በክፍፍል የሚታመሰው የተቃዋሚዎች መንደር (ጽዮን ግርማ)
የፓርቲዎች አመራሮች ስለ ክፍፍሉ ይናገራሉ
ጽዮን ግርማ
ከተመሠረተ በአንድ ዓመቱ የመሰንጠቅ አደጋ ያንዣበበትን የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የነበሩና ያሉ ፓርቲዎችን በአንድነትና በሕብረት መሥራትና መጓዝ ያለመቻላቸውን አባዜ አስመልክቶ ጋዜጠና ጽዮን ግርማ በጉዳዩ ላይ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን፣ ኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራውን፣ የፖለቲካ ምሁራንን፣ አቶ ገብሩ አስራትን፣ አቶ ስዬ አብርሃን እና ሌሎች ወገኖችን በማነጋገር ያቀረበችው ጽሑፍ ነው። መልካም ንባብ!
የፊውዳል ሥርዓቱን አገዛዝ በመቃወም በተማሪዎች እንቅስቃሴ የተጀመረው አብዮት፣ ደርግን ወደ ሥልጣን ካመጣው በኋላ የህዝብ ብሶት የወለዳቸውን አጀንዳዎች አንግበው ቡድን በመመስረት፣ በተቃውሞ ጎራ መንቀሳቀስ የጀመሩት ኢህአፓና - መኢሶን የያዙት ርዕዮተ ዓለምና ፀረ-ደርግ አቋማቸው አንድ ቢሆንም ታሪካቸው ግን እርስ በርስ የመጨራረስ ነበረ።
የደርግን አምባገነናዊ የአገዛዝ ሥርዓት በመቃወም፣ ጠመንጃ አንግበው ለትጥቅ ትግል ወደ ጫካ ያመሩት አብዮተኞችም ቢሆኑ በረሃ ላይ ህወሓት፣ ጀብኻ፣ ህዝባዊ ግንባር አርነት ኤርትራ፣ ከኢህአፓና ከመሳሰሉ የትግል ድርጅቶች ጋር የነበራቸው ትብብር በስተመጨረሻ አንድነትን ሳይፈጥር ህወሓት ወደ ሥልጣን ሲመጣ ኢህአዲግን ቢመሰርትም ከሻዕቢያ በስተቀር ሌሎቹ ደብዛቸው ጠፍቷል።
ደርግ ከሥልጣን ተወግዶ ኢህአዲግ የሥልጣን ወንበሩን ሲጨብጥ በሽግግር መንግሥት ምስረታ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ይፋ ተደረገ። በዚህ ወቅትም፤ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ሕብረት (ኢዲህ)፣ ሲዳማ ኣርነት ንቅናቄ (ሲኣን)፣ ጉራጌ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የአፋርና የሶማሌ ድርጅቶች እንዲሁም ደርግን ተቃውመው ወደ ትጥቅ ትግል የገቡና ሌሎች አዳዲስ ድርጅቶች ተቀላቀሉ።
ከሽግግር መንግሥት ምስረታው በኋላ ፓርቲዎቹ በፓርላማ መቀመጫ አግኝተው ጥቂት እንደቆዩ፣ አንዳንዶቹ በአሸባሪነት በመጠርጠራቸው በኢህአዲግ ስልት ሲወገዱ፤ ሌሎቹ ደግሞ በ1987 ዓ.ም. የተደረገው ምርጫ ፍትሃዊ አለመሆኑን ገልፀው ጥለው ወጡ።
እነዚህ ድርጅቶች በኢህአዲግ ላይ የሚያቀርቡት ተቃውሞ ተመሳሳይ ቢሆንም እርስ በርሳቸው በጋራ ተሰባስበው ሊሰሩ የሚችሉበትን ዕድል ሊፈጥሩ አልቻሉም፤ እንደውም አንዳንዶቹ በአንድ ብሔር ላይ አደረሱት በተባለው ጭፍጨፋ እነሱን ለሚቃወሙ ሌሎች ብሔራዊ ፓርቲዎች መፈጠር ምክንያት ኾኑ።
በ1987 ዓ.ም. ከተደረገው ምርጫ በኋላ የውድድር ፖለቲካ ባህል እንደ አዲስ በመጀመሩ፣ የመላው አማራ ህዝቦች ድርጅት (መአህድ)፣ ደቡብ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ደህዲን)፣ የኢትዮጵያ ሠላምና ዲሞክራሲ አማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት (ዲሠዲአኃ)፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ሕብረት (ኢተፓድሕ)፣ ትብብር ለዲሞክራሲ በኢትዮጵያ (ትዲኢ)፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት (ኢዲኃሕ) እና ሌሎች ፓርቲዎች በቡድንና በሕብረት ሆነው ቢመሰርቱም ከመለያየትና ከመበታተን ባለፈ እንቅስቃሴዎቻቸውን መቀጠል አልቻሉም። አንዳንዶቹም መመስረታቸው በውል እንኳ ሳይታወቅ ከመበተን ያለፈ ፋይዳ አልነበራቸውም።
አብሮ የመሥራት ጥላቻ የነገሠበት የተቃዋሚዎች መንደርም ሲሰባሰቡና ሲበተኑ እስከ ምርጫ 97 የዘለቁ ሲሆን፤ በዚህ ምርጫ ወቅት የተፈጠሩት የፓርቲዎች ጥምረት ለህዝቡ መነቃቃትንና አዲስ የፖለቲካ መንፈሥን ፈጥረው ነበር።
ፖለቲከኞቹ ሀገራዊ አቋማቸውን በፕሮግራም፣ በፖሊሲ መልክ ቀርፀው መተዳደሪያ ደንብ አዘጋጅተው፣ ራሳቸውን በድርጅት አዋቅረው ሥራ ከጀመሩ የከራረሙትና አዲስ የተቋቋሙ ድርጅቶች በጋራ በመሆን “ቅንጅት”ን አቋቁመው በሌሎች ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ድርጅቶች ተሞክሮ ያልተሳካውን በጥምረት መሥራት ለመሞከር አንድ ብለው በድጋሚ የጀመሩበት ግዜ ነበር።
መሰባሰብ - መበታተን
መኢአድ፣ ኢዴአፓ - መድህን፣ ኢዴሊና ቀስተደመና በጋራ ሆነው “ቅንጅት”ን በመመስረት በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን አዲስ የፖለቲካ ባህል በማለማመድ ወደ ምርጫ ከገቡ በኋላ ብዙ ርቀት መጓዝ አልቻሉም። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተነጋግሮ ከመተማመን ይልቅ ልዩነትንና መጠፋፋትን፤ ከድርጅት ጥቅም ይልቅ የሥልጣን ጥምን፣ የግል ጥቅምንና ዝናን ማግበስበስ በመምረጣቸው መከፋፈላቸው የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው።
ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ፤ በህዝብ ዘንድ በድንገት ተቀባይነት ያገኘ ፓርቲ ነበር። ነገር ግን በኢህአዲግ በተደረገበት የማዳከም ተፅዕኖ እና በውስጥ ችግሮቹ ምክንያት ብዙም ሳይጓዝ የመበታተን አደጋ ገጥሞታል።
ፓርቲው በ1997 ዓ.ም. ሀገራዊ ምርጫ ላይ ከተሳተፈ በኋላ ከመንግሥት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በተነሳው ረብሻና አመጽ፣ የበርካቶች ሕይወት አልፏል፣ በርካቶች ቆስለዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም ፓርቲው በውስጥ ችግር በመታመሱ እነ አቶ ልደቱ አያሌው ኢዴአፓ-መድህንን ይዘው በመለየታቸው ክፍፍሉ አንድ ብሎ ጀመረ።
አለመግባባቱ እየተካረረ በመምጣቱና በድጋሚ ረብሻ በመቀስቀሱ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ወደ እስር ቤት ሲያመሩ፣ ቀሪዎቹ የፓርቲው አባላት እነ አቶ አየለ ጫሚሶ፣ እነ አቶ ተመስገን ዘውዴ፣ ምርጫ 97 ቡድን በሚል ተከፋፍለው ከእስር የተፈቱትን አመራሮች ተቀበሏቸው። የአመራሮቹ ከእስር መፈታትም የተበታተኑትን ከማሰባሰብ ይልቅ ራሱ ተከፋፍሎ በእንካ ሰላንቲያ ሲታመስ መክረሙ በዚህ ትውልድ የተከሰተ እውነታ ነበር።
በመጨረሻም ፓርቲው በደረሰበት የመጨረሻው የክፍፍል ደረጃ፣ ኢዴአፓ፣ ቅንጅት (የእነ አቶ አየለ ጫሚሶ)፣ የፓርላማ ቡድን፣ መኢአድ፣ ኢዴሊ፣ ግንቦት ሰባት ንቅናቄ እና አንድነት የተባሉ ሰባት ቅርንጫፍ ፓርቲዎችን አፍርቷል። ከዚህ በኋላም ስንት ቅርንጫፎች ሊያፈራ እንደሚችል መገመት አዳጋች ነው።
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ
ቅንጅትን ለመበታተን የዳረገው የውስጥ ችግር፤ የፓርቲው ሕገ ደንብ አለመከበሩ፣ የጥቂት ግለሰቦች አምባገነንነትና፣ የግለሰቦች ፍላጎት ከፓርቲው አጀንዳ በላይ መግነኑ መሆኑን አበክረው ይገልፁ የነበሩትና በቅንጅት አመራርነታቸው የሚታወቁት፣ የኃይል ሚዛኑ ያጋደለላቸው ፖለቲከኞች ተሰባስበው ከቅንጅቱ ስህተቶች መማራቸውን በመግለጽ “አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ” ፓርቲን መሰረቱ።
በቅንጅቱ ውስጥ ወሳኝ ሚና የነበራቸውና በከፍተኛ አመራር ላይ የነበሩት፣ እነ ፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያም፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፣ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም፣ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ እና ሌሎቹም ፖለቲከኞች፤ ከእነ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል ጋር ያላግባባቸው ጉዳይ የፓርቲው ሕገ ደንብ አለመከበሩ፣ የግለሰብ የበላይነት መኖሩና የሥልጣን ፍላጎት በማየሉ መሆኑን በመግጽ የፓርቲውን ሕግና ደንብ አክብረው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት ቡድኖች እነሱ ብቻ መሆናቸውን በይፋ ገልፀው ነበር ፓርቲውን የመሰረቱት። ትናንት በጋራ ሌሎችን ሲወቅሱ የነበሩት ዛሬ ደግሞ በተመሳሳይ ጉዳይ እነሱ እየተወቃቀሱ ይገኛሉ።
ከጅምሩ ከመበተን ያልዳነው “አንድነት”
አንድነት እንደ ፓርቲ አደረጃጀቱ እውን እየሆነ ሲመጣና የድርጅት ቅርጽ መያዝ ሲጀምር የሊቀመንበርነቱን ቦታ ማን ይያዘው? የሚለው አጀንዳ፣ ቦታውን መያዝ ለሚፈልጉ ፖለቲከኞች ራስ ምታት ሆነ። ቦታውን ለማግኘትም በግል የተደረገው የምረጡን ቅስቀሳ ጤናማ ያልሆነ አሉባልታና ጥላቻ፣ ከዚያም ግልጽ ባልሆነ መንገድ እንደ ፓርቲ ቡድናዊ አሠራርን መሠረተ።
ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም ከጅምሩ ከሊቀመንበርነቱ ውድድር ራሳቸውን በማግለላቸው ፉክክሩ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳና በኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው መካከል ሆነ። በመጨረሻ በተደረገው ምርጫ ወ/ት ብርቱካን የሊቀመንበርነቱን ቦታ ሲይዙ፣ ኢ/ር ግዛቸው ም/ሊቀመንበርና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሆኑ። ከምርጫው ማግስት ጀምሮ የሁለቱም ቡድኖች በፓርቲው ውስጥ በጎሪጥ መተያየት ጀመሩ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በዚህ ሁኔታ የነበረውን አለመግባባት አቻችለው፣ ፓርቲውን ለስድስት ወራት ከመሩት በኋላ ታሰሩ።
ከወ/ት ብርቱካን እስር በኋላ
ከወ/ት ብርቱካን እስር በኋላ “የሥራ አስፈፃሚ አባላቱ የፓርቲውን ሥራ በተገቢው መንገድ እየሠሩ አይደለም።” የሚሉ ቀደም ሲልም የወ/ት ብርቱካን ደጋፊ የነበሩ የም/ቤት አባላት ተቃውሞ ማቅረብ ጀመሩ።
የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባላት 18 የነበሩ ሲሆን፤ ውይይት በሚደረግበትና በድምጽ ብልጫ በሚወሰንበት ጊዜ ሰባቱ ከወ/ት ብርቱካን ጋር፣ ስድስቱ ከእነ ኢንጂነር ግዛቸው ጋር አምስቱ ደግሞ መሐል ላይ በመሆን ሃሳብ ሲሰጡ እንደነበር አንድ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ይገልፃሉ።
ከሊቀመንበሯ እስር በኋላ እሳቸውን ጨምሮ አምስት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በመጓደላቸው 13 ሲቀሩ፣ ከነዚህ ውስጥ ቀደም ሲል ከወ/ት ብርቱካን ጋር የነበሩት ሁለቱ በዛኛው ቡድን ውስጥ ወ/ት ብርቱካንን ሲደግፉ የነበሩና መሐል ሰፋሪዎቹ ተቀላቅለው አስራ አንዱን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በአንድ መሥመር ላይ ተገናኙ።
ብቻቸውን ሲቀሩ የምክር ቤቱ አባላት
አንድነት ሲመሰረት 60 የብሔራዊ ምክር ቤት አባላትና 15 ተለዋጭ የምክር ቤት አባላት ነበሩት። ከነዚህ ውስጥ ከ60 የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት 15 በመጓደላቸው ተለዋጮቹ የተተኩ ቢሆንም ከሙሉ ምክር ቤት አባላትና ከተለዋጮቹ ሁለቱ በሞት ሲለዩ፣ ሌሎቹ ወደ ውጭ ሀገር በመሄዳቸው ፓርቲውን ጥለው በመውጣታቸው ሥራ አስፈፃሚውን የሚጨምረው የምክር ቤት አባላት ቁጥር 54 ነው።
ከዚህ ውስጥ 10 የሚሆኑት፣ የብሔራዊ ምክር ቤት አባላትና 11 የፓርቲው አባላት፤ በጋራ በመሆን 11ዱን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፤ የፓርቲውን ሕገደንብ ጥሰዋል፣ ፓርቲው መሥራት የሚገባውን እየሠራ አይደለም፣ ሰዎችን ያለአግባብ እያገደ ይገኛል፣ … የሚሉና ሌሎች ወቀሳዎችን ያዘሉ ክሶችን አቅርበው፣ ክርክር ሲያደርጉባቸው ከቆዩ በኋላ ጥያቄው ተቀባይነት አጥቶ በድምጽ ብልጫ ቢሸነፉም፤ ይህን ባለመቀበላቸው አለመግባባቱ ወደ አደባባይ ወጥቶ ላለፉት አራት ዓመታት በተለያየ ጊዜ የመበታተን አደጋ ሲገጥማቸው ቡድኖቹ በየፊናቸው “የእኛ ቡድን ትክክል ነው። የፓርቲውን ሕገ ደንብና መመሪያ ያከብራል። በዛኛው ቡድን የፓርቲው ደንብ ተጥሷል” የሚሉ ተመሳሳይ ሃሳቦች መቀንቀን ጀምረዋል።
አንድነትም እንደ “ቅንጅት” በሌላ የመበታተን አደጋ ውስጥ ወድቋል? የሚል ጥያቄ አመራሮቹ ሲቀርብላቸው “ፓርቲው ሠላማዊ ሥራውን እየሠራ ነው፤ ይሄ በዲሞክራሲያዊ አሠራር የሚመጣ የሃሳብ ፍጭት ነው። ተከፋፈለ፣ ተበታተነ፣ ተሰነጣጠቀ የሚሉት ጋዜጠኞች ናቸው” በማለት ቀደም ባሉት ጊዜያት ለነበሩት ክፍፍሎች የሰጡት ምላሽ ቃል በቃል የነበረውን ይደግማሉ።
ለዓመታት በእንደዚህ አይነት የመበታተን የፓርቲ ሂደት ውስጥ ያለፉት አመራሮች አንድ ናቸው። አስገራሚው ነገር ሁሌም የሚያነሷቸው የልዩነት ሃሳቦቻቸው፤ “ግልጽነት የለም፣ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አይከበርም፣ ጥቂት አምባገነኖች ነግሰዋል” የሚሉ ተመሳሳይ ጉዳዮች ናቸው፤ ነገር ግን አንዳቸውም ቢሆኑ “ያኛው ቡድን ነው እንዲህ ያደረገው” ከሚል መወነጃጀል ባለፈ “የችግሩ ምንጭ ይኼ ነው፣ እኛ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ጥፋት ሠርተናል” ብሎ ያመነም ሆነ ለችግሩ መንስዔ ራሱን ተወቃሽ ያደረገ ፖለቲከኛም ሆነ ቡድን የለም። በአፍ የሚናገሩትን የፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ የፓርቲ የዲሞክራሲ መርኅና ሌሎች ለዲሲፕሊን ተገዢ የሚያደርጉ ሥነሥርዓቶችን ማን ሊያከብርላቸው ይሆን?
ለፓርቲዎች መበተን - ሁለት ምክንያቶች
የመንግሥት ሥልጣን የያዘው ገዢ ፓርቲ የሚቀርፃቸውን ፖሊሲዎችና፣ ብልሹ አሠራሮችን በመቃወም “የህዝብ” ያሏቸውን ብሶቶችና ጥያቄዎች ይዘናል፣ ብለው የሚደራጁ ከዛም ለጋራ ዓላማ በሚል የሚተባበሩና የሚጣመሩ ድርጅቶች በሁለት ምክንያት መበተን ሊያጋጥማቸው ይችላል።
አንደኛው ፓርቲዎቹ የውስጥ ችግራቸውን አቻችለው ድርጅታቸውን በማጠናከር፣ ደጋፊ አሰባስበው፣ የህዝብ ብሶቶችን ማስተጋባት ሲጀምሩ፣ በኢህአዲግ የጠለፋ ስልት ተመተው ይወድቃሉ። ፓርቲዎቹም ቢሆኑ ቀደም ሲል በጠንካራ መሰረት ላይ ያልተገነቡ በመሆናቸው ቶሎ ይበታተናሉ።
ፖለቲከኞቹም ቀደም ባሉት ጊዜያት በራሳቸው የውስጥ ችግር ምክንያት ተጠላልፈው፣ ከወሬ ባለፈ ቁምነገር መሥራት ሲያቅታቸው ለመበታተናቸው ተጠያቂውን ኢህአዲግ የማድረግ አባዜ ተጠናውቷቸዋል።
የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት፤ አንድ ፓርቲ በተጠናከረ ቁጥር፤ በውስጡ ጥርጣሬና መከፋፈል እንዲኖር ኢህአዲግ የሚሠራው ሥራ እንደሚኖር ይናገራሉ። ኢህአዲግ የመንግሥትነት ሥልጣን፣ ኃይልና ገንዘብ ያለው ድርጅት በመሆኑ እንዲህ ያሉ የመበተን ሙከራዎችን ከመሥራት ሊያግደው የሚችል ነገር እንደማይኖር፤ ነገር ግን ፓርቲዎቹ ቀድሞውንም መሰረታቸው ጠንካራ ከሆነ በእንደዚህ ያለ ሙከራ ሊበተን እንደማይችሉ ጨምረው ይገልፃሉ።
አንድ የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር ስለዚህ ሁኔታ ሲያስረዱ፤ የመንግሥትነት ሥልጣን በእጁ የጨበጠ ፓርቲ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተጠናክረው እንዳይወጡ በስውር የሚያደርጋቸው ማዳከሞች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፤ ቀደም ሲል በነበሩት የተፎካካሪ ፓርቲ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥም ኢህአዲግ ተመሳሳይ ነገሮችን ሲሠራ መታየቱ የታሪክ ሐቅ እንደሆነ ያስረዳሉ። “ነገር ግን” ይላሉ የፖለቲካ ሣይንስ ምሁሩ፤ “ፓርቲዎቹ ለእንዲህ አይነት አደጋ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉት ውስጣቸውን አጠናክረው የህዝብ አጀንዳዎችን ይዘው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ነው። አሁን ያሉት ፓርቲዎች ቀድሞውኑ ከሚንደፋደፉበት የውስጥ ችግራቸው ወጥተው “ተነሳንለት” የሚሉትን የህዝብ አጀንዳ ማንቀሳቀስ ሳይጀምሩ፣ “ገዢው ፓርቲ ያደክመናል” የሚል መከራከሪያ ቢያነሱ የማዳከም ሙከራው መደረግ አለመደረጉን ከመስማት ባለፈ ልናየው አንችልም” ብለዋል።
ቀደም ሲል የመኢአድ አባል የነበሩ፣ በቅንጅት ግዜ የችግር አስወጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው የሠሩ፣ ከእስር ከተፈቱ በኋላም ከኢ/ር ኃይሉ ሻውል ጋር በተደረገው ክፍፍል፤ ከፕሮፌሠር መስፍንና ከወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ሆነው “ያኛው ወገን የፓርቲውን ደንብ አላከበረም” በሚል ከቡድኑ ተለይተው የነበረ ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ፤ እነ ፕሮፌሠር መስፍንን ለዲሲፕሊን ተገዢ አይደሉም ሲሉም እየወቀሷቸው የሚገኙት የፓርቲው ም/ሊቀመንበርና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፤ “የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዲሞክራሲያዊ ያልሆኑት የመንግሥትነት ሥልጣን የያዘው ፓርቲ ኢ-ዲሞክራሲያዊ በመሆኑ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
ይህን ሃሳባቸውን ሲያስረዱ ምሳሌያቸውን የሚጀምሩት ኢትዮጵያን ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት ጋራ በማቆራኘት ሲሆን፤ ከሁለት ሀገሮች በስተቀር የአብዛኛው አፍሪካ ሀገራት ገዢ መንግሥታት ኢ-ዲሞክራሲያዊ በመሆናቸው ሥልጣናቸውን ላልተገደበ ጊዜ የማቆየት ባህሪ አላቸው። የሥልጣን ጊዜያቸውን ለማራዘም ስለሚፈልጉ የሚያካሂዷቸው ምርጫዎች የይስሙላ ናቸው። በዚህም ምክንያት ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲያድጉ አይፈልጉም በማለት ለፓርቲያችን መዳከም ሥልጣን ላይ ያሉትን መንግሥታት ይኮንናሉ።
ለአንድ ፓርቲ መጠናከር ምሁራን ወደ ፓርቲ መምጣታቸው የግድ መሆኑን የሚገልፁት ኢንጂንየሩ፤ ምሁራን ወደ ፓርቲ እንዳይመጡ ደግሞ ገዢው ፓርቲ በተለያየ መንገድ በሚፈጥረው ተጽዕኖ ሕይወታቸው እንዳይናጋ ስለሚሰጉ ከፖለቲካው መድረክ ምሁራን ይገለላሉ፤ ይሄ ለፓርቲዎቹ ኢ-ዲሞክራሲያዊ መሆን መንገድ ከፋች ነው ይላሉ - ኢ/ር ግዛቸው።
በዚህ ጉዳይ የማይስማሙት ፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማሪያም፣ “የቅንጅት ጅማሮ በግልጽነትና ተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ ስለነበር በርካታ ምሁራን ፓርቲውን ሲቀላቀሉ ታይተዋል። ነገር ግን ፓርቲዎቹና ፖለቲካው እውነተኛ የዲሞክራሲ መሠረት የያዙ ባለመሆናቸው እና ምሁሩ ደግሞ የታፈነ ሥርዓት ውስጥ መግባት ስላማይፈልግ ወደ ኋላ ሲያፈገፍግ እንደሚታይ አስተያየት ይሰጣሉ። ስለዚህም ያሉት ፓርቲዎቸ ውስጣቸውን በዲሞክራሲያዊ አሠራር አጥርተው በትክክለኛው አሠራር ከሄዱ፣ ምሁራንም ወደ ተቃዋሚዎች መንደር ይመጣሉ።” የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ።
ለመበታተን - የውስጥ ችግር
የቅርብ ጊዜ ክስተቶች እንደሚያሳዩት ፓርቲዎች ተጠናክረው በሕብረት እንዳይሠሩ የሚያደርጋቸው ዋና ችግራቸው የውስጥ ነው። ላለፉት አሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያደራጁ ግለሰቦች ወደ ተቃውሞው ጐራ ሲቀላቀሉ፣ የተነሱለትን ዓላማ ወደ ጐን በማድረግ፣ ከድርጅታቸው ጉዳይ ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም መጠበቃቸው አብሮ የመሥራት እንቅፋታቸው ነው።
“ሰዎች በጋራ ለመሥራት በሚሰባሰቡበት ጊዜ በአለመለካከት፣ በርዕዮተ ዓለም፣ በአሠራር፣ የፖለቲከኞቹ ግላዊ ባህሪ፣ አመለካከት እና በፖሊሲ ልዩነቶች አለመግባባት ሊከሰት ይችላል። እንዲሁም የሥልጣን ፍላጎት የራሱን ሽኩቻ ሊፈጥር ይችላል። መበታተን የፖለቲካ ሂደት ባህሪ ነው የሚል እምነት ባይኖረኝም እነዚህ ልዩነቶች ሁሌም ወደ መበታተንና መከፋፈል ሊወስዱ የሚችሉ ችግሮች ናቸው” የሚሉት አቶ ገብሩ አስራት፤ ፓርቲው ቀድሞውኑም አሠራሩን በሕገ ደንቡ ላይ በመመርኮዝ ከገነባው እነኚህ ችግሮች ሲከሰቱ፣ የፓርቲው አሠራር፣ ሕገ ደንቡን ተከትሎ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፍታት ከቻለ፣ ጤነኛ የኾነ አካሄድ ሊመጣ እንደሚችል ይጠቁማሉ።
“በአንድ ፓርቲ፣ በሕብረትም ኾነ በቅንጅት ጠንክሮ ያለመውጣት መሠረታዊ ችግር የኢትዮጵያ የፖለቲካ ገጽታ ብቻ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም” የሚሉት ኢ/ር ግዛቸው፣ የኢትዮጵያን ጉዳይ ከአፍሪካ ጋራ በመደመር “በኢትዮጵያና አፍሪካ ሀገሮች ያለው የዲሞክራሲና የፖለቲካ ባህል ዝቅተኛ በመሆኑ ነው” ይላሉ። በኢትዮጵያ ፖለቲካና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ልምድ ያላቸውና በሦስቱ መንግሥታት ዘመን ያለፉት ፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያም፤ ፓርቲዎች አብረው መሥራት ያልቻሉት የውድድር ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ባህል በመሆኑ ነው ይላሉ።
በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ያለ የሚመስል ውድድር በኢትዮጵያ የተጀመረው በቅርብ በመሆኑ፤ የተማረው፣ ያልተማረው፣ እዚሁ ሀገር በፖለቲካ ውስጥ ብዙ የቆየውም ሆነ ከፈረንጅ ሀገር የመጣ በፖለቲካው ጉዳይ አስተሳሰባቸው አንድ አይነት መሆኑን ይናገራሉ። “በኢትዮጵያ ታሪክ የተለመደው ደግሞ ሥልጣን በብቃትና በችሎታ ሳይሆን በሹመት ሲሰጥ ነው” ይላሉ።
“በአንድ ላይ እኩዮች ሆነው ተሰባስበው አንድ ሰው ይመርጣሉ። የተመረጠው ሰው የተመረጠበትን ዓላማ ይስትና ራሱን እንደ ደጃዝማች ሌሎችን ደግሞ እንደ ሎሌ መመልከት ይጀምራል፤ ይህን የሚያደርገው አንዴ ሥልጣን ላይ ወጥቶ ወንበሩን ከተቆናጠጠ በኋላ ወርዶ ሌላ ሥራ መሥራት አይፈልግም፤ ምክንያቱም ሥልጣኑ የሚሰጠውን ሦስት ነገር ማጣት ያስፈራዋልና ነው” ይላሉ ፕ/ር መስፍን።
“ሥልጣን ኃይል ነው፣ ሥልጣን ሀብት ነው፣ ሥልጣን ዝና ነው” የሚሉት ፕሮፌሠር፤ የግል ጉዳያቸውን ትተው ራሳቸውን ለድርጅት ጉዳይ ያላስገዙ ፖለቲከኞች ሥልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ ሥልጣን የሚሰጣቸውን እነዚህን ሦስት ጉዳዮች ላለማጣት አምባገነን ሆነው ለረጅም ጊዜ ይቀጥላሉ። ይህንን የማይቀበሉ ሌሎች ሰዎች አማራጭ ስለማይኖራቸው ፓርቲውን ጥለው ይወጣሉ።” ይላሉ። “እኔ የማምንበት ዋናው ጉዳይ ፓርቲዎች በጋራ ተጠናክረው መሥራት የማይችሉበት ዋናው ምክንያት የሥልጣን ጥመኞች በሚፈጥሩት አምባገነናዊነት ምክንያት ነፃና ግልጽ የሆነ ዲሞክራሲያዊ አሠራር በፓርቲ ውስጥ አለመኖሩ ነው።” ብለዋል።
ለመበታተኑ ችግር ነው የሚሉትን ምክንያት አብጠርጥረው የሚገልፁት፣ የሚመሯቸው ፓርቲዎች በተደጋጋሚ የመበታተን አደጋ የሚገጥማቸው አመራሮች ሲሆኑ፤ ላለፉት ዓመታት ለችግሮቹ መንስዔ በመፈለግ ፓርቲዎቻቸውን ከመበተን አደጋ ጠብቀው ዲሞክራያዊ አሠራር የሰፈነበት አማራጭ ፓርቲ ለመመስረት ያልቻሉበትን ምክንያት ሲጠየቁ ሁሌም ጣታቸውን ወደ ሌሎች ይቀስራሉ።
የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ከፍተኛ የኢህአዲግ ባለሥልጣንና የአሁኑ የመድረክ አባል አቶ ስዬ አብርሃ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ በፖለቲካ፣ በሀገራዊና፣ በህዝብ ጥያቄዎች (Issues) ላይ ማነጣጠር እንዳለበት ይናገራሉ። የመበታተኑ መንስዔ ነው ብለው የሚያስቡት ደግሞ ከፖለቲካ ጉዳዮች እና ጥያቄዎች እንዲሁም ከድርጅቶቹም በላይ ዋናው ጉዳይ ግለሰቦች መሆናቸው ነው ይላሉ። አንዳንድ ጊዜም ከሀገርና ከህዝብ ጉዳይ በላይ ዋናው አጀንዳ ፓርቲው ይሆናል። ትኩረቱ ወደ ዋናዎቹ የሀገርና የህዝብ ጉዳዮች እንዳይደረግ የፓርቲዎቹ ጉዳይ መግነን ችግር ይፈጥራል የሚሉት አቶ ስዬ፤ ፖለቲከኞቹ የተነሱለትን ዓላማ ስተው ወደ ሌላ አቅጣጫ ሲያተኩሩ ችግሩ ጐልቶ እንደሚወጣም ያስረዳሉ።
የመፍትሔ አቅጣጫ ሲያስቀምጡም፤ “የሰዎች ትኩረት ወደ ዋናው ፖለቲካዊና አንገብጋቢ የሀገር ጉዳዮች እንዲያተኩር ከአሉባልታና ከእንካ ሰላንቲያ ወጥቶ በፖሊሲ ጉዳዮች እንዲያተኩር ማድረግ ያስፈልጋል። ሰዎች በዋና ዋና የሀገር ጉዳዮች ምን አቋም ያዙ? የሚለው ግልጽ መውጣት አለበት። ሁሉም ተደራጅቶና ተባብሮ የመታገልን አስፈላጊነት ይናገራሉ። ነገር ግን ድርጅት ለመፍጠር ከራስ ነፃነት ቆርጦ መስጠት ያስፈልጋል። የራስን ኢጐ (ego) ለድርጅት ተገዢ ማድረግ ያስፈልጋል። የጋራ ለሆኑት ነገሮች ስኬት ራስንም መጨቆን፣ ራስን ማስገዛት፣ ከራስ ነፃነት ከግለኝነት ቆርጦ መጣልና ለቡድን ሥራ ራስን ማስገዛት ይጠይቃል” ሲሉ ይመክራሉ።
ግለሰቦች “ጉዳይ” ከመሆናቸው አሠራር በመውጣት የህዝብ ዋና ዋና ጉዳዮች፣ “ጉዳይ” የሚሆኑበት ደረጃ ላይ መድረስ ያስፈልጋል።
አያይዘውም “የፖለቲከኞቹ አስተሳሰብ ማደግ አለበት። ግለኝነትን ማዕከል ካደረገ አስተሳሰብ ወጥቶ ለጋራ ጥቅም ራስን ማስገዛት ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ የተለመደው የፖለቲካ ባህል ፈጥኖ በፓርቲ መሰባሰብና በተፈለገው ጊዜ መበተን ነው።
“ፖለቲከኞች ፓርቲውን በፈለጋቸው ግዜ ጥለው ሲመጡ የሚያጡት ብዙ ነገር የለም። መራጩም ጉልበት የለውም፣ የመረጠውን የፓርቲ አባል አይቆጣጠርም። ሁሉም የራሱ ንጉሥ ነው። ቡድኑ በግለሰቦች ላይ ሞራላዊና ፖለቲካዊ ኃይል የለውም። ለቡድኑና ለጋራ አጀንዳ ተገዢ እንዲሆኑ የሚያደርግበት ጉልበት የለውም። ይህን ለማስጠበቅ የሚችሉ የተጠናከሩ ቡድኖችም የሉም። ከግል አጀንዳ ይልቅ የድርጅት አጀንዳን የሚያስቀድም የፖለቲካ ባህል እድገት ያስፈልጋል። ችግሩ በሂደት እየተቀረፈ ይመጣል።” ሲሉ አቶ ስዬ ተስፋ ያደርጋሉ።
“ችግሩን አውቀው ተባብረው በቡድንና በጋራ ሆነው መጓዝን ካልተቀበሉ ወደ ሥልጣንም ሊመጡ አይችሉም፤ ስለዚህ ወደ ሥልጣን ለመጠጋት የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ የፖለቲካ ዲሲፕሊንን እና ድርጅታዊ ዲሲፕሊን ሊኖራቸው ይገባል። ይሄን ሲያደርጉ በቡድን መሥራት ራስን ለትልቅ ቁምነገር ማስገዛት ይመጣል፤ ከዛም ስብስቦች ይፈጠራሉ በጋራ መክረው፣ በጋራ ወስነው በጋራ መንቀሳቀስ ይለምዳሉ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የጎደለው በጋራ መሥራት ነው። ይህንን የፖለቲካ እድገት ማረጋገጥ ካልተቻለ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እንዴትስ ብለው ህዝብ ያሰባስባሉ? እንዴትስ ብለው መንግሥት ይመራሉ? እየተንገዋለሉ ያሉት ነገሮችን ገትቶ የያዘው ችግር፣ ካልተፈታ የትም አይደርሱም።” በማለት ሃሳባቸውን የሰጡት አቶ ስዬ ናቸው።
“በኢትዮጵያ 92 በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ ፓርቲዎች አሉ። ብዙ ፓርቲዎች መኖራቸውም የዚህ በሽታ ምልክት ነው።” የሚሉት አቶ ስዬ “ከዚህ ወጥተን ጉልበታችንን እናሰባስብ፤ እጅ ለእጅ እንያያዝ ያለማለታቸው አጠቃላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር ውስጥ መግባቱን ያሳያል። ቀስ በቀስ ግን መሪዎቹም ደጋፊዎቹም በአስተሳሰብ ይበስሉና አንድ ነጥብ ላይ ይደርሳሉ። ደጋፊዎቹ መሪዎቻቸውን አደብ ማስገዛት የሚችሉበት ሁኔታ ይመጣል።” በማለት ለዓመታት በክፍፍል የሚታመሰው የተቃዋሚዎች ፓርቲዎች መንደር አንድ ቀን ሊረጋጋ እንደሚችል ይገምታሉ።



