Ethiopia Zare (ረቡዕ ሐምሌ 29 ቀን 2001 ዓ.ም. August 5, 2009)፦ ፕ/ር መስፍንን ጨምሮ 21ዱ የታገዱት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት “የአንድነት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሥልጣን መባለግ” በሚል በተከታታይ ሲያወጡት የነበረውን መግለጫ ክፍል ሦስት አወጡ። ይኸው መግለጫ “በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ደንባዊና ተቋማዊ አሠራር ሲፈተሽ” የሚል ንዑስ ርዕስ ሰጥተውታል።

 

የታገዱት አባላት በዚሁ መግለጫቸው ላይ፤ “የዲሲፕሊን ኮሚቴ አሰያየም”፣ “የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት ቁጥር”፣ “የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት ጥንቅር”፣ “ክስ በይርጋ ስለመታገድ”፣ እንዲሁም “የሕግና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴንና የዲስፕሊን ኮሚቴዎችን ተግባር ማቀላቀል” የሚሉ ነጥቦችን አንስተዋል።

 

መግለጫው “… ይህ የገዘፈ የፓርቲን የሥነ ሥርዓት መመሪያ ከፓርቲው አካላት ውሳኔ ውጭ በሽምቅ የመቀየር ሕገ-ወጥ ተግባር በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አባላት በሙሉ ተመክሮበት የተፈፀመ ነው ለማለት ያስቸግራል። ስለሆነም የሥራ አስፈፃሚው አባላት የዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር ተባባሪ ካልሆኑ ድርጊቱን በግልፅ ማውገዝና በአፋጣኝ እንዲታረም ማድረግ ይኖርባቸዋል። …” በማለት ለመላው የሥራ አስፈፃሚ አባላት ጥሪ አስተላልፏል።

 

ሙሉውን መግለጫውን ከዚህ በታች ያቀረብነው ሲሆን፣ ያለፉትን ሁለት ክፍሎች ለማንበብ ከፈለጉ፦ ክፍል አንድን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!ክፍል ሁለትን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!

 

የአንድነት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሥልጣን መባለግ - ክፍል ሦስት

በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ደንባዊና ተቋማዊ አሠራር ሲፈተሽ

 

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊና ተቋማዊ አሰራሩን በመከተል የተነሳለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚችለው መተዳደሪያ ደንቡ ተከብሮ፣ መርሆዎቹ ተጠብቀውና የአመራር አባላቱና አካላቱ ለሕግ የበላይነት ተገዥ ሆነው በአንድ መንፈስ መታገል ሲችሉ ብቻ ነው። ለዚህም ተግባራዊነት የሥነ ሥርዓት መመሪያ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑ በመተዳደሪያ ደንባችን አንቀጽ 11፣9 ላይ ተገልጧል። በፓርቲያችን ውስጥ የሚወጡ ማናቸውም መመሪያዎች ለፓርቲው ዓላማ ከግብ መድረስ የሚያግዙ፣ ደንቡን መሠረት ያደረጉና በማናቸውም ጊዜ ወደ ኃላፊነት በሚወጡ ሰዎች ሊፈፀሙ የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል።

 

ደንብም ሆነ መመሪያ ወቅታዊ ችግርን ብቻ ታሳቢ አድርጐ፤ አለበለዚያም ወንበርን ለማስጠበቅ ታስቦ አይዘጋጅም። ዛሬ በኃላፊነት ላይ የሚገኡ ሰዎች መመሪያ ሲያወጡ ነገ በቦታው ላይ ሊኖሩ እንደማይችሉ እያሰቡ መሆን ይኖርበታል።

 

ዘግይቶም ቢሆን የወጣው የፓርቲያችን የሥነ ሥርዓት መመሪያ ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲሆን ብዙ ጥረት ተደርጐ በብሔራዊ ምክር ቤቱ የፀደቀ ቢሆንም በፓርቲያችን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ የሚገኘው ቡድን የተወሰኑ አንቀጾችን በማውጣትና ሌሎችን ደግሞ በመለወጥ መመሪያው የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ፍትሃዊ አሰራር ለማስፈን የሚያስችል ሳይሆን፤ የቡድኑን ፍላጐት ለማሳካት የሚጠቅም አድርጐታል።

 

1. የዲሲፕሊን ኮሚቴ አሰያየም

 

በፓርቲ ውስጥ የሚቀርቡ የሥነ ሥርዓት ክሶችን ተመልክቶ ፍትሃዊ ውሳኔ መስጠት አንድነት የቆመለትን የሕግ የበላይነት መከበር መርህ ለማጽናት የሚቻለው በሥነ ሥርዓት መመሪያው የመክሰስ ሥልጣን ከተሰጣቸው አካላት ተፅዕኖ ነፃ የሆነ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሲኖር ነው። ይህም በመሆኑ በብሔራዊ ምክር ቤቱ የፀደቀው የሥነ ሥርዓት መመሪያ አንቀጽ 7፣1 «የዲስፕሊን ኮሚቴው በሕግና ሥነ ሥርዓት ቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት የሚቋቋም ሆኖ በብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴውና በብሔራዊ ምክር ቤቱ ይፀድቃል» ተብሎ ተደንግጓል። በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ የሚገኘው ቡድን ግን ይህን አንቀጽ ከመመሪያው ውስጥ በማውጣት በዲሲፕሊን ኮሚቴ ስም ሕገ-ወጥ ቡድን አቋቁሟል። የዚህ አንቀጽ ከመመሪያው ውስጥ መውጣት ትክክለኛ ፍትህ በመስጠት የፓርቲውን ደንብ የሚያከብርና የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ተግባር ለማከናወን የሚያስችል እውቀቱና ልምዱ ያላቸው ሰዎች ወደ ኮሚቴ አባልነት እንዳይገቡ በማድረግ በሕግ ስም ፍላጐትን ለመፈፀም ያስችላል።

 

2. የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት ቁጥር

 

በብሔራዊ ምክር ቤቱ የፀደቀው የዲስፕሊን መመሪያ አንቀጽ 6፣2 በብሔራዊ ደረጃ የሚቋቋመው የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት ቁጥር ሰባት (7) እንዲሁም ከዚያ በታች የሚገኙ የፓርቲ መዋቅሮች የዲሲፕሊን ኮሚቴ ደግሞ አምስት (5) አባላት እንዲኖረው በሥነ ሥርዓት መመሪያው አንቀጽ 6፣3 ላይ ተደንግጓል። ይህም የሆነው የኮሚቴዎቹ አባላት ቁጥር በርከት ማለት ጉዳዩን በጥልቀት አይቶ፣ መርምሮና በመረጃ አረጋግጦ ፍትሃዊ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል በመሆኑ ነው።

 

ነገር ግን በሥራ አስፈፃሚው ውስጥ ያለው ቡድን ይህን በመለወጥ በሁሉም ደረጃ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት ቁጥር ሦስት (3) ብቻ እንዲሆን በማድረግ ከመመሪያ ውጭ ለተሰየመ የዲሲፕሊን ኮሚp ሰብሳቢ ሊሆን የማይገባውን የሥራ አስፈፃም ኮሚቴ አባል የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሰብሳቢ በማድረግ ሕገ-ወጥ በሆነ መመሪያ ነው አቶ ታምራት ታረቀኝ ከፓርቲው እንዲባረሩ የተደረገው።

 

በመሠረቱ ቀድሞውንም የሥነ ሥርዓት መመሪያው የብሔራዊ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት ቁጥር ሰባት (7) እንዲሆን የተደረገው የኮሚቴ አባላትን በመደለል ፍትህን ለማዛባት ሊኖረው የሚችለውን እድል ለማጥበብ ነው። የኮሚቴ አባላት ቁጥር ሦስት (3) ሲሆን ጉዳዩን በስፋት ለማየት ያለው እድል በጣም ጠባብ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የኮሚቴው አባላት ሁለቱ (2) ከተገኙ ምልዐተ ጉባዔ ሞልቷል ስለሚባል በሁለት ሰው መወሰን ይቻላል። ሁለቱ በድምፅ ቢለያዩ የሰብሳቢው ድምፅ ብልጫ ስላለው በአንድ ሰው ድምፅ ብቻ ውሳኔ ላይ እንዲደረስ ያመቻል። የኮሚቴው አባላት ሰባት ከሆኑ ግን ጉዳዩን ከተለያየ አቅጣጫ የማየት ሰፊ አቅም ይኖራል። ኮረም ለመሙላት አራት ሰው መገኘት ይኖርበታል። አራት ሰዎች ተገኝተው የድምፅ ልዩነት ቢፈጠር የመጨረሻው ትንሽ ቁጥር የሚሆነው ሁለት ድምፅ በመሆኑ በአንድ ድምፅ የሚወሰንበት ሁኔታ አይኖርም።

 

3. የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት ጥንቅር

 

የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት ክስ ለመመስረት ስልጣን ከተሰጣቸው አካላት ውጪ መሆን ብቻ ሳይሆን በእነርሱ ተፅእኖ ስር የማይወድቁ መሆናቸው ለፍትሀዊ ውሳኔ መገኘት በጣም ወሳኝ ነው። ይህም በመሆኑ ነው በየደረጃው የሚቋቋሙ የዲሲፕሊን ኮሚቴዎች የራሳቸው ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢና ፀሐፊ እንደሚኖራቸው በብሔራዊ ምክር ቤቱ በፀደቀው የሥነ ሥርዓት መመሪያው አንቀፅ 6፡4 ላይ በግልፅ የሰፈረው። አንድነት ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ያለው ቡድን ግን የሕግና ስነስርአት ኮሚቴ አባላትን የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት አድርጎ ከመሰየሙም በላይ መመሪያው የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሆኑ የማይፈቅድላቸውን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የሕግና ሥነ ሥርዓት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ ንጉሤ ነውጤን የሁለቱም ኮሚቴዎች ሰብሳቢ አድርጐ ሰይሟል። ይህም የአቋቋመውን አካል ፍላጎት ከማስፈፀም ውጭ በአባላት ላይ አለአግባw ለሚቀርብባቸው ክስ ፍትሃዊ ውሳኔ እንዲያገኙ የሚረዳ አይደለም።

 

4. ክስ በይርጋ ስለመታገድ

 

በፓርቲያችን ውስጥ ተፈፀሙ የሚባሉ ጥፋቶች በተፈለገ ጊዜ የሚነሱ ከሆነ ፍትህና ደንብ ለማስጠበቅ ሳይሆን ለበቀል ሊውል ስለሚችል ክስ የሚቀርብበት የጊዜ ገደብ ወሰን ሊበጅለት ይገባል። በመሆኑም በሥነ ሥርዓት መመሪያው አንቀፅ 12፣4 «ማንኛውም የድሲፕሊን ጥፋት መፈፀሙ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ካልቀረበ በይርጋ እንደሚታገድ» ተደንግጓል። በሥራ አስፈፃሚው ውስጥ ያለው ቡድን ግን ይህን የመመሪያውን የጊዜ ገደብ በሽምቅ ስልቱ ወደ ስድስት ወር ቀይሮታል። ይህ የይርጋ ጊዜ የተቀየረበት ዋናው ምክንያት በሥራ አስፈፃሚው ውስጥ ያለው ቡደን ከፓርቲው ሊያባርራቸው በሚፈልጋቸው አቶ አምሃ ዳኘው ላይ ክስ የመሰረተው «ጥፋት አጥፍተዋል» ከተባለበት ጊዜ ከሦስት ወር በኋላ በመሆኑና በፓርቲው በፀደቀው የዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት ክሱ በይርጋ የሚታገድ ስለሆነበት ነው። በመመሪያው ላይ የሠፈሩ አንቀጾችን ሳያይና ሳያገናዝብ ክስ የመሠረተው ሥራ አስፈፃሚው ውስጥ ያለው ቡድን ይህን አንቀጽ ወደ መለወጥ ሕገወጥ ተግባር የገባው አቶ አምሃ ዳኘው ለደረሳቸው ክስ በጻፉት የመልስ ደብዳቤ ክሱ በመመሪያው መሠረት በይርጋ የሚታገድና አመራሩም ክስ ለመመሥረት የማይችል መሆኑን በመግለፃቸው ነው።

 

5. የሕግና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴንና የዲስፕሊን ኮሚቴዎችን ተግባር ማቀላቀል

 

የሕግና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ በመተዳደሪያ ደንባችን አንቀፅ 37 መሰረት የሚቋቋም እና በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሚመራ ሲሆን የብሄራዊ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ደግሞ በሥነ ሥርዓት መመሪያው አንቀፅ 7 መሰረት የሚቋቋም ነው። በመሆኑም ሁለቱ ኮሚቴዎች አደረጃጀታቸውም ሆነ ተግባራቸው የተለያየ ነው። በአንድነት ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ የሚገኘው ቡድን ግን ይህን በመሻር ለውጦ ባቀረበው የዲሲፕሊን መመሪያ አንቀፅ 8፡1 ላይ «በብሄራዊ ደረጃ የሚቋቋመው የሕግና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ የሚቀርብለትን ክስ ሰምቶ ውሳኔ ይሰጣል» በማለት ለውጦታል። በተግባርም የሕግና ሥነ ሥርዓት ቋሚ ኮሚቴ አባላት የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት እንዲሆኑ አድርጓል። በዚህ አድራጎቱም በሥነ ሥርዓት መመሪያው ክስ የማየት ስልጣን ያልተሰጠው አካል ክስ እንዲያይ በማድረግ የሁለቱ ኮሚቴዎች ሥራ መለያ መስመር የሌለው እንዲሆን አድርጎታል።

 

ዛሬ የሥነ ሥርዓት መመሪያን በመለወጥ ሕገ ወጥ ተግባር ለመፈፀም የደፈረው ሸማቂ ቡድን ይህ ተግባሩ ከአሁኑ ካልተገታ የፓርቲውን ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ እንዳሻው ከማድረግ የሚመለስ አይሆንም። በጀመረው የፖለቲካ ውሳኔ በመቀጠልም ፓርቲያችንን ከተነሳለት አላማ በተቃራኒ የሚወስደው ይሆናል። ስለሆነም እዛ ደረጃ ከመደረሱ በፊት አባላትና ደጋፊዎች ይህን ሕገ ወጥ ተግባር የሚፈፅመውን ቡድን ለይቶ በማወቅ ለመፍትሄው ዛሬውኑ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። በአብዮታዊ እርምጃ ጥያቄን ማፈን የልዩነት ሀሳብንም ማጥፋት እንደማይቻል ከራሳችን ታሪክ አለመማራችን ያሳዝናል። የሚበጀውና ዘላቂ መፍትሄም የሚያስገኘው ለጥያቄዎች ትክክለኛና ሕጋዊ መልስ መስጠት፣ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ሀቅን ይዞ በድፍረት መነጋገር፣ ከበቀለኝነት ከጥላቻና ከማንአህሎኝነት ስሜት ጸድቶ ከወንበር ፍቅር በላይ ለፓርቲ ዓላማ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ነው። ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ጊዜያቶች የባከኑ ቢሆኑም አሁንም ጨርሶ አልመሸምና እያጨበጨቡ ወደ ገደል ከሚገፉ አማካሪዎች ለየት ብሎ ተጨባጩን እውነታ በመገንዘብ ለእርምት ራስን ማዘጋጀት ከአንድነት አማራሮች ይጠበቃል።

 

ይህ የገዘፈ የፓርቲን የሥነ ሥርዓት መመሪያ ከፓርቲው አካላት ውሳኔ ውጭ በሽምቅ የመቀየር ሕገ-ወጥ ተግባር በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አባላት በሙሉ ተመክሮበት የተፈፀመ ነው ለማለት ያስቸግራል። ስለሆነም የሥራ አስፈፃሚው አባላት የዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር ተባባሪ ካልሆኑ ድርጊቱን በግልፅ ማውገዝና በአፋጣኝ እንዲታረም ማድረግ ይኖርባቸዋል። አባላቱም በመተዳደሪያ ደንባችን አንቀፅ 6፣1፡3 የተገለፀውን የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብና ፕሮግራም መከበሩን የመከታተል መብታቸውን ተግባራዊ በማድረግ አንድነትን ለመታደግ የተጀመረው ጥረት አካል እንዲሆኑ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን። ዝም አንልም!!

 

የአንድነት ፓርቲ ጉዳይ የሕዝብ ጉዳይ ነው!!

የአንድነት መርህ ይከበር ከሚሉ የአንድነት አባላት

ሐምሌ 26 ቀን 2001 ዓ.ም.

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ