ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ (ክፍል አንድ)

Prof. Getachew Hiale and Prof. Fikre Tolossa

ውድ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

ለጤናዎ ባያሌው እንደምን ሰነበቱ? ድምፆቻችንን ከተሰማማን ብዙ ጊዜ ሆነን አይደል? እኔ ለጤናዬ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። ርስዎን እንደ አላመምዎት ተስፋ አደርጋለሁ።

የእኔን አዲስ መጽሐፍ አስመልክቶ ርስዎ ስተለተቹት ከመመለሴ በፊት (ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ”የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ አስተዋፅኦ” በሚል ርዕስ የሰጡትን ትችት ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)፣ የተከበሩት ሊቀ-ሊቃውንት መሪራሰ አማን በላይ ለአንባብያን አስተላልፍላቸው ዘንድ የሰደዱልኝን የአደራ መልዕክት አቀርባለሁ። ከዛ በኋላ ወደ ራሴ ምላሽ እሸጋገራለሁ። ለአንባብያን የተላከ የመሪራስ አማን በላይ መልዕክት እነሆ፦ 

ይድረስ ይህን ለምታነቡ ሁሉ የአገሬ ሰዎች፣

የተወለድኩት፣ የአደግኩትና የተማርኩት በዛው በጎንደርና በጎጃም ነው። የትውልዴ ስፍራ በለሳ ነው። አባቴ መምህር በላይ ድሉ ካኅን ነበሩ። ከውድ አባቴ ከመምሀር በላይ፣ ከአባ ጼሄማ በጎንድ ተክለኃይማኖት፣ ከመሪጌታ መንክር ደብረኤልያስ ጎጃም፣ ከመሪጌታ ጉባኤ በዛው በጎጃም፣ ቅዳሴን፣ ቅኔን፣ ዜማን፣ ብሉይን፣ ሃዲስን፣ የእንጨት አዋጅን (የመድኃኒት እጽዋትን)፣ የሃረግ ስዕልን፣ የኢትዮጵን ታሪክ፣ አቡሻህርን (ባህረሃሳብን) እና ሌሎችንም በአድባራት እና ገዳማት የሚሰጡ የኢትዮጵያን ትምሀርቶችን በሚገባ ተምሬአለሁ። በለተይ በቅኔ፣ በግስ ርባታ እና ሰዋሰው ችሎታዬ በመምህራኔ እና የትምሀርት ባልንጀሮቼ ስሜ የተጠራ ነበር። በዚህም ምክንያት በጎጃም በይስማ ደጀን በመሪጌታ መንክር ዘንድ ቅኔ አስነጋሪ ነበርኩ። ተማሪ ሳለሁና ትምሀርቴንም ካጠናቀቅኩ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተዘዋወርኩ አያሌ ገዳማትን እና አድባራትን እየጎበኘሁ በውስጣቸው የአሉትን ምስጢራዊና ጥንታዊ መጻሕፍቶቻችንን ለመመርመር እድል አግኝቻለሁ።

የ18 ዓመት ልጅ ሁኜ ወደ ኑበያ (ሱዳን) ተጉዤ በነበረበት ወቅት በአንድ በፈራረሰ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቤተክተርሰትያን ቅጥር ግቢ በተቀበረ የድንጋይ ሳጥን ውስጥ፤ ምናልባት ኢትዮጵያ ውስጥ የሌሉ የኢትዮጵያን ታሪክ ጨምሮ ስለተለያዩ ጉዳይዎች የሚዘረዝሩ በግዕዝ የተጻፉ የብራና መጻሕፍትና ጥቅሎች አገኘሁ። ይህ የሆነው የዛሬ 50 ዐመት አካባቢ ነበር። እነዛን መጻሕፍት ይዤ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ ከነሱ ውስጥ አውጣጥቼ አሳጥሬና መጥኜ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ በሚል ርዕስ እንድ መጽሐፍ ጽፌ ለማሳተም ሞክሬ ነበር። ሆኖም ዶክተር ኃይሉ ወልደአብ የሚባሉ ሀቀኛ ምሁር ብራናዎቹን መርምረው፣ ይህ አንተ የጻፍከው መጽሐፍ እውነተኛው ታሪካችን በመሆኑ እስከዛሬ የተጻፉትን ስለሚቃረን ችግር ይደርስብሃል፤ ስለዚህ አቆየው፣ ብለው መከሩኝ። እኔም ቀና ምከራቸውን ሰምቼ የደርግንም የሽብር ዘመን አሳልፌ፣ መጽሐፉን በሚስጥር አቆይቼው ኖሬ፤ የዛሬ 24 ዓመት አካባቢ በድፍረት አሳተምኩት። ከዛ በኋላ በብርቅዬዎቹ ብራናዎች ላይ ተመርኩዤ አያሌ መጻሕፍትን እያከታተልኩ አወጣሁ። በወቅቱ በደረሰኝ መረጃ መሰረት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የእኔን መጻሕፍት ከማንበብ አልፈው ከነሱ ውስጥ እየጠቀሱ በአደባባይ ተጠቅመውባቸዋል። ዘግይተውም ብራናዎቹን እጃቸው ለመክተት የሁለታችንም ወዳጅ የሆነውን ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ የሚሠራውን አቶ ፈንታሁን ጥሩነህን እና ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን አማላጅ ልከው እባክህ ብራናዎቹን ልመርምራቸው፣ አሉኝ።

እኔ ግን ከዚህ በፊት ሌሎች ምሁራን ነን የሚሉ ሰዎች እንደዚሁ ብራናዎቹን አሳየን ብለውኝ ባሳያቸው ሊወስዱብኝ ሞክረው ስለነበር ከስህተቴ ተምሬ ብራናዎቹን ለፕሮፌስር ጌታቸው ኃይሌ ለመስጠት አልፈቀድኩም። ደግሞም ንብረቶቹ የኔ የግሌ ስለሆኑ የራሱን ንብረት ለደቂቃስ ቢሆን ያለዋስትና ማን ለማን ይሰጣል? ከዚህም በተጨማሪ ታሪከ-ነክ እና ባህረሃሳብን ጨምሮ ፕሮፌሰሩ የጻፉአቸውን መጻሕፍት ሳነብ ምንም የታሪከ አውቅት የሌላቸውና የግዕዝ ችሎታቸውም ደረጃ በጣም ዝቅ ያለ ሆኖ ስለአገኘሁት፤ በባህረሃሳባቸውም ውስጥ ከባድ ስህተት ፈጽመው ስለዐየሁአቸው የእኔን የግዕዝ ብራናዎች፣ ያውም በጥንታዊ ግዕዝ የተከተቡትን ተረድተው ለመፍረድ በጣም እንደሚያስቸግራቸው ተከሰተልኝ። ከዚህም በላይ፣ እኚህ ግለሰብ ሊቃውንት አባቶቻችንን ኢትዮጵያውያንን ስለሚንቁና አረቦችን፣ ግሪኮችንና አውሮጵያውያንን እያወደሱ “አባቶቻችን” ስለሚሉ፤ ለኢትዮጵያውያን የአላቸው ፍቅር እና ከበሬታ አጠራጣሪ ሆነብኝ። በመጨረሻም፣ ሰውየውን ስለማላምናቸው በቀላሉ የማይገኝ ንብረቴን ከእጄ ማውጣት ጨነቀኝ። የማላምናቸውም፣ የገቡበትን ሁሉ ድርጅት አፍርሰው የሚወጡ ናቸው፣ ሲሉ ስለሰማሁና የኑሮ መተዳደሪያቸውም ፈረንጆች በርካሽ ገዝተውም ሆነ ሰርቀው ያከማቹአቸውን የኢትዮጵያ ብራናዎችንና ቅርሶችን መመዝገብና ማቀናጀት ነው ስለተባለ ነው። ይህ በመባሉም እኔ ያገኘሁአቸውን ለትውልድ ላስተላልፍ ያቀድኩአቸውን ብርቅዬ ጥንታዊ ብራናዎች ለእኚህ ሰው ይመርምሩ ብዬ ሰጥቻቸው የደለበ ደሞዝ ለሚከፍሉአቸው ፈረንጆች እሳቸው ቢዳርጉአቸውና እነዛ ፈረንጆች በውድ ዋጋ ቢሸጡአቸው ወይም ብራናዎቹ በሚመሰክሩት የኢትዮጵያ ታላቅነት ፈረንጆቹ ቀንተው ቢያጠፉት፤ አለዛም ለኢትዮጵያ ጠላቶች አሳልፈው ቢሰጡአቸው የማን ያለህ ልል ነው፣ በሚል ስጋት ስለተጨነኩም ነበር።

እንግዲህ እላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ብራናዎቹን ስለከለከልኩአቸው ፕሮፌሰሩ ተናደው አማን በላይ ምንም ብራናዎች የለውም፤ ይህን ሁሉ መጽሐፍ የሚጽፈው ከልቡ እያፈለቀ ነው፣ እውነት ለማስመሰልም ከኢትዮጵያ ታሪክ ያጣቅሳል፤ ብለው በሃስትና በድፍረት ውሸታምና አጭበርባሪ አድርገውኝ ስሜን አጥፍተዋል። እሳቸው በኔ ላይ ላደረሱብኝ የስም ማጥፋት እግዚአብሔር ይበቀልልኛል። ካህኑ የእግዚአብሔር አገልጋይ አባቴ መምህር በላይም ሆነ በየደብሮቹና ገዳማቱ የነበሩት ቅዱሳን መምህሮቼ ከቶውንም ውሸት እንዳልናገርና ለእውነት ብቻ እንድቆም በግበረገብነት እያነጹ አሳድገውኛል። ስለዚህ ልብወለድ ጽፌ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው ብዬ አላቀርብም። የጻፍአኩቸው ሁሉ መጻሕፍት እውነተኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ናቸው። በእኔ ዘንድ የሚገኙትን ብራናዎች ግን ለደህንነታቸው አስተማማኝ ጊዜ ሲደርስ የኢትዮጵያና የዓለም ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም ሀቀኛ የአገራችንና ዓለምአቀፍ ምሁራን በተገኙበት ሸንጎ ላይ ለባህል ሚኒስቴር፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወይም ለቤተመጻሕፍት ወ መዘክር አስረክባለሁ። ታዲያን በዛን ጊዜ ዋሾው እኔ ልሁን ፕሮፌሰር ጌታቸው ይለያል። እግረመንገዴን ግን አንድ ነገር መግለጽ እሻለሁ። ከኑብያ ካገኘሁአቸው መጻሕፍት ውስጥ ታሪከ-ነገሥት ዘ ኢትዮጵያን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኬኔዲ ቤተመጻሕፍት እና የሱባንና የግዕዝ መዝገበቃላትን ለቤተመጻሕፍት ወ መዘክር አንዳንድ ቅጂዎች አበርክቻለሁ። ዳሩ ግን ይህን ቁምነገር ብዬ በአዋጅ አላስነገርኩም። የብራናዎቹን ቅጂዎች በመስጠቴ ቤተመጻሕፍት ወ መዘክር መቀበሉን የሚያንጸባርቅ የምስክር ወረቀት ሲሰጠኝ፣ የኬነዲ ቤተመጻሕፍት ግን አመሰግናለሁ እንኩዋን አላለኝም።

የእኔ ሳያንስ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ውሸታም የአደረጉትና በአደባባይ የዘለፉት አገሩን ኢትዮጵያን የሚወደውን፣ በጎሠኝነት ጎራ ፍጹም ተሰልፎ የማያውቀውን፣ በሰብዕናው ልዕልና እና በምሁርነቱ ርቀት እጅግ የማከብረውን ወዳጄን ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን ጭምር ነው። ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳም ልብወለድ ወይም (ሚት) አልጻፈም። ከኔ መጻሕፍት በተጨማሪ 42 የተለያዩ የታሪክ ዋቢ መጻሕፍት ላይ ተንተርሶ ነው፤ ከዚህ በፊት እኔም ሆንኩ ሌሎች ባለታሪኮች ያልደረሱትንና ያልደረሱበትን የአገራችንን አደገኛ ውጥረት የሚያረግብ መጽሐፍ የጻፈው። ስለዚህ የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ የተሰኘው መጽሐፉ የርሱ የራሱ፣ ላቡን አንጠፍጥፎ፣ እውቀቱን ጨምቆ፣ የጻፈው የታሪክ መጽሐፉ ነው። ይህም እጅግ የሚያስመሰግነው ድንቅ ሥራው ከዚህ ቀደም ያልነበረ ወሪጅናል እንደሆነ በዚህ አጋጣሚ ላረጋግጥ እወዳለሁ።

በመጨረሻ ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ አማን በላይ ምንም ከሱዳን የተገኘ መጽሐፍ የለውም፣ ከልቦናው አንቅቶ ነው የሚጽፈው ስለአልከው፤ ከዚህ ቀደም ለፕሮፌሰር ፍቅሬ በፍላሽ ድራይቭ ሰጥቼው ከነበረው ኑብያ ውስጥ ካገኘሁት ጥንታዊ የብራና መጽሐፍ ላይ ጥቂት ገጾች ለናሙና እንዲያሳይ ስለፈቀድኩለት ከኮምፒተሩ ላይ ያለችግር ከታተመለት ለአንባብያን ያቀርበዋል። በኑብያ ካገኘሁአቸው መጻሕፍት መሃል በቅርብ የተገኘው ይህ ብቻ ስለሆነ ነው ለጊዜው ይህን ለሕዝብ አቅርብ ያልኩት። ሌላው ጊዜና ቦታው ሲፈቅድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይቀርባል።

ፕሮፌሰር ጌታቸው አዳምጥ፣ እኔና የግዕዝ ሊቃውንት በተለያዩ ጊዜያት የግዕዝ ችሎታህን እንደገመገምነው በጣም ደካማ ነው። ከልምምድ ብዛት ያካበትከው እንጂ በቅጡ የተማርከው አይደለም። ግዕዝ ለማያውቁ ሰዎች ግዕዝ የምትችል መስለህ ትታያቸው ይሆናል። ባህረሃሳብ ባልከው መጽሐፍ ውስጥ እንኩዋን ግዙፍ ግዕዛዊና ቀመራዊ ስህተቶች ሠርተሃል። የአንተን ባህረሃሳብ ምንነት፣ ምንጭና ስህትት አስመልክቶ የጻፍኩት ራሱን የቻለ መጽሐፍ ስለማወጣ ነቀተህ ተጠባበቅ። አሁን ለጊዜው ግን፣ በርካታ ብራናውን ተወውና እስቲ እነዚህን ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለናሙና ያቀረባቸውን የግዕዝ ገጾች ወደ አማርኛ ተርጉመህ ችሎታህን አሳየን። ከዛ በኋላ ስለ ሌሎቹ መጻሕፍት እንነጋገራለን። በመጨረሻም፣ መሪራስ አማን በላይን እኔ ወደ እኔ ና ብዬው ሳይመጣ ቀረ ስለአልከኝ፤ ከኔ አንድ ነገር ለማግኘት የፈለግከው አንተ ስለሆንክ ወደ እኔ መምጣት የነበረብህ አንተ ነህ። አንተ ትፈልገኛለህ እንጂ ለእኔ አታስፈልገኝምና። ለጊዜው በእዚሁ ልሰናበትህ።

መሪራስ አማን በላይ፣
ጸሀፌ-ታሪክ
እ.ኤ.አ. ታህሳስ 21 ቀን 2016

ውድ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ከዚህ በታች የሰፈረው ደሞ እኔ ፍቅሬ ቶሎሳ ለእርስዎ የጻፍኩት ነው።

የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ በሚል ርዕስ የከተብኩትን የታሪክ መጽሐፌን አፈታሪከ ነው፣ ብለው እርስዎ ለእርስዎ ድክመቶች የመሰለዎትን ነጥቦች ብቻ እየነቀሱ እና እየቆነጸሉ በማውጣት አስፍረዋል። ይህ የጻፉት ነገር ወይ ምሁራዊ ግምገማ አይደል፣ ወይ ትንተና አይባል፣ ወይ የመጽሐፍ ማስተዋወቂያ ተብሎ አይፈረጅ፣ እንዳው መላ ቅጡ የጠፋው በቂም በቀል መጽሐፉን ለማጠልሸት የተወረወረ ድንጋይ ነው። አርዕስቱ ራሱ አንባቢን የሚያታልል ነው፤ “የፕሮፌሰር ፍቅሬ አስተዋጽኦ” ይላል። አንባቢው ወደ ውስጥ ሲገባ ግን አርዕስቱ አንባቢን የመሳቢያ ወጥመድ እንደሆነ እና ይዘቱ ሸረኛ እንደሆነ ይረዳል። እኔ ለጽሁፌ ማስደገፊያ 47 መጻሕፍትን አስፍሬአለሁ። ከእነሱ ውስጥ የመሪራስ አማን በላይ 5 ብቻ ናቸው። እርስዎ ግን የሳቸውን ብቻ የጠቀሰኩ አስመስለው ትችቶን ሆነ ብለው በሳቸው ሥራዎች ላይ ብቻ አቀረቡ።

የእሳቸውንም መጻሕፍት ቢሆን እኔ ሳልመረምር በዓይን ጭፍን አልተጠቀምኩባቸውም። በሚገባ መርምሬአቸው ከህሊናዬ ተሙዋጉቼ ሳበቃ እነሱን በሌሎቹ መጻሕፍት አመሳክሬ፣ አንጥሬና አበጥሬ አሳማኝ መደምደሚ ላይ ደርሼ ነው። ሰውዬው ሊቅ ስለሆኑ የኢትዮጵያን ታሪክ ከታች እስከላይ፣ ከቀንዱ እስከ ጭራው፣ ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው። ይህም እውቀታቸው ጠሊቅ ሊሆን የበቃው እና በርካታ የታሪክና የጥበብ መጻሕፍትን ሊደርሱ የቻሉት፣ ከህጻንነታቸው ጀምሮ ዕድሜልካቸውን በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች፣ ደብሮችና እና ገዳማት እየዞሩ አዕምሮአቸውን ስለ አነጹት ነው። በዛ ላይ በጀበል ኑባ፣ ኑብያ ያገኙአቸው ብርቅዬ ብራናዎች ተደምረው ልሂቅ ባለታሪክ ለመሆን በቅተዋል። እንጂ እርስዎ አለአግባብ ጨዋነት በጎደለው መልኩ እንደሚዘልፉአቸው የአፈታሪክ ጸሐፊ አይደሉም። በእውነቱ እርስዎ ክብርን እጅግ የሚሹ ሰው ሆነው ሳሉ ሌሎች ትልልቅ ሰዎችን በድፍረት ለመዘርጠጥ የማያፈገፍጉ ሰው ነዎት። እርስዎ እንደሚሉት መሪራስ አማን በላይ የከተብዋቸው ከዐስር በላይ ብርቅዬ መጻሕፍት የአፈታሪክ ወይም የልብ ወለድ ከሆኑ በክህሎታቸው ከነ ሆመር፣ ከነ ዳንቴ፣ ከነሼክስፒር እና ቶልስቶይ ይበልጣሉ ማለት ነው። ስለዚህም አንድ ሳይሆን ሁለት የስነጽሁፍ ኖቤል ፕራይዝ ሽልማቶች ይገባቸዋል። እኚህ ሰው እጃቸው ውስጥ የከበሩ ጥንታዊ ብራናዎች እንደ አሉ ርስዎም ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለዚህም ማስረጃው የራስዎ ምስክርነት ነው። በአንድ ወገን መሪራስ አማን በላይ ከሱዳን አገር ያገኘው ምንም ብራና የለም፣ ፈጥሮ ነው የሚደርሰው ይላሉ። እሳቸው መጽሐፍ ሲያሳትሙ ግን ርስዎ ተሽቀዳድመው መጻሕፍታቸውን በእጅዎ ይከታሉ። ስለ እኔም መጽሐፍ “ልብወለድነት” ርስዎ በጫጫሩት ላይ ከፍ ብለው አማን በላይ ከሱዳን አገር ያገኘው ምንም ነገር ስለሌለው ነው እንጂ፤ ቢኖረው ኖሮ እኔ የማውቃቸው ፈረንጆች መርምረውት ምንነቱን ባረጋገጡት ነበር፣ ይላሉ። እንዳው ለነገሩ ብራናውን ሳያዩ ፈረንጆቹ እንዴት ይመረምሩታል? ቀድሞ ዐጠገቡ መች ደረሱ? ፈረንጆቹ ስለአልበሉት ምግብ ጣዕም እንዴት ይመሰክራሉ? ደሞስ ለፈረንጅ ምስክርነት ማን ግድ አለው? ርስዎ እንጂ እኔና መሪራስ አማን በላይ ለፈረንጅ ምስከርነት ግድ የለንም። ታሪካችንን እኛ ለፈረንጅ እናስተምረዋለን እንጂ ፈረንጅ አያስተምረንም። በዛው በኔው ትችት ላይ ዝቅ ብለው ደግሞ መሪራስ አማን በላይን አንተ ያገኘከውን ታሪከ ነገሥት ለታሪክ መርማሪዎች አሳይ፣ ብለው ይመክሩአቸዋል። ማስረጃው የርስዎ የራስዎ ቃል እነሆ። እጠቅሶታለሁ-

"በመጨረሻ፥ ለመሪራስ አማን በላይ አንድ ጥያቄ ላቅርብ፤ አንዳንድ የታሪከ ነገሥት ቅጂዎች ተገኝተው ታትመዋል፤ የታተሙት ሁሉ የየራሳቸውን አዳዲስ ነገሮች አስተምረውናል። አንተም ያገኘኸው ታሪከ ነገሥት በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን የተቀዳ ስለሆነ፥ አንዳንድ ቅጅ ለአዲስ አበባ ወይም ለደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ልትሰጥ ትችላለህ። መሪራስ ሆይ፤ በጎውን ይምራህ።"

እላይ የሰፈረው የርስዎ ቃል ነው። ባንድ ወገን አማን በላይም አንተም የጻፋችሁት ልብወለድ ወይም አፈታሪክ (ሚት) ነው፣ አማን ምንም የብራና መጻሕፍት የለውም እያሉ፣ መልሰው ደግሞ “አንተም ያገኘኸው ታሪከ ነገሥት በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን የተቀዳ ስለሆነ፥ አንዳንድ ቅጅ ለአዲስ አበባ ወይም ለደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ልትሰጥ ትችላለህ። መሪራስ ሆይ፤ በጎውን ይምራህ።" ይላሉ። እራስዎን በራስዎም ይቃረናሉ።

እጃቸው ውስጥ ብራና ከሌለ ምኑን ነው የሚያስመረምሩት? ስለዚህ እኚህ ሰው ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት እንዳገኙ ርስዎ ያውቃሉ ማለት ነው። ካልሆነም ያምናሉ። ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ፣ መሪራስ አማን ምንም አላገኘም፣ እሱ እና አንተ አፈታሪከ ነው የደረሳችሁት ብለው በላያችን ላይ ለምን ሃሰት ይነዛሉ? ርስዎን ከሚያህል ዕድሜ ከጠገበ ሰው ይህን የመሰለ ደባ ይጠበቃልን? እግዚአብሔር ፊት ቀርበው በምድር ላይ ሆነው ስተለተናገሩትና ስለሠሩት ሁሉ በእግዚአብሔር የሚጠየቁበት ጊዜ እንደቀረበ አያውቁምን? እውነተኛው የኢትዮጵያ ታሪክ አሁን በኔ መጽሐፍ ውስጥ ተንጸባርቆ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይ አማራውና አሮሞው ለመግባባትና ለመታረቅ በሚሞከርበት ወቅት በሁለቱም ሆነ በሌሎቹ ሕዝቦቻችን መሀል ደም መፍሰስ እንዲቆም ይህ መጽሐፌ በሚረዳበት ሰዓት፣ እርሰዎ በሃቅ ላይ ያልተመሰረተ በግል ቂምዎ ላይ የቆመ አፍራሽ ሃሳብ መሰንዘርዎ አሳዝኖኛል። ሌሎችም በርካታ ሰዎች በርስዎ ተንኮላዊ ድርጊት ማዘናችውን ገልጸውልኛል። ምሁርነት እንደዚህ ነውን? የመሪራስ ብራናዎች ጉዳይ ርስዎን ለምን እንደሚያብከነክኖትና እንደሚያበግኖት ምስጢሩን ለማያውቀው አንባቢ አሁን አብራራዋለሁ።

በውነትም መሪራስ አማን በላይ ከኑበያ፣ ሱዳን የአገኙአቸው ብራናዎች እንዳላቸው እላይ በተቀመጠው ንግግሮ ራስዎ አረጋግጠዋል። እኔም ከዚህ በታች በማስፍረው እሳቸው ከዛው ከኑብያ ከአገኙአቸው ጽሁፎች መካከል አንዱ በሆነው ጥቂት ገጾች አረጋግጣለሁ። ይህ ጥንታዊ መጽሐፍ ገጹ 333 ቢሆንም በፍላሽ ድራይቭ ከተጫነው ኮምፒተር ላይ ለማውረድ ስላልተመቸኝ ለጊዜው እታች የሰፈሩትን ኮምፒተሩ የፈቀደልኝን ቅጠሎች ብቻ ለአንባብያን አስቀምጫለሁ። ለኔ በገባኝ አነስተኛ የግዕዝ ችሎታዬ እንደምረዳውና መሪራስ አማን መጽሐፉን በሰጡኝ ጊዜ የነገሩኝን እንደማስታውሰው፣ መጽሐፉ የሚዘግበው ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርሰቶስ ከሙታን መሃል ተለይቶ ከተነሳ በኋላ በነበሩት 40 ቀናት ለደቀመዛሙርቱ፣ በተለይም ለማቴዎስ፣ ለማርቆስ፣ ለዮሃንሰ ወልደዘብዴዎስ፣ ለቶማስ እና በኋላም ለሉቃስ ስለ ቤተክርሰትያን አስተዳዳሪዎች ሥርዓት የአስተማራቸውን የሚያትት ነው። በተለይ ኤጲስቆጶሳትና ጳጳሳት ከፈለጉ ሚስት ማግባት መቻላቸውን እየሱስ ክርስቶስ ይፈቅዳል። ይህ መጽሐፍ፣ ንስጥሮስ ምንኩስናን ከማስተዋወቁ በፊት ይህ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ይመሰክራል። እየሱስ ክርስቶስ እነዚህን የቤተክርስትያን ሹማምንት ማግባት ከፈቀደላቸው ታዲያ ለምንድነው የማያገቡት? መነኮሳት ንስጥሮስን ነው የሚከተሉት ወይንስ እየሱስን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። መጽሐፉ አነጋጋሪ ስለሆነ ይመስለኛል መሪራስ አማን ሊያሳትሙት ያልቸኮሉት። ለማንኛውም ቅጠሎቹ እነሆ። በቀላሉ ከኮምፒተሩ ላወርድ የቻልኩትን ብቻ ስለሆነ ያቀረብኩት ቅደም ተከተሉ ተዘበራርቆአል። ቅጠሎቹ በተለያዩ ጊዜያትና ብዕሮች የተከተቡ ሳይሆኑ አይቀሩም። ቁምነገሩ የመጽሐፉ ይዘት ሳይሆን መሪራስ አማን በላይ ኑብያ ውስጥ ያገኙት ልዩና ብርቅዬ የብራና መጻሕፍት እንደ አላቸው ማሳየቱ ነው። እታች የሚሰፍሩት ገጾች ኮፒራይት የመሪራስ አማን በላይ ብቻ ነው።

Geez book

Geez book

Geez book

Geez book

ፕሮፌሰር ጌታቸው ሆይ!

እስከከዛሬ ድረስ ስለ አኢትዮጵያውያን ማንነት፣ ስለ ንግሥተ-ሳባና በጠቅላላው ስለኢትጵያ ታሪክ እርስዎ የሚያሰራጭዋቸውን ስህተቶች በሚመለከት ዕድሜዎን በማገናዘብ እና ርስዎን በማክበር በአደባባይ ስምዎን ጠርቼ ተናግሬ አላውቅም። እንደ አላየ ዓይቼ አልፎት ነበር። አሁን ግን ራስዎ ነገር ፍለጋ ወደ እኔ ስለመጡ የርስዎን ችግር ለማጋለጥ እገደዳለሁ። ችግርዎ ራስዎን ከማንም በላይ አዋቂ ማድረግ እና በእኔ እጅ ውስጥ ያላለፈ እና በኔ ያልተባረከ የብራና፣ የቤተክርስትያን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጉዳይ ዋጋ የለውም፣ አፈታሪክ ነው፣ ማለትዎ ነው። ቸሩ እግዚአብሔር ግን ለሁሉም ሰው አዕምሮ ለግሶአል። ስለዚህ ሁሉም ሰው በየደረጃው ነገሮችን የመርመር አቅም አለው። የሰው ልጅ ሁሉ አይናቅም። እውቀትን ደግሞ ማንም በሞኖፖሊ አልያዛትም።

ትዝ እንደሚልዎት፣ የዛሬ 6 ወይም 7 ዓመት አካባቢ ዋሺንግተን ዲሲ ስብሰባ ላይ ተገናኝተን መሪራስን ለማገዝ ስል የሳቸውን መጽሐፈ ዐብሪህትን እና ሌሎችንም መጻሕፍቶቻቸውን ሸጨልዎት ሳለ በመሪራስ እጅ ውስጥ የሚገኙትን ብራናዎች እየመረመሩ ወደ እንግሊዝኛ ተርጉመው ለዓለም ሕዝብ እንዲገልጹ መሪራስ አማን በላይ ፍቃደኛ መሆናቸውን ልጠይቅልዎት ወይ ብዬዎት፤ ርስዎም ይህን ቢሆን እንደሚደሰቱ አረጋግጠውልኝ ነበር። ይህን ሃሳብ ራሴው ያቀረብኩልዎት በነዚህ አስደናቂ ብራናዎች ምክንያት አገራችን እንድትከበር በጎውን አስቤ ነበር። ወደ ካሊፎርኒያ እንደተመለሰኩ እኔም ይህን ሃሳብ ለመሪራስ አማን አካፈልኩአቸው። እሳቸውም ሃሳቡ ቸር ነው፣ ፕሮፌሰር ጌታቸውን ግን በደንብ አላውቃቸውም። ከዚህ በፊት ሌሎች ምሁራን ልክ እንደሳቸው ብለውኝ እውነት መስሎኝ ብራናዎቹን ከአሳየሁአቸው በኋላ እኔን በማግለል ብራናዎቹን ሊወስዱብኝ ስለሞከሩ መጠንቀቅ አለብኝ፣ ስለ አሉ ነገሩ ሳይሳካ ቀረ። ከዛም ርስዎ አቶ ፈንታሁን ጥሩነህን (ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ የሚሠራውንና መሪራስ ብራናዎቹ እንዳላቸው አምኖ አንዳንዶቹን የመሪራስን መጻሕፍት ለህትመት የአረመው) ወደ መሪራስ አማላጅ ልከው ብራናዎቹን ለመመርመር ቢሞክሩም አልተሳካልዎት። ስለዚህ ተበሳጭተው ቂም ይዘው አማን ውሸቱን ነው፣ በእጁ ምንም ብራና የለም፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ብሎ የሚጽፈው ሁሉ ልብ-ወለድ ነው፤ እያሉ ርስዎ ማውራት ጀመሩ። ንግግርዎ የብስጭት እና የእልህ ነው። ርስዎ የፈለጉት ተሳክቶሎዎት ቢሆን ኖሮ የኔንም ሆነ የመሪራስን ሥራ ዛሬ አፈታሪከ ነው ባላሉም ነበር። ለደንታዎ ሲሉ እውነተኛ ታሪክ ነው እያሉ ምስራቹን በነዙት ነበር።

እንዳው ለነገሩ፣ እንድ ጥያቄ ላቅርብልዎትና በዛን ጊዜ ርስዎ ራስዎ የመሪራስን መጻሕፍት የኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ የተባለውን ጨምሮ ገዝተው አንብበው ከውስጣቸው ጥቅሶች ነቀሰው አውጥተው በአደባባይና በጽሁፍ አልተጠቀሙባቸውም? ሃቁ ለምን ብራናዎቹ እጄ አልገቡም ብለው ተቆጭተው አይደል መጻሕፍቱን ተረት የሚሉት? ዳሩ ግን፣ ተረት ከማለት በቀር ተረት ስለመሆናቸው አንድም እንኩዋን ማስረጃ አላቀረቡም። በሌላው እንኩዋን ቢቀር በዕድሜዎ ትልቅ ሰው አይደሉም እንዴ? አገራችን ላይ እሳት እየነደደ እና ኢትዮጵያችን ልትበጣጠስ እያሰጋት ባለችበት ወቅት ለችግራችን መፍትኄ የሚሰጥ እውነተኛ ታሪካችን ሲወጣ እሰየው እንደማለት በግል ኢጎዎ ተነሳስተው እንዴት እንዲህ ያደርጋሉ? ነውር አይደለም እንዴ? ተሳስቼም ከሆነና እውነት ከልብዎ ቀና ካሰቡ ድካሜን እና ጥረቴን አደባባይ ወጥተው ከማጠልሸት ለምን ለእኔ ስልክ ደውለው አላናገሩኝም?

እኔ በመጽሐፌ ውስጥ በርካታ ቁምነገሮችን አንስቼ ሳለ ርስዎ ስለነዚህ ቁምነገሮች ምነው ትንፍሽም አላሉ? ከዚህ በፊት ያልተባሉ እንዳንድ የቆዩ የታሪክ እሳቤዎችንና ግንዛቤዎችን እኔ ውድቅ አላደረግኩምን? ለምሳሌ እንግሊዛዊው ኡሉንዶርፍ ኦሮሞዎች ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ምንም አላበረከቱም ብሎ ሲዘባርቅ፤ እኔ ኦሮሞዎች ያበረከቱትን ሁሉ ዘርዝሬ በማስረጃ አላቀረብኩምን? ታዲያ ስለ እሱ ምነው ጸጥ አሉ? አማራ የገዢ መደብ ተብሎ በሃሰት ተፈርጆ እየተዋከበና እየተገደለ ሲኖር፤ አማራው እንደ ስርወ-መንግሠት የገዢ መደብ ሆኖ ገዝቶ እንደማያውቅ አዲስ ማስረጃ ኮልኩሌ አማራው የገዢ መደብ እየተባለ ግፍ የሚፈጸምበት አግባብ እንዳልሆነ ስለ እሚመሰክረው አዲሱ ግኝቴ ምነው ዝም አሉ? ከዚህ የላቀስ የቀድሞውን እሳቤ ፉርሽ የሚያደርግ ምን አለ? ስለጎሣ፣ ስለ ነገድ፣ ስለዘር እና ስለ ብሔር ልዩነቶች ከዚህ በፊት ያልተባለውን እኔ አዲስ ትንታኔ አቅርቤ ስለዚህ እንዳይናገሩ ምላስዎ ለምን ተያዘች? ኦሮሞዎች በላቲን ከሚጽፉ ይልቅ በኢትዮጵያ ፊደላት ቢከትቡ ብዙ ጥቅም እንደ አለው በማስረጃ ስለ ጠቆምኩትስ ምነው አንድም ቃል አልተናገሩ?

ከዚህ ሁሉ በላይ፣ ንግሥተ-ሳባን አረብ ነች ወይም ቢልቂስ የምትባል የአረብ ንግሥት ነች እያላችሁ እርስዎና መሰልዎችዎ መሳሳታችሁን በዘርዋ ሃረግ እና በተዘዋዋሪ የአመክንዮ ማስረጃዎች ቆልዬ በ53 ገጾች ስለመዘገብኩት አዲስ ክስተት ምነው አድናቆትዎን አልገለጹም? አንድ እውነተኛ ምሁር ይህን የቀድሞውን ግንዛቤ ማድነቁ እንኩዋን ቢቀር አንባቢን ለውይይት አይጋብዝምን? ርስዎ ግን አንባቢውን በመናቅ ቅጥፈት ያሰራጫሉ። የዛሬ ዘመን አንባቢ ግን የረቀቀ ስለሆነ የኔ መጽሐፍ እውነተኛ የአገራችንን ታሪከ እንደሚያንጸባረቅ ማስረጃዎቼን አመዛዝኖ ያለነጋሪ ይገነዘባል። ባለፉት 4500 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰቱት ስርወ-መንግሥታት የኩሽ፣ የኢትዮጵ፣ የሰለሞን፣ እና የዛጉዌ ብቻ እንደሆኑ እኔ በማስረጃ አቅርቤአለሁ። የትግሬም ሆነ የኦሮሞ ወይም የአማራ ስርወ-መንግሥት እንዳልነበረ፣ የኦሮሞ ዝርያዎች ግን በወንድሞቻቸው በአማራዎች የጦር ሠራዊት እርዳታ ከኦሮሞዋ ከሃዊ ጊፍቲ መንዲያ ልጅ ከተስፋኢየሱስ (ይኩኖዐምላክ) ጀምሮ በጋብቻ እሰለሞን ስርወ-መንሥት ውስጥ “ሰርገው ገብተው”፣ እስከ አጼ ኃይለሥላሤ ድረስ በንጉሠነገሥትነት እና በንግሥተነገሥታትነት ኢትጵያን እንደመሩ፣ በዘመነ መሳፍንትም ደሞ ከትንሹ እስከ ትልቁ ራስ አሊ ኢትዮጵያን እንደገዙ በአዲስ ማስረጃ አስደግፌ አቅርቤአለሁ። ይህም አዲስ ትንተና መሪራስ አማን በላይን ከመተዋወቄ እና መጻሕፍታቸውን ከማንበቤ በፊት ባለፉት 27 ዓመታት Ethiopian Review በተባለው መጽሔት በጻፍኩአቸው መጣጥፎቼ ውስጥ ተንጻባርቀዋል። እነሱም ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው---

Nobles of Oromo Descent Who Ruled Ethiopia,
Oromo Contribution to Ethiopian Civilization,
Amara Contribution to Ethiopian Civilization,
Tigre Contribution to Ethiopian Civilization,
Common Factors Uniting the People of Ethiopia,
Nigusse Negest, Balemulu Siltan Enderassie, Emperor, Prime Minster.

እነዚህም ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ኢትዮጵያውያን ያነበቡዋቸው መጣጥፎች እኔ ታሪካችንን ባልተለመደ መልኩ የማቅረብ ክህሎት እንደ አለኝና አያሌ ሙሁር-ተብዬ ሁሉ በታሪክ ውዥንብር ውስጥ ተዘፍቆ፣ እናት ኢትዮጵያን ክዶ በየጎሣው ሲወሸቅ እኔ የማያወላዳና ቀጥ ብሎ የወጣ የኢትዮጵያዊነት አቁዋም እንደነበረኝ ይመሰክራሉ። ለታሪክም ጸሃፊነት እኔ አዲስ እንዳልሆንኩ እማኝ ይሆናሉ። ቀደም ሲል እንደ ገለጽኩት፣ ርስዎ ራስዎ እላይ በተጠቀሱት እና በሌሎቹም መጣጥፎቼ የተነሳ አድኖቆትዎን በወቅቱ እንደቸሩኝ ዛሬ አሌ አይሉም።

ውድ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣

ሌላው የርስዎ ችግር ኢትዮጵያውያንን መናቅና ማጣጥል አረቦችን፣ ግሪኮችን እና ሌሎች ነጮችን ማምለክ ነው። ንግግርዎችዎ እና ጽሁፍዎችዎ ሁሉ ሲፈተሹ ይህን እውነት ይፈነጥቃሉ። ለምሳሌ ንግሥተ-ሳባ የኢትዮጵያ ንግሥት መሆንዋን አንኩዋር አንኩዋር አዳዲስ ማስረጃዎች (በ53 ገጾች) በመጽሐፌ ውስጥ አቅርቤልዎት ማስረጃዎቹ ዓይኖችዎ ላይ እያፈጠጡ የርስዎን የተሳሳተ ድምዳሜ ስለ አፈረስኩብዎት፤ ርስዎ ሳባን ስምዋን ቀይረው “ቢልቂስ” ብለው፣ በሃሰት ሳባ የኛ ቢልቂስ ናት ለሚልዋት ለአረቦች ይሸልሙዋታል። ደሞም ባሕረሃሳብ ብለው ባቀነባበሩት መጽሐፍዎ በገጽ 67 ላይ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌሎቹ ክርስትያኖች ተለይተን የእየሱስ ክርስቶስን ልደት በ7 ዓመት ወደ ሁዋላ ቀርተን ለምን እንደምናከብር እየጠየቁ፤ እየሱስ ክርስቶስን በ7 ዓመት ወጣት ልናደርገው ነውን በማለት ያወቁ የበለጡ መስሎዎት በራሳችን ላይ እያሾፉና እየተሳለቁ፤ ይህን ያደረግነው እኛ ኢትዮጵያውያን ቀን አቆጣጠርን ባለማወቃችን እንደሆነ አድርገው ይዛለፋሉ። ርስዎ ስለራስዎ እንደሚመሰክሩት እውነት የታሪከ አጥኚ ቢሆኑ ኖሮ ምክንያቱን ባወቁ ነበር።

ምክንያቱ ግን እኛ አላዋቂ፣ ፈረንጆች አዋቂ ሆነው ሳይሆን፤ ፈረንጆች የጌታችንን የእየሱስ ክርስቶስን ልደት መቁጠር የሚጀምሩት የዚያን ጊዜው የሮማን ኢምፓየር ቄሳር የነበረው አውጉስቶስ ቄሳር፣ እየሱስ ከመወለዱ ከ7 ዓመታት አስቀድሞ እንደ እግዚአብሔር ይመለክ ስለነበር የራሱ ልደት እንዲከበር ስለ አወጀ ከዛን ወቅት ጀምረው አውሮፓውያን ቀን ስለቆጠሩ እና እኛ ደግሞ ራሱ እየሱሰ ክርስቶስ ከተወለደበት ቀን አንስቶ መቁጠር ስለጀመርን ነው። ስለዚህ እኛ የህያውን የእግዚአብሔርን ልጅ ትክክለኛውን ልደት እናከብራለን እንጂ፤ የጨካኙን አረመኔ ቄሳር ልደት አንዘክርም። ስለዚህ ትክክለኛው የዘመን አቆጣጠር የኛ ርስዎ የሚያሾፉበቱ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ የዘመን አቆጣጠርን ዘዴ ርስዎ "አባቶቻችን” ከሚሉዋቸው ከግብጾች፣ ከሶሪያውያን እና ከግሪኮች እንደቀዳን እያተቱ ይሳለቁብናል። ሃቁ ግን የግብጾቹና የሌሎቹ ቤተክርስትያናት የዘመን አቆጣጠር ከኛው ጋር በምንም አይገናኝም። ካንዳቸውም ጋራ የኛው አንድነት የለውም። አይመሳሰልምም። እውነት እኛ የቀንን እና ዘመንን አቆጣጠር የቀዳነው ከነሱ ከሆነ ለምን የነሱ ከኛው ጋር ዛሬ የማይገጥም ሆነ? አሁንም ሃቁ የኛን የዘመን አቆጣጠር የኛው ሊቃውንት ፈልስፈው ያቆዩልን ነው። እነሱም በአቀማመር እና በስሌት የረቀቁ ነበሩ እንጂ፤ እርስዎ በዚሁ በባህር ሃሰብ መጽሐፍዎ እንደሚሰድቡዋቸው እና እንደሚያዋርዱአቸው ሰኞና ማክሰኞን እንኩዋን የማይለዩ መሃይማን አልነበሩም። እግረ-መንገዴን አንድ ጥያቄ ልጠይቆትና፣ እነዚያን ግብጻውያን “አባቶቼ፣ አባቶቼ” የሚሉአቸው ለርስዎ በግብጽ አገር ስኮላርሺፕ ከመስጠት በተረፈ ሊቃውንታችንን ከማስገደል፣ አንዳንዴም ስውር ሙስሊም ሆነው መስጊድን ከመገንባት የዘለለ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ምን ፈይደውልናል? አረቦች ሊያደርጉን ከማሻጠር በቀር ቅኔ አስተምረውናል ወይስ ዜማ፣ ወይስ አቁዋቁዋም ወይስ ብሉይና ሃዲስን አስጠንተውናል? ራሳቸው አማርኛ ወይም ግዕዝ አይናገሩ አይጋገሩ። አብዛኞቹ ተንቀሳቃሽ ሃውልቶች ብቻ ነበሩ። ከባድ የወርቅ ዋጋ እየተከፈላቸው ለ1500 ዓመት ያህል በኛ ሲያላግጡ ኖረው አገራችንን አፈራረስዋት። እና ርስዎ እነዚህን የእምዬ ኢትዮጵያን ጣውንቶች አባቶቻችን ይላሉ። ይሄ ፌዝ ነው። የኔ እና የመሪራስ አባቶች ግን ጠቢባኑ ኢትዮጵያውያን እንጂ አረቦችና ግሪኮች አይደሉም። የእርስዎን አባቶች ግብጻውያንን ደግሞ ፈርኦን ንጉሦችና ህንደኬ ንግሥቶች ሆነን የገዛናቸውና ያሠለጠናቸው እኛው ኢትዮጵያውያን ነን እንጂ በመንፈሳዊነትም ሆነ በቁሰ-አካል ሥልጣኔ ከኛ በታች የሆኑት ግብጻውያን እኛን አላሠለጠኑንም። በእውኑ እርስዎ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያውቁ ቢሆኑ ኖሮ ሆነ ብለው ካልካዱት በቀር ይህን በተገነዘቡት ነበር።

እኔን፣ አንተ የስነጽሁፍ ሰው እንጂ ባለታሪክ አይደለህም፣ ስለአሉት ርስዎም የቁዋንቁዋ ተመራማሪ እንጂ ከቶውንም ባለታሪክ አይደሉም። ታሪክን አስመልከቶ አባ ባህሪይ ስለ ኦሮሞ ጽፈውት ርስዎ ከግዕዝ ወደ አማርኛ በተረጎሙት የአባ ባሀርይ ድርሰቶች መጽሐፍ ላይ ተርጉዋሚ እንጂ ባለታሪክ እንዳልሆኑ አምነዋል። ታዲያ በየትኛው የታሪክ እውቀትዎ ላይ ተመርኩዘው ብቁ ሆነው ነው የእኔን እና የመሪራስ አማን በላይን የታሪክ መጻሕፍት ልብወለዶች ናቸው ለማለት የደፈሩት? እንደ እውነቱ ከሆነ የኔን እና የመሪራስን የታሪክ መጻሕፍት ለመፈረጅ ብቃት የለዎትም። እኔ ግን ምንም በታሪክ ትምህርት ዲግሪ ባይኖረኝም (በነገራችን ላይ ብዙዎች ባለታሪኮች የታሪክ ዲግሪ አልነበራቸውም። እነ ክቡራን ተክለጻድቅ መኩሪያ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ ይልማ ደሬሳ፣ አቤ ጎበኛ፣ አስረሰ የኔሰው እና ሌሎችም ለአብነት ይጠቀሳሉ።) የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ሆነ የኮሌጅ ተማሪ ሆኜ በታሪከ ትምህርት አልበለጥም ነበር። በዚሁ የታሪክ ችሎታዬ በመምህራኖቼ ተመልምዬ ገና የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ የማታ 8ኛ ክፍል የአደጉ ተማሪዎችን በእንግሊዝኛ ቁዋንቁዋ ታሪክ እያስተማርኩ ገንዘብ ይከፈለኝ ነበር። በመስኮብ አገር የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ በርካታ የዓለም ታሪክ ኮርሶችን ተከታትያለሁ። በጀርመን አገርና በአሜሪካ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የአፍሪካን ታሪክ፣ የኢትዮጵያን ጨምሮ አስተምሬአለሁ። በማስተምርም ጊዜ ራሴ እማርና እመራመር ነበር። ምን አለፋዎት ስለ እኔ የታሪክ ችሎታ ከእርስዎ ከራስዎ እና ከፕሮፌሰር መስፍን በላይ ማን እማኝ አለኝ?

የዛሬ 15 ዓመት ገደማ በሎስአንጅለስ ከተማ በአድዋ ድል በዓል ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በግንባር ስንገናኝ የአሉኝ ይታወሶታል? ኢትዮጵያን ሪቪው ገና ሲወጣ ፈጥኜ የማነበው የአንተን ጽሁፍ ነው፣ ነበር የአሉኝ። ታዲያ በዛን ወቅት እኔ በብዛት እከትብ የነበረው እንደዛሬው ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ እና የኢትዮጵያ ታሪክ ነው። አዎን በደጉ ጊዜ የእኔን የታሪክ እውቀት ራስዎ አድንቀውልኝ ነበር። ዛሬ ግን ምላስዎን አጠፉት።

በርካታ ሕብረተሰባዊ መጻሕፍትን የከተቡት፣ ለሰብዓዊ መብት የሚሙአገቱት እና በድፍረትና በግልጽነት የሚናገሩት አንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አዳፍኔ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እና በቃላቸውም ስለ እኔ የታሪክ እውቀት መስክረዋል። ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ የኢትዮጵያን ታሪከ፣ በተለይ የኦሮሞን ታሪክ ጠንቅቆ ሊጽፈ የሚችል ነው፣ ብለው ስለ እውነት መስክረዋል፤ እኔም አላሳፈርኩአቸውም። ይህን የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ የተሰኘውን ከእርስዎና ከመሰሎችዎ በቀር ድፍን አገር የወደደውን መጽሐፍ ጽፌ አኮራሁአቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ካንዴም ሁለቴ ተገናኝተን ስለመጽሐፉ ስንወያይ በፈገግታ እያዩኝ “አንዳንድ ሰዎች፣ አንተ አማራ የለም ብለሃል፣ ወዳጅህ ፍቅሬ ቶሎሳ ግን አለ ብሎ ጽፎአል፣” ከአሉኝ በኋላ “ድሮ የምናውቀውን ታሪከ ገለባብጠህ ጽፈሃል፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አብዮት አካሂደሃል፣ አንተ የጻፈከውን አዲስ ታሪክ በአዲስ መልክ እያገናዘብን ማንነታችንን እንደገና መመርመር አለብን፣” በማለት የሃቀኛ ምሁርን እውነተኛ አስተያየት ከልባቸው ገልጸዋል። ቀጣፊ እና መሰሪ ምሁር ቢሆኑ ኖሮ የኔን የቀድሞ ሃሳብ የሚያፈርስ አዲስ ሃሳብ አመጣ ብለው አፍረው እና ተናደው መጽሐፌን ባጣጣሉት ነበር። አዎን፣ ሃቀኛ ምሁር የቀድሞ እሳቤውን የሚሽር አዲስ ትክክለኛ እሳቤ ሲመጣ የኔን የድሮውን ይሽርብኛል ብሎ ከድሮው ጋር ሙጭጭ ብሎ፣ ዓይን አውጥቶ፣ ሃሰት እያዛመተ ገር አንባቢን አያሳስትም።

እርስዎ ግን ታሪክ አውቃለሁ እያሉ መሃይም እንኩዋን የማይሠራውን ታሪካዊ ስህተት ፈጽመዋል። እንዴት ማለት ደግ ስለሆነ እንዴት ይበሉ። ስለ አማራው በከተቡት አንድ መጽሔት ላይ በሸዋ የሰለሞንን ስርወ-መንግሥት ስለተከለው ስመ-መንግሥቱ ይኩኖዐምላክ፣ ወላጆቹ ያወጡለት ስም ተስፋእየሱስ ስለተባለው ንጉሥ ሲጽፉ፤ የልጁን እና የአባቱን ስሞች አምታተው ገለባብጠው መዝግበዋል። የተስፋእየሱስ አባት ስም እድምአሰግድ ነበር። እርስዎ ግን ልጁን እድምአሰግድ፣ አባቱን ተስፋእየሱስ ብለው አፋልሰው አስፍረዋል። ይህ የስህተት ስህተት ነው። የሚያሳፍርም ነው። የታሪክ አላዋቂነትዎ ተጋልጦ እንዳያፍሩ አስቤለዎት ከዚህ ቀደም በትዝብት ብቻ አልፌዎት ነበር። ይህንን አሳፋሪ ስህተት ርስዎ ሊሠሩ የቻሉት ርስዎ እንደ ጣኦት ከሚያመልኩዋቸው ኢትዮጲስት-ተብዬዎች አንዱ የነበረው ኮንቲ ሮሲኒ በመንደርተኞች መረጃ ላይ ተንተርሶና ተሳስቶ አባቱን ልጅ፣ ልጁን አባት አድርጎ ስቶሪያ ዴ ኢትዮጵያ ብሎ በጻፈው መጽሐፍ ውስጥ በስህተት ያስቀመጠውን ርስዎ ምንጩን ሳያጣሩ በቀጥታ ከተክለጻድቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአጼ ይኩኖአምላክ እስከ አጼ ልብነድንግል መጽሐፍ ላይ ስለገለበጡ ነው። ስለ ተስፋእየሱስ እናት ማንነት ይሄው ጣልያናዊ የዘባረቀውን እርስዎም በዛው ፅሁፍዎ እንደገደል ማሚቶ አስተጋብተዋል። ርስዎ ኢትዮጵያውያን ባለታሪኮችን ስለሚንቁ እንጂ (ኢትዮጵያውያንን ሲንቁ ራስዎንም እንደናቁ ይገንዘቡ) ኢትዮጵያውያን ባለታሪኮች ያኖሩትን ሸዋ የተደበቁትን የአክሱም ነገሥታት ዝርያዎች የስም ዝርዝር ቢመለከቱ ኖሮ ይህን ግዙፍ ስህተት ባልፈጸሙ ነበር።

እሱውም ከላይ ወደታች እንደሚከተለው ነው፦

ድልነአድ፣ አግባጽዮን፣ ጽንፈአርእድ፣ ነጋሺ ዛሬ፣ አስፍሃ፣ ያእቆብ፣ ባህር-ሰገድ እና እድም-አሰግድ ናቸው። የመጨረሻው የተስፋእየሱስ (የኩኖአምላክ) አባት ነው። ለወደፊቱም ይህን ሃቅ እወቁት።

ሁሉንም ስህተትዎን እዚህ አልዘረዝረውም። የአማራውን መኖር ለመካድ አማራ ብለው እንዳይጠሩ “አማራ” የሚለውን ቃል “ቤተዘመድ” የሚል አዲስ ስም አውጥተውለት አንባቢውን ግራ የሚያጋቡትን እዚህ አልጠቅሰውም። እርስዎ የእኔ እና የአማን በላይን የታሪክ ሥራዎች ለመተቸት ብቃት እንደሌለዎት ከዚህ በላይ ምን ማስረጃ አለ? የርስዎ ሙያ የቁዋንቁዋ ጥናት ብቻ ስለሆነ ታሪክ አለማወቅዎን አዋቂዎች ሲያስታውሱዎት እኔ እኮ ብራና ስመረምር ነው የምኖረው፣ ብለው ይከላከላሉ። መረመርኩ የሚሉዋቸው በቀጣሪዎችዎ በነጮቹ ከኢትዮጵያ የተዘረፉት፣ የተሰረቁትም ሆነ ያለዋጋቸው በሳንቲሞች ተለቅመው ቅጂም ሆኑ ወሪጂናሌ ወደ አሜሪካ የመጡት ብራናዎች የታሪክ ብቻ አይደሉም እንጂ የታሪክ ብቻ እንኩዋን ቢሆኑ እነሱን ካታሎግ ሲያደርጉ መዋልዎ ባለታሪክ አያስብሎትም፤ ወይም አያደርግዎትም። እውነቱን ንገረኝ ከአሉ እነሆ።

የኔ መጽሐፍ መውጣት ርስዎን እንቅልፍ የነሳው ሌላው ምክንያት በንግሥት-ሳባ ምክንያት ነው። አረቦች ስለ ንግሥት- ሳባ የሚዘላብዱትን ቅጥፈት እርስዎ ደግመው ጽፈው በአንድ አውሮፓ በሚታተም ጁርናል አሳትመው አንድ ኮፒ ከሦሰት ዓመታት በፊት ልከውልኝ ነበር። ስልክ ደውዬለዎት ቢልቂስና ሳባ ሁለት የተለያዩ ሴቶች እንደሆኑ አስረድቼዎት፣ “ሳባ” የሚለው ቃልም ከኩሽ የወረደ የወንድ ስም፣ እንዲሁም የከተማ መጠሪያ እንደሆነ አብራርቼልዎት፣ ርስዎ በጻፉት እንደማልስማማ ነገርኩዎት። እንግዲህ የማያውቁትን የኢትዮጵያ ታሪክ አውቃለሁ ብለው ሌላ ርስዎ የሚምታታቦት እና የሚያምታቱት የንግሥተ-ሳባ ማንነት ነው። ንግሥተ-ሳባ የሳባ (ከተማ) ንግሥት ማለት ነው። ፈረንጆቹ “ሺቫ” የሚሉት “ሳባ” ለማለት ነው። ርስዎ ሳባን “ቢልቂስ” ነች፣ የአረብ ንግሥት ነች፣ ይላሉ። ይህ ከስህተትም ስህተት፣ እጅግ ትልቅ ስህተት ነው። አረቦች ተምታቶባቸው ወይም ዝና ፈልገው ነው ሳባን ቢልቂስ የሚያደርጉት። ቢልቂስ ማን እንደሆነች ማወቅ ከፈለጉ ግን ቢልቂስ ማለት በኢትዮጵያዊትዋ እመቤትዋ በንግሥተ-ሳባ የተሾመች የየመን ንግሥት ነበረች። ሳባ እስዋን በየመን ላይ ልትሾም የቻለችው የመን በዛን ጊዜ ከኢትዮጵያ ግዛቶች አንደኛዋ በመሆንዋ ነው። ለእርስዎ እንደሚመስልዎት አረቦች ራሳቸው የሾሙአት አንዲትም የአረብ ንግሥት በታሪክ አልነበረችም። አረቦች ሴትን ከሰው ስለማይቆጥሩ ሴትን እንኩዋን በላያቸው ላይ በቤታቸውም ውስጥ አያነግሡም ነበር። እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ሴት ልጅን እና ሙሉ መብትዋን ስለምናከብር ባለፉት 3800 ዓመታት ውስጥ በርካታ ሴቶችን በኢትዮጵያ፣ የመን፣ ግብጽ፣ ሊብያና ኑብያ ግዞቶቻችን ላይ አንግሠን ነበር። ሴቶቻችን ደግሞ ደንበኛ “ንጹህ” ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ቢልቂስም ከሳባ በታች በየመኖች ላይ የተሾመች በዘርዋ ኢትዮጵያዊ ነበረች። ይህውሎት የኢትዮጵያ ታሪክ እንደዚህ ነው እንጂ እርስዎ እንደሚያናንቁትና እንደሚሳለቁበት አይደለም።

ብራና ሳገላብጥ ስለምውል እኔ የታሪክ አዋቂ ነኝ፣ ማለትዎን ይተዉና፤ በትህትና ጆሮዎንና ዓይንዎን ከፍተው አዳምጠው እና ዐይተው ገናና ታሪካችንን ይማሩ። ርስዎ እንደሚሉት ቢልቂስ ሳባ እና የአረብ ንገሥት ከሆነችስ እንደኛ አረቦች ለምን ሰሎሞናዊ ስርወ-መንግሥት አልመሰረቱም? ለምን እንደ እኛ ታቦት የላቸውም? ለምን እንደኛ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተወደሱም? ለምን እንደኛ ትንቢትስ አልተተነበየላቸውም? ለምን እንደ እኛ የሰለሞን ዝርያ ነን የሚሉ ለ3000 ዓመታት የነገሡ 225 ነገሥታት የላቸውም? ነው ወይንስ የርስዎ ቢልቂስ ከሰለሞን ልጅ አልወለደችም? መልሱን እኔው እነግርዎታለሁ። አዎን አልወለደችም። እናትዋ “ኢትያኤል” ስትል በልጅነትዋ ስም ያወጣችላት የኛዋ ንግሥተ-ሳባ ግን ከንጉሥ ሰለሞን ምንይልክን ስለወለደች እሱ ይዞት የመጣው ታቦት እኛ አለን፣ እሱ የሰለሞንን ስርወ-መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ መስርቶ ለ3000 ዓመታት የነገሡ 225 ነገሥታት እና ንግሥተነገሥታት ነበሩን፣ አጼ ኃይለሥላሴ የመጨረሻው ሰለሞናዊው ንጉሠነገሥት ነበሩ፣ እንላለን። አግአዝያን፣ ፈላሾችና ኦሪታዊው የአይሁዳውያን ኃይማኖትም ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገቡና ሊኖሩ የቻሉት ንግሥተ-ሳባ የኢትዮጵያ ንግሥተ-ነገሥታት ሆና ሳለ ከኢትዮጵያ ተነስታ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ፣ ከንጉሥ ሰለሞን ምኒልክን በመውለድዋ ነው እንላለን። እርስዎ ግን ይህን ታሪካችንን ያጣጥላሉ፤ ይክዳሉ፤ አፈታሪክ ነው ይላሉ፤ እሱንም እስከነአካቴው ለአረቦችም ይዳርጋሉ። ስለ ንግሥተ-ሳባ እና ቢልቂስ ማንነት በዚህ ርስዎ ልብወለድ በሚሉት መጽሐፌ ውስጥ ልዩ ልዩ ማስረጃዎች ደርድሬ ፍርጥርጥ አድርጌ በ53 ገጾች አስሬዋለሁ። ሁለተኛም ይህ ጥያቄ እንዳይነሳ የመጨረሻ ፍርድ ሰጥቼበታለሁ። ርስዎ ያውጡት እና የኔን አነጻጽሮ የትኛው ለህሊና እውነት እንደሆነ አንባቢ ይፍረድ።

(ክፍል ሁለት ይቀጥላል። መጽሐፌን አስመልክቶ ስለ አሰፈሩት ተጨማሪ ነጥቦች በክፍል ሁለት ውስጥ አካትታለሁ።)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!