የማናቸውም ኢትዮጵያዊ ግለሰብን የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ለማክበር ሲነሳ በቅድሚያ ግን የራሱን በቅርብ አካሉ የሆኑ ግለሰቦችን ነፃነትን እንዴት ነው የሚያየው? ከሃሳብ ነፃነት የበለጠ ነፃነትስ ምን አለ? “ለምንድን ነው ሃሳባችሁን የገለጣችሁት” ተብሎ የግለሰቦች የትግል ሞራልስ ለምን ይሰበራል? ደግሞስ መተማመን በራስ ነው። እንደኔ የግል እምነት የአንድነት ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በራሱ የሚተማመን፣ የሚሠራውን የሚያውቅ፣ እናም የሚመጣውን ውጤት በቅድሚያ የሚያውቅ አድርጌ ነበር የማስበው እንጂ፤ ፈታኝ ወቅት ሲመጣበት “አስቸጋሪ” የምላቸውን በውሳኔ አስወግጄ ጥቂቶች የምንግባባው ብቻ እንሂድ የሚል አይመስለኝም ነበር። አቶ መለስ የሚዲያ ጀግና ናቸው። በተግባር ግን ፈሪ ናቸው። እናም ተቀናቃኞቻቸው ጎን ሆነው በዓላማቸው ትክክለኛነት ማንንም አሳምናለሁ ብለው በጀግንነት ሲሰለፉ ያየሁበት መድረክ የለም። መሪዎች እስር፣ ግድያ፣ አፈና፣ ሕግ ማውጣት፣ … የሚያዘወትሩት በራስ መተማመናቸው ተሟጥጦ ማለቅ ሲጀመር ነው። ታድያ የአንድነት መሪዎች አባላትን በሆነ ባልሆነው ማገድ በራስ ካለመተማመን ወይስ ከምን የመጣ ነው?
ሁለት ጥያቄዎችን ላነሳ እወዳለሁ።
ሀ. በቅንጅት ውስጥ በሁለት ፓርቲዎች መካከል (መኢአድና ኢዴአፓ) የተፈጠረ ሽኩቻንና “እኔ እበልጣለሁ”፤ “እኔም አላንስም” ትርምስ ሲያስታርቁና ሲሸመግሉ የነበሩ ሰዎች ምሳሌነት ዛሬስ ለምን ጠፋ?
ለ. የአንድነት አባላት እርስ በእርሳቸው ተወያይተውና ልብ ለልብ ተቀራርበው ቅራኔአቸውን መፍታት ካልቻሉ እንዴት ነው ደጋፊዎቻቸውን በአግባቡ የሚመሩትና ከገዥው መንግሥት ጋር አብረው መሥራት የሚችሉት?
6. ድርጅታዊ መዋቅርን ጠብቆ መታገል የመበታተን አደጋን ስለመከላከሉ
ቀደም ብዬ ለማመላከት በሞከርኩት ሃሳብ ግለሰባዊ ወይም ቡድናዊ ሃሳብን በማናቸውም መልኩ ማስተጋባት አንድ የዲሞክራሲ ዘርፍ መሆኑን ገልጫለሁ። ለምሳሌ ወረቀት መበተን በበጎ ጎኑ ሲታይ አንድ የትግል ዘዴ ቢሆንም አያይዞ የሚያስከትለው ጥያቄ አለ። ይህም ወረቀት ላይ ተቃውሞን በመግለጽና በፊርማ በማረጋገጥ (ፒቲሽን) የማዘጋጀት ዘዴ ለምን አስፈለገ? የአንድነት የሥራ አስፈፃሚ አካልን ፊት ለፊት አስቀምጦ ማወያየት ይህን ያህል ከባድ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ በሚገባ መፈተሽ ይኖርበታል። ከበርካታ የአባላት መብቶች መካከል አንዱን ለአብነት እንመልከት፦
ድርጅታዊ መዋቅርን ጠብቆ ማብራሪያና መረጃ የመጠየቅና ሂስ የማቅረብ መብት የሚለው መሠረተ ሃሳብ በብዙ ጎኑ የፓርቲ አባላትን መብት ያስከብራል። ከዚያም ባሻገር ድርጅታዊ መዋቅርን ጠብቆ መታገል ፓርቲውን ከመበታተን አደጋ ይከላከላል። በተለይም ምን ጊዜም እውነትን ፊት ለፊት በመናገር የሚታወቁ አንጋፋ ሰዎች በመጨረሻው ሰዓት ላይ በዚህ አይነት የትግል ስልት ሳገኛቸው የእነሱ ሳይሆን የእኔ ሞራል ነው ዝቅ ያለው። በዚህ ረገድ ብዙ ማለት ይቻል ነበር። ነገር ግን ብዙ ቢባል ተጠቃሚው ማን ይሆናል? የሚለው እየኮረኮመኝ ብዙ ከማለት ታቅቤአለሁ።
የአንድነት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለሰየመው የብሔራዊ ምክር ቤት ነው። ቢያጠፋም ሊጠየቅ የሚገበው በዚሁ አካል ይመስለኛል። በእርግጥ የአንድነትን አጠቃላይ ሰብዕናና ማንነት የሚጋፋ ድርጊት በአስፈፃሚው አካል ከተፈፀመ በዝምታ ታይቶ የብሔራዊ ምክር ቤትን ስብሰባ መጠበቁን እኔም አልደግፈውም። ይሁን እንጂ ተቃውሞን አንድም ድርጅታዊ መዋቅር ጠብቆ አሊያም ፊት ለፊት ቀርቦ መወያየትና ወደ ተሻለ አማራጭ ማምራት አዋቂነት ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ወጣት ታጋዮም ምሳሌነቱ የጎላ ነው።
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ብሔራዊ ኃላፊነት የተሸከመ ፓርቲ እንደመሆኑ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የሰጠው ኃላፊነትም የዛኑ ያህል ብሔራዊ ይዘት አለው። ለዚህ አመራር ይመጥናሉ ተብለው የተመረጡት ግለሰቦች በቅንጅት አጭር ዕድሜና ከዚያም በፊት በነበራቸው ሀገራዊና ወገናዊ ፍቅር እንዲሁም አንድነት ሲመሠረት በነበራቸው የማያጠራጥር ሰብዕና (personality) የተመረጡ ናቸው። የአንድ ፓርቲ አንድ አካል ዘላለማዊ ሳይሆን ተቀያያሪና ተለዋዋጭም ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ትናንት ብሔራዊ ኃላፊነትን ሊወጡ የሚችሉ መሪዎቻችን ናቸው ብለው ከመቀመጫቸው ተነስተው በጭብጨባና በሞራል የሰየሟቸውን አስፈፃሚዎች መናኛ በሆኑና ሚዛን ውስጥ ሊገቡ በማይችሉ እንደውሎ አበል አከፋፈል፣ የሠራተኛ ቅጥር፣ አንዱን የማቅረብና ሌላውን የማራቅ፣ … ወዘተ የመሳሰሉት ተራ ጉዳዮች ተኮልኩለው የሞራል መስበሪያ ሆነው መቅረባቸው በእጅጉ ግምት ላይ ይጥላል።
ስለሆነም የአንድነት አባላት ሥልጣን ያላችሁም ሆነ የሌላችሁ፤ እባካችሁን ገና ፓርቲው ሥልጣን ሳይዝ በህዝብ ዘንድ እንዳይናቅ ከፍተኛ መቻቻልና አብሮ በፍቅር መታገልን አዳብሩ። የሠላማዊ ትግል አብሳሪ የሆነው የአንድነት ፓርቲ በራሱ ውስጥ ሠላምን አጣ ተብሎ መሳለቂያ እንዳይሆን ተግባራችሁ ሁሉ በእውቀት ላይ የተመሰረተና ትዕግስትንና አንድነትን የተጎናፀፈ ይሁን እላለሁ።
ማጠቃለያ
• በአንድነት ፓርቲ ውስጥ በሁለት ክፍሎች መካከል ተፈጠረ የሚባለው ልዩነት ግለሰቦች/ቡድን ሃሳባቸውን በነፃነት መግለጽ መቻላቸውን ከሚያንፀባርቅ ያለፈ ትርጉም ሊሰጠው አይገባም። ሆኖም ሆኖም በአፈፃፀም የታየው የቅራኔ አፈታት ዘዴ ታርሞና ይበልጥም የድርጅቱን መመሪያ መሠረት አድርጎ ቢሆን ይመረጣል።
• ሀገሩንና ወገኑን በቅንነት ለማገልገል የህዝብ አደራን የተቀበለ መሪና አስተባባሪ አካል፣ በማናቸውም መልኩ ተጠያቂነት ሳያስደነግጠውና አቋራጭ የውሳኔ መፍትሔ ለመስጠት ሳይቻኮል፤ ነገሮችን በሰከነ ሁኔታ መርምሮ በመቻቻል መርኅ እንዲመራ ራሱን ከተወዳሽነት ለተጠያቂነት ክፍት አድርጎ ቢሠራ በመሪነት ችሎታው (leadership quality) ይወደዳል እንጂ አይወገዝምና፤ ትግሉ ከሥርዓት ጋር ብቻ ሳይሆን ከራስ ጋርም ይሁን እላለሁ።
• የፖለቲካ እስረኞች በገዥው ፓርቲ እየደረሰባቸው ያለው የህሊናና የአካል ጉዳት እኛ ለነፃነታችንና ለመብታችን በሕብረት እንድንነሳ ቀስቃሽና አዘጋጃችን ነው። በተለይም የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳ የፖለቲካ ተከታዮቿን ስብሰባ ላይ፤ “… እኔ በእምነቴም በራዕዬም ፅኑ ነኝ፤ እናንተስ? …” በማለት ላቀረበችው ጥያቄ ተግባራዊ ምላሽ ልንሰጣት ይገባል። ይህም የሚሆነው ደግሞ የቅንጅት የዓላማ ወራሽነታችንን በገቢር ስንገልጽ ብቻ ይሆናል።
ማስታወሻ፦ ይህ አስተያየት የራሴ፣ የግሌ እንጂ የቡድን ይዘት የለውም። ስለሆነም የሚሰጠኝ ማሪሚያና ማስተካከያ ካለ ከነእርምቱ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ። በተለይም በርካታ መስዋዕትነት የከፈሉና እየከፈሉም ያሉ መሪዎቻችንን ምናልባት በስሜት ተስቤ በማይገባቸው ቃላት ገልጫቸው ከሆነ በቅድሚያ ታላቅ ይቅርታ እጠይቃቸዋለሁ። በዚህ ረገድ ማስተካከያ ቢሰጠኝ እታረማለሁ። ነገር ግን “ስልቻ ቀልቀሎ - ቀልቀሎ ስልቻ፤ ዝም ብለሽ ተቀበይ የሰጡሽን ብቻ” ከሚል መሠረተ ሃሳብ ዝም ብለህ ተቀበል የሚለኝ ካለ መልሴ አንድ ነው። ዝም ብዬ አልቀበልም!
ስሜነህ - ከስዊድን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



